ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሳሳቢ የሳይበር ደኅንነት ተጋላጭነት መገኘቱን ተከትሎ በዓለም ዙሪያ በርካታ ድረ ገጾች እንዲወርዱ ተደረገ
አብዛኛውን የኢንተርኔት ክፍል በሚያንቀሳቅሰው የፕሮግራሚንግ ቋንቋ ላይ ሁለት እጅግ አሳሳቢ የሳይበር ደኅንነት ክፍተቶች መገኘታቸውን ተከትሎ ድረ ገጾች ማሻሻያ እንዲያደርጉ ዓለም አቀፍ መንግሥታት እና ተቋማት አሳሰቡ።
ለጥቃት ተጋላጭ የሚያደርጉት ክፍተቶች የተገኙት 'ፒኤችፒ' በተባለው የፕሮግራሚንግ ቋንቋ ውስጥ ነው። ይህን ጉድለት የሚደፍን ማስተካከያ ትናንት ረቡዕ ተደርጓል።
ማሻሻያውን ተግባራዊ ማድረግ የማይችሉ ተቋማት ድረ ገጾቻቸውን ከአገልግሎት ውጪ ማድረግ እንዳለባቸው በርካታ የሳይበር ደኅንነት ኤጀንሲዎች መክረዋል።
ይህንን ተከትሎም እንደ የፊንላንድ መንግሥት፣ የስኮትላንድ ዋና ከተማ ኤድንበራ ምክር ቤት እና ቢቢሲ ያሉ ተቋማት ገጾቻቸውን ከኢንተርኔት ላይ እንዲያወርዱ አስገድዷል።
ይህ ጉድለት እንዳለ የተደረሰበት በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ነው። የሳይበር ደኅንነት ተቋም የሆነው 'ዊዝ' እንደሚገልጸው፤ ይህ ጉድለት የዓለምን ገጽታ እየለወጠ ባለው ኤአይ አማካኝነት ከተደረሰባቸው "የደኅንነት ተጋላጭነቶች እጅግ የከፋው" ነው።
ክፍተቱ መገኘቱን ተከትሎ፣ ፊንላንድ የአገሪቱ መንግሥትን ይፋዊ የድረ ገጽ አገልግሎቶች ለጊዜው እንዲዘጉ አድርጋለች። የኔዘርላንድስ የሳይበር ደኅንነት ተቋም በበኩሉ ለጥቃት ተጋላጭ የመሆን ዕድል በመኖሩ ድረ ገጹን ከአገልግሎት ውጪ ማድረጉን ገልጿል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ደግሞ፣ ተቋማት ማሻሻያውን ተግባራዊ ማድረግ የማይችሉ ከሆነ ሥርዓቶቻቸውን ከኢንተርኔት ላይ እንዲያወርዱ በኤክስ ገጹ መክሯል።
ዋይት ሀውስ እንደገለጸው የአሜሪካ የፌደራል መሥሪያ ቤቶች ችግሩን በቶሎ ለመፍታት ዋና ዋና ከሚባሉ የኤአይ ምርምር ተቋማት ጋር እየሠሩ ነው።
የጃፓኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናኤ ታካኢቺ በኤክስ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአገሪቱ ዜጎች ያሏቸው ይፋ የሆኑ ድረ ገጾች የተሠሩበት ፕሮግራሚን ቋንቋ 'ፒኤችፒ' መሆን አለመሆኑን እንዲያረጋግጡ አሳስበዋል።
የኢንተርኔት ላይ ኢንሳይክሎፔዲያ የሆነውን 'ዊኪፒዲያ' የሚያስተዳድረው ዊኪሚዲያ ፋውንዴሽን፣ የደኅንነት ተጋላጭነቶችን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎ የተወሰኑ ተጠቃሚዎች ረቡዕ ዕለት አንዳንድ የዊኪፒዲያ ክፍሎችን መጠቀም አልቻሉም ነበር።
ይህ ግዙፍ የደኅነንት ተጋላጭነት መኖሩ የተደረሰበት 'ካሊፍ' እና 'ዊዝ' በተባሉት የሳይበር ደኅንነት ተቋማት ውስጥ በሚሠሩ ተመራማሪዎች ነው።
ከተቋማቱ አንዱ የሆነው ካሊፍ እና ፒኤችፒ ፋውንዴሽን የኤአይ ኩባንያ የሆነው 'ኦፕንኤአይ' ያስጀመረው 'ፓች ዘ ፕላኔት' የተባለ ፕሮግራም አካል ነበሩ።
ተቋማት በዚያ ፕሮግራም አማካኝነት በድረ ገጽ ግንባታ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን ማግኘት እና ማስተካከል እንዲችሉ የላቁ የኤአይ መሣሪያዎች እንዲጠቀሙ ተፈቅዶላቸዋል።
ኦፕን ኤአይ ባወጣው ጦማር፣ ግኝቱ "በቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ተፅዕኖ ካሳደሩ የደኅንነት ጉዳዮች አንዱ ነው" ብሏል። በራሱ ኩባንያ ውስጥ የሚሠራ አንድ ተመራማሪም ሌሎቹ ተቋማት ጉዳዮች በደረሱበት ተመሳሳይ ጊዜ ተጋላጭነቱ መኖሩን ደርሶበት እንደነበር ገልጿል።
ይህ ክፍተት ከአስር ዓመት በላይ ሳይታወቅ ቆይቷል። ነሐሴ ላይ ግን ተመራማሪዎቹ የላቀ የኤአይ መሣሪያ እንዲጠቀሙ በተፈቀደላቸው ከጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ተደርሶበታል።
ምርመሩን ካደረጉት ተቋማት አንዱ የሆነው 'ዊዝ'፣ "ይህ ሒደት እውን እንዲሆን የላቁ የኤአይ ሞዴሎች ወሳኝ ሚና ነበራቸው፤ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በተለያዩ መተግበሪያዎች ላይ የሚሠሩ የጥቃት አጋላጮችን እንድናዘጋጅ እና እንድንጠቀም አስችለውናል" ብሏል።
እንደ ተቋሙ ገለጻ "70 በመቶ ገደማ" የሚሆነው የኢተርኔት ክፍት ለዚህ ክፍተት ተጋላጭ ነው። ቢቢሲ ይህንን ቁጥር በገለልተኝነት አላረጋገጠም።