የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ የምርጫ ባለሥልጣናትን ማስፈራራት እንዲያቆም በፍርድ ቤት ታዘዘ

ሁለት ሴት መራጮች ድምፅ እየሰጡ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የፌዴራል ዳኛ የአሜሪካ መንግሥት የአካባቢ እና የግዛት የምርጫ ባለሥልጣናት በድምጽ አሰጣጥ ሒደት ውስጥ ባላቸው ሚና ምክንያት የወንጀል ክስ ይመሠረትባችኋል በሚል ማስፈራራት እንዲያቆም ትዕዛዝ ሰጡ።

የፍትሕ ሚኒስቴር አንዳንድ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ወደ ጎን እንዲተዉ ወይም የትራምፕ አስተዳደር መራጮቹ የአሜሪካ ዜጋ ላይሆኑ ይችላሉ ብሎ ክስ የሚያቀርብባቸውን ድምፆች እንዲሰርዙ መጠየቅ ማቆም እንዳለበት የካሊፎርኒያ ዳኛ ወስነዋል።

ውሳኔው የመጣው በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ከመካሄዱ ከጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ነው።

ምርጫው የአሜሪካን የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ኮንግረስ) የሚቀጥሉትን ሁለት የዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመናት የሚቆጣጠረው የትኛው የፖለቲካ ፓርቲ እንደሆነ ይወስናል።

ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ውሳኔውን በመተቸት "የምርጫ ማጭበርበርን ለምን ይቃወማሉ?" ብለዋል።

ባለፈው ወር መጀመሪያ የፍትሕ ሚኒስቴሩ በካሊፎርኒያ ለግዛቱ ጸሐፊ እና ለሎስ አንጀለስ ግዛት መዝገብ ቤት ደብዳቤዎችን ልኳል።

በደብዳቤው የትራምፕ አስተዳደር "ዜጋ ያልሆኑ" ናቸው ብሎ የሚያምኗቸውን 20,000 የተመዘገቡ መራጮችን የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ውድቅ እንዲያደረጉ መጠየቁን የፍርድ ቤት ሰነዶች አሳይተዋል።

ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ደግሞ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት የታጠቁ ወታደሮች በመላው ካሊፎርኒያ ለካውንቲ ባለሥልጣናት እና ሠራተኞች መራጮችን ከመዝገብ ካላስወገዱ የወንጀል ክስ ይገጥማችኋል ብለው የሚያስፈራሩ ደብዳቤዎችን ልከዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ነገር ግን የምርጫ ሠራተኞች እነዚህን ጥያቄዎች ማሟላት እንደማይችሉ ተናግረዋል። በግዛት እና በፌዴራል ሕግ የሚጠየቁትን የምርጫ ሂደቶች መከተል እንዳለባቸው ተናግረዋል። አንድ ዳኛ ሁኔታውን ተመልክተው፤ በምርጫው ላይ "ውድመት" ያስከትላል በሚል የፌደራል ባለሥልጣናትን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።

በተመሳሳይ ጊዜ የፍትሕ ሚኒስቴሩ በካውንቲ የምርጫ ባለሥልጣናት ላይ የወንጀል ምርመራ መጀመሩን እና የፌዴራል ከፍተኛ የሕዝብ ዳኞች (ጁሪ) መጥሪያ ማውጣቱ ተነግሯል።

የምርጫ ሠራተኞችን የሚወክሉ የሲቪል መብቶች ቡድኖች እና የሠራተኛ ማኅበራት የፍትሕ ቢሮው "ምርጫውን ለማስተዳደር ባላቸው ግዴታ ላይ ጣልቃ ገብቷል" በሚል ክስ መሥርተዋል።

ክሱን የተመለከቱት ዳኛ ትሪና ቶምፕሰን አስተዳደሩ ድርጊቱን እንዲያቆም ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ዳኛዋ በትዕዛዛቸው "ተከሳሾቹ ድርጊቱ ዜጋ ያልሆኑ ሰዎች የሚያደርጉትን ሕገ-ወጥ የድምጽ አሰጣጥ ለማስቆም እንደሆነ ቢናገሩም፤ ድርጊታቸው በምርጫ አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ በመግባት እና ሕጋዊ መራጮችን የመከልከል ውጤት ሊኖረው ይችላል" ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ተመሳሳይ ደብዳቤ በዋሽንግተን ግዛት መላኩንም ዳኛዋ ጠቅሰዋል።

የፌደራል ባለሥልጣናት ድርጊት ትራምፕ እና አስተዳደራቸው እየተስፋፋ ነው ብለው የሚያምኑትን የመራጮች ማጭበርበር ለመዋጋት ለዓመታት የዘለቀ ዘመቻ አካል ነው።

ይሁን እንጂ የትራምፕ አስተዳደር የሚያነሳው ማጭበርበር እጅግ በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰት መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።

ከሁለት ቀናት በኋላ ከሚካሄደው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በፊት ፕሬዝዳንቱ በድምጽ አሰጣጡ ደኅንነት ላይ ጥርጣሬ ፈጥረዋል።

በፖስታ ድምጽ አሰጣጥ ላይ "ከፍተኛ" ማጭበርበር እንደሚፈፀም እና ዜጋ ያልሆኑ ሰዎች ድምጽ መስጠታቸውን በመጥቀስ ክስ አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንቱ በአሜሪካ ውስጥ የመራጮችን ማጭበርበር ሪፖርት ላደረጉ ሰዎች አንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንደሚሰጡም ተናግረዋል።