ፕሬዝዳንት ዢ 'ሥልጣናቸውን ሊያጠናክሩ የሚችሉበት' በዝግ የሚካሄደው የቻይና ትልቁ ፖለቲካዊ ጉባኤ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በቻይናዋ መዲና ቤይጂንግ ውስጥ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚታደሙበት ትልቅ ፖለቲካዊ ጉባኤ በዝግ እየተካሄደ ነው። ይህ ጉባኤ ገዢው የኮሚኒስት ፓርቲ በቀጣዮቹ ዓመታት ምን ዓይነት አካሄድ እንደሚከተል ሊወስን ይችላል።

ለአምስተኛ ጊዜ በሚካሄደው ምልአተ ጉባኤ ላይ 300 ገደማ የኮሚዩኒስት ፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ይሰበሰቡበታል። የቻይና መንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ፣ ይህ ጉባኤ በፓርቲው አባላት ዘንድ "ዲሲፕሊንን ለማጥበቅ" የሚያስችል መንገድ ይጠርጋል።

ዛሬ ሰኞ የጀመረው ጉባኤ ለአራት ቀናት ይቆያል። ጉባኤው፣ በቅርቡ አመራሮች ላይ የሹም ሽር እርምጃ የወሰዱት ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ሥልጣናቸውን ይበልጥ የሚያጠናክሩበትን ዕድል ይሰጣቸዋል።

በተለመደው አሰራር መሠረት፣ በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ ምልዓተ ጉባኤ እጅግ ሚስጥራዊ ነው። የተላለፉ ዋና ዋና ውሳኔዎች እና ዝርዝር ማብራሪያ የያዘ ሰነድ ግን ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ ይፋ ይደረጋል።

የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ምልዓተ ጉባኤ ምንድነው?

ምልዓተ ጉባኤው በየዓመቱ ቢያንስ አንድ ጊዜ የሚካሄድ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ዝግ ስብሰባ ነው።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ሲሆን ብዙውን ጊዜ በአንድ የሥራ ዘመን ውስጥ ሰባት ምልዓተ ጉባኤዎች ይካሄዳሉ። ጉባኤዎቹ የአገሪቱ አመራር ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎችን የሚያመለክቱ ስለሚሆኑ በትኩረት ይጠበቃሉ።

ቅድሚያ የሚሰጣቸው አዳዲስ አጀንዳዎች የሚቀረጹበት እና አዲስ ማዕከላዊ ኮሚቴ የሚዋቀርበት ቀጣዩ የፓርቲ ኮንግረስ ስብሰባ አንድ ዓመት ብቻ የቀረው በመሆኑ፣ የዚህ ዓመቱ ጉባኤ እየተካሄደበት ያለው ወቅት ወሳኝ ነው።

በፓርቲው ይፋዊ አሰራር መሠረት ማዕከላዊ ኮሚቴው የፓርቲውን ከፍተኛ አመራር የሚመርጥ ቢሆንም፣ ወደ ምርጫው የሚያመሩት ትክክለኛ ሂደት ግን በፓርቲው ልሂቃን ብቻ የሚያዝ ሚስጥራዊ ጉዳይ ነው።

የፓርቲው መሪ የሚሆን ሰው የሚቆይበት ጊዜ ለመወሰን ተቀምጦ የነበረው የሥልጣን ዘመን ገደብ በመሻሩ፣ ቀጣዩ የፓርቲ ኮንግረስ ዢን የአገሪቱ መሪ አድርጎ በድጋሚ እንደሚመርጥ ጥርጥር የለውም።

የዘንድሮው አጀንዳ ምንድን ነው?

ከዚህ ቀደም በተደረጉ የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሺ የፓርቲው "አስኳል" እንደሆኑ የታወጀ ሲሆን ያለገደብ በመሪነት እንዲቆዩ የሚያስችለው የሥልጣን ዘመን ገደብም ተነስቷል። ስብሰባዎች "የዢ ጂንፒንግ እሳቤ" በመባል የሚታወቀውን የግል ፍልስፍናቸውም ከቀድሞው የፓርቲው ሊቀመንበር ማኦ ጋር በእኩል ደረጃ የሚያስቀምጥ ውሳኔ ለማስተላለፍም ጥቅም ላይ ውለዋል።

የዚህ ዓመቱ ጉባኤ ዢ በቀጣይ በሚደረገው የኮንግረስ ስብሰባ ላይ የሚቀርቡ ስትራቴጂዎችን በመወሰን የአባላቱ አመለካከት ተመሳሳይ መስመር ላይ መሆኑን እንዲሁም ተወካዮችም ታማኝ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ ዕድል ይሰጣቸዋል።

እስከ ሐሙስ የቀቆየው ይህ ጉባኤ የሚካሄድበት ትክክለኛ ቦታ እንኳ በይፋ አልተገለጸም። ከዚህ ቀደም የተደረጉ ምልዓተ ጉባኤዎች ቤጂንግ በሚገኘው ጂንግሲ ሆቴል ውስጥ ይካሄዱ ነበር።

21 አባላት ባሉት ፖሊትቢሮ መስከረም ላይ የሰጠው ገለጻ እንደሚያመለክተው፣ በጉባኤው ላየዕ "የፓርቲውን አጠቃላይ ጥብቅ አስተዳደር ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ወደፊት ማራመድ በሚቻልባቸው በርካታ ዋና ዋና ጉዳዮች" ላይ ውሳኔ ይተላለፈዋል።

ብዙዎች ይህንን የተገነዘቡት፣ በርቀት ከሚገኙ የፓርቲ ባለሥልጣናት ታዛዥነትን እና ውጤታማነትን ይበልጥ ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት እንደሆነ ነው።

የጉባኤው አቅጣጫ ይህ መሆኑ፣ በቅርቡ ፓርቲው ውስጥ በተወሰዱ መጠነ ሰፊ ከሥልጣን የማንሳት እርምጃዎች ምክንያት የጎደሉትን "ባዶ ወንበሮች" የሚመለከቱ ተሰብሳቢዎች እጣ ፈንታቸውን በተመለከተ በስጋት ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ ነው።

"የሞራል ብልሹነት" ጨምሮ በአጠቃላይ በቀረቡ የሙስና ክሶች ምክንያት በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሥልጣን ተባርረዋል።

ባለሙያዎች፣ "የሞራል ብልሹነት" የሚለውን ክስ የሚመለከቱት ለዢ የማይታመኑ ሰዎችን ለማጥቃት እንደሚቀርብ ውንጀላ ነው። ምክንያቱም በጥቅሉ ለፓርቲው ታማኝ አለመሆን እንደ "ሞራል" ብልሹነት ሊወሰድ ይችላል።

በእስያ ሶሳይቲ የፖሊሲ ኢንስቲትዩት ግምት መሠረት፣ በአውሮፓውያኑ በ2022 ማዕከላዊ ኮሚቴውን ከተቀላቀሉት 44 የሠራዊት አባላት መካከል እስካሁን ያልተነሱት ሁለቱ ብቻ ናቸው።

የቻይናን የጦር ኃይሎች የሚመራው ባለሰባት አባላቱ ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮሚሽን የአባላቱ ቁጥር ወደ ሁለት ወርዷል። ሁለቱ የኮሚሽኑ አባላት ዢ ጂንፒንግ እና አንድ ሌላ ጄኔራል ናቸው።

ዛሬ የተጀመረው ምልዓተ ጉባኤ ዢ የዚህ ወታደራዊ ኮሚሽን አባል የሚሆኑ አዲስ ወታደራዊ አመራሮችን መምራት እንዲችሉምቹ ዕድል ይፈጥራል።