ኤአይ በሰው ልጆች ላይ "ቅስፈት" ደቅኗል ሲል አንትሮፕክ አስጠነቀቀ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አንትሮፕክ የአክሲዮን ገበያ ሽያጩን ከመጀመሩ በፊት ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) በሰው ልጆች ላይ "አሰቃቂ ወይም የኅልውና ስጋት" ሊደቅን ይችላል ሲል አስጠነቀቀ።

ኩባንያው ለገበያ ሲቀርብ 1.8 ትሪሊዮን ዶላር ዋጋ ከተገመተው ስፔስኤክስ የበለጠ ዋጋ እንደሚኖረው ተገምቷል።

አንትሮፒክ ምን ያህል ድርሻዎችን ለገበያ እንደሚያወጣ፣ የድርሻዎች ዋጋ ወይንም መቼ ይፋ እንደሚያደርግ እስካሁን አላስታወቀም።

የ 'ክለውድ ቻትባት' ሠሪ የሆነው ኩባንያው በዓመቱ መጀመሪያ አጋማሽ 16.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ያሳወቀ ሲሆን፤ 80.7 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ ገጥሞኛልም ብሏል።

'ናስዳቅ' በተባለው የአክሲዮን ገበያ ላይ ድርሻዎችን ለገበያ እንደሚያቀርብ የገለፀው አንትሮፒክ፤ ይህም ሙሉ ለሙሉ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ላይ ያተኮረ የመጀመሪያው ኩባንያ ያደርገዋል።

እርምጃው ለመጪው የቴክኖሎጂ ልማት ናሙናም ያደርገዋል።

አክሲዮኑን ለመሸጥ ባቀረባቸው ሰነዶች ላይ አንትሮፒክ በፖሊሲ አውጪዎች፣ በተቆጣጣሪዎች እና በተመራማሪዎች እንዲሁም በድርጅቱ ሠራተኞች ዘንድ የኤአይ ሥርዓት በሰው ልጆች ላይ ትልቅ ስጋት መደቀኑ ይነሳል ብሏል።

የላቀ የኤአይ ሥርዓት "ያለ ክትትል፣ ቁጥጥር እና የደኅንነት መመሪያዎች ከለማ፣ ከተሠራ እና ወደ ሥራ ከተሰማራ ለሰው ልጆች ቅስፈት ወይም የኅልውና አደጋ ይደቅናል። በዋናነት እንዲህ ዓይነት ሥርዓት ለሌላ ዓላማ ከዋለ፣ ከተራባ፣ ለመሣሪያነት ከዋለ ወይም ያለ ተጠያቂነት ሥራ ላይ ከገባ. . . " ሲል አስጠንቅቋል።

አንትሮፒክ ከአምስት ዓመታት በፊት በዋና ሥራ አስፈፃሚው ዳሪዮ አሞዲ፣ በእህታቸው ዳንኤል አሞዲ እና በሌሎች አምስት ሰዎች የተመሠረተ ኩባንያ ነው። የኩባንያው የባለቤትነት የድርሻ ሽያጭን ለሕዝብ ለመክፈት ያለውን ፍላጎት የገለፀው ባለፈው ዓመት መጨረሻ ሰኔ ወር ላይ ነበር።

ዋነኛ ተቀናቃኙ የሆነው 'ኦፕንኤአይ' ወዲያው ይህን ፈለግ በመከተል በሚቀጥለው ዓመት አክሲዮን መሸጥ እንደሚጀምር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ተናግረዋል።

ይህ ዕቅድ የኩባንያው ኤአይ የሳይበር ደኅንነት እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ጥሰቶችን ከመፈፀሙ በኋላ የተሰማ ነው።

የሁለቱም ኩባንያዎች የአሁን እና የቀድሞ ሠራተኞች ኤአይ ቴክኖሎጂዎች ወደፊት የሰው ልጅ ላይ ከሚከሰቱ ጉዳቶች የመጠበቅ አቅም እንዳይኖራቸው ተደርገው እየለሙ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

አንትሮፒክ ሰኞ ዕለት የአክሲዮን ገበያውን ለመክፈት ዕቅዱን ሲያሳውቅ የታዋቂው አሜሪካዊ ሙዚቀኛ ኤልቨስ ፕሬስሊ ሙዚቃ ባለቤት የኤአይ ኩባንያው 'ክላውድ' የተባለውን ቻትቦትን ለማሠልጠን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሙዚቃዎችን ተጠቅሟል በሚል ከስሰዋል።

አንትሮፒክ አዲስ ሰነድ ላይ ከዚህ ቀደም ኤአይ ለሰዎች ጥቅም በሚሰጥ መንገድ ለማልማት የገባውን ቃል በድጋሚ አስታውሶ፤ ለመዋዕለ ነዋይ አፍሳሾቹ ደግሞ አደጋውን አስጠንቅቋል።