በምርጫ የተሸነፉት የብራዚል ፕሬዚደንታዊ ዕጩ ቦልሶናሮ ፓስፖርታቸው መሰረዙን ተከትሎ ወደ አሜሪካ ሸሹ

የብራዚል ፕሬሲደንታዊ ዕጩ ፍላቪዮ ቦልሶናሮ በእሁዱ ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ነጭ ሸሚዝ ለብሰው ንግግር ሲያደርጉ ከአንገት በላይ የሚታዩበት ፎቶ
የምስሉ መግለጫ, ሽንፈታቸውን ያልተቀበሉት ፍላቪዮ ቦልሶናሮ ምርጫው እንዲሰረዝ ጥሪ አቅርበዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

በፕሬዚደንታዊ ምርጫው የተሸነፉት ፍላቪዮ ቦልሶናሮ፣ ብራዚል ፓስፖርታቸውን ከሰረዘች ከጥቂት ሰዓታት በኋላ አሜሪካ መግባታቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ገለፁ።

ከሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ምርመራ እተደረገባቸው የሚገኙት የቀኝ ዘመም እጩው፣ ፓስፖርታቸውን እንዲያስረክቡ የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መስጠቱን ተከትሎ ነው አገራቸውን ለቅቀው የሄዱት።

ቦልሶናሮ በዚህ ጉዳይ ገና ክስ ያልተመሰረተባቸው ቢሆንም የቀረበባቸውን ውንጀላ አስተባብለዋል።

ቦልሶናሮ ፓስፖርታቸውን ለባለሥልጣናት እንዲያስረክቡ የተሰጣቸው የመጨረሻ ቀን ካለፈ በኋላ ማክሰኞ ዕለት የተሰረዘ ሲሆን፣ ይህም ከብራዚል ወጥተው ሊሆን ይችላል የሚል ሰፊ ግምት እንዲኖር አድርጓል።

ምንጮች ለቢቢሲ ብራዚል እና ቢቢሲ ሙንዶ እንደተናገሩት፣ ቦልሶናሮ ፍሎሪዳ ደርሰው ከታናሽ ወንድማቸው ኤዱዋርዶ ጋር ተገናኝተዋል። ሆኖም፣ ከብራዚል ወደ አሜሪካ የተጓዙበት ትክክለኛ መንገድ ግልጽ አይደለም።

ቢቢሲ ከሁለቱ ወንድማማቾች አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ቦልሶናሮ ወደ አሜሪካ መግባታቸው የተዘገበው፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለብራዚሉ የፕሬዚደንታዊ ምርጫ ተሸናፊ እና ለቤተሰባቸው ቪዛ እንደሚሰጥ እንዲሁም ወደ አገሪቱ እንዲገቡ እንደሚፈቅድ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ካረጋገጡ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።

ቢቢሲ ዋይት ሀውስን፣ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትን እንዲሁም የአሜሪካ እና የብራዚል ኤምባሲዎችን በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ጠይቋል።

ከተጠረጠሩበት የሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ጋር በተገናኘ ቦልሶናሮ በ24 ሰዓታት ውስጥ ፓስፖርታቸውን ለፖሊስ እንዲያስረክቡ የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰኞ ዕለት አዝዞ ነበር።

ቦልሶናሮ በወቅቱ በሰጡት አስተያየት ከአገራቸው እንደማይወጡ እና በእሁዱ ምርጫ ባሸነፉት የግራ ዘመም ተቀናቃኛቸው ፕሬዚደንት ሉላ ዳሲልቫ ላይ የሚደረገውን ተቃውሞ እየመሩ እንደሚቀጥሉ ተናግረው ነበር።

ፓስፖርታቸውን እንዲያስረክቡ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ቦልሶናሮ "ያሉበትን በፍፁም እንደማያውቁ" ጠበቆቻቸው ለቢቢሲ ብራዚል ገልፀዋል።

"ስለዚህ ጉዳይ ምንም አናውቅም፣ ምን እንደተፈጠረም እስካሁን መረጃ የለንም" ሲሉ አንድ ጠበቃቸው ተናግረዋል።

ቦልሶናሮ ሰኞ ከሰዓት በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቪዲዮ ከለጠፉ በኋላ ምንም አይነት ይፋዊ መግለጫ አልሰጡም።

አንድ የፖሊስ ምንጭ ለቢቢሲ ኒውስ ብራዚል እንደገለፁት፣ የፌዴራል ፖሊስ መኮንኖች ቦልሶናሮ ወደ ጎረቤት አገር አርጀንቲና ተጉዘው እንደሆነ ለማረጋገጥ የድንበር ማቋረጫዎችን መርምረዋል።

ይሁን እንጂ፣ የአርጀንቲና ባለሥልጣናት ቦልሶናሮ በማንኛውም የድንበር ማቋረጫ በኩል ወደ አገራቸው ስለመግባታቸው የተመዘገበ ማስረጃ እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቦልሶናሮ ስለ አባታቸው፣ የቀድሞው ፕሬዚደንት ዣየር ቦልሶናሮ የተሰራውን ፊልም ለመደገፍ ካወጡት የገንዘብ ምንጭ ጋር በተያያዘ በቀረቡባቸው የሙስና ክሶች ቀድሞዉንም ምርመራ ሲደረግባቸው ነበር።

አባታቸው ዣየር ቦልሶናሮ፣ መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ በማሴር ተፈርዶባቸው በቤት ውስጥ እስር ላይ ይገኛሉ።