በኢትዮጵያ 55 በመቶ ሴቶች ሚስትን ለመደብደብ የሚያበቃ ምክንያት አለ ብለው እንደሚያስቡ ጥናት አሳየ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ሴቶች ባል ሚስቱን ለመደብደብ አሳማኝ ምክንያት ይኖረዋል ብለው እንደሚያምኑ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ያደረገው ጥናት አመለከተ።
ሚስትን ለመምታት አሳማኝ ምክንያት እንዳለ የሚያስቡ ወንዶች ብዛት ከሴቶች ያነሰ ቢሆንም፤ ከዚህ ቀደም ከነበረው አንጻር በ11 በመቶ ጨምሮ ተገኝቷል።
ይህ ቁጥር ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ባካሄደው ሰፊ የሥነ ሕዝብ (ዴሞግራፊ) እና የጤና ዳሰሳ ጥናት ነው። በሐምሌ 2018 ዓ.ም. መጀመሪያ ይፋ በሆነው በዚህ ጥናት ውስጥ 30 ሺህ ገደማ ሰዎች ተሳትፈዋል።
የፕላን እና ልማት እንዲሁም ጤና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ተቋማትም የጥናቱ አካል ናቸው። ባለ 767 ገጹ ጥናት የዜጎች የትምህርት እና የሥራ ሁኔታ እንዲሁም የመጠጥ ውሃ፣ የንጽህና አገልግሎት እና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ያሉበትን ደረጃ ዳስሷል።
በሴቶች ላይ የሚደርሰው የቤት ውስጥ ጥቃት ጉዳይም በጥናቱ የተካተተ ሌላኛው ጉዳይ ነው። የጥናቱ ተሳታፊ የሆኑ ሴቶች እና ወንዶች ሚስትን መደብደብን በተመለከተ ያላቸውን ምልከታ እንዲያጋሩ ተጠይቀዋል።
አጥኚዎቹ፣ 'ሚስትን ለመምታት በቂ ምክንያት ናቸው ወይ?' ሲሉ አምስት ሁኔታዎችን ዘርዝረውላቸዋል። በምክንያትነት የቀረቡት፤ ምግብ ማቃጠል፣ መጨቃጨቅ፣ ለባሏ ሳታሳውቅ ከቤት መውጣት፣ ልጆችን ችላ ማለት እንዲሁም ወሲብ መከልከል ናቸው።
ከእነዚህ ምክንያቶች ውስጥ ቢያንስ አንዱ ሚስትን "ለመምታት በቂ እንደሆነ" ከተጠየቁ ሴቶች ውስጥ 55 በመቶ ያህሉ 'አዎ' የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ይህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ወንዶች ብዛት 39 በመቶ ነው።
ምላሹን የሰጡ አብዛኞቹ ወንዶች እና ሴቶች ሚስትን ለመምታት "በተገቢ" ምክንያትነት የጠቀሱት 'ልጆችን ችላ ማለት' የሚለውን ነው።
በጥናቱ ውጤት ላይ ሚስትን ለመምታት አሳማኝ ምክንያት እንዳለ የሚያስቡ ሴቶች ቁጥር ከወንዶች ቢበልጥም፤ ከዚህ ቀደም ከነበረው አንጻር ቀንሷል።
የስታቲስቲክስ አገልግሎት ከ10 ዓመት በፊት ተመሳሳይ ጥናት ባደረገበት ወቅት ይህ ምልከታ ያላቸው ሴቶች ቁጥር 63 በመቶ ነበር። ከ25 ዓመት በፊት ደግሞ 85 በመቶ የነበረ መሆኑ "በጊዜ ሂደት እየቀነሰ መምጣቱን" እንደሚያሳይ ጥናቱ ያረስዳል።
በተቃራኒው የወንዶች ቁጥር በ11 በመቶ ጨምሮ ታይቷል። ከአስር ዓመት በፊት ሚስትን ለመደብደብ 'ተገቢ' የሚሆን ምክንያት እንዳለ የሚያስቡ ወንዶች ብዛት 28 በመቶ ነበር።
በሴቶች መብት ላይ የሚሠራው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት 'ሴታዊት' ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ስኂን ተፈራ፤ ለቤት ውስጥ ጥቃት አሳማኝ ምክንያት እንዳለ የሚያስቡ ሴቶች ቁጥር ከወንዶች በልጦ መታየቱ አይዋጥላቸውም።
ሚስቶች ድብደባ የሚደርስባቸው በባሎቻቸው እንደሆነ ዶ/ር ስኂን ይጠቅሳሉ። "ብዙ ጊዜ ወንዶች ሲጠየቁ 'ሚስትን መምታት ልክ አይደለም' ይላሉ። ግን በዚህ ልክ ወንድ ሚስቱን መምታት ልክ አይደለም [ከተባለ ሚስቶቻቸውን] የሚመቱት ታዲያ ማናቸው?" ሲሉም ጥያቄ ያነሳሉ።
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጥናት መሠረት፤ ባል ወይም የፍቅር አጋር ኖሯቸው ከሚያውቅ ሴቶች ውስጥ 30 በመቶው አካላዊ፣ ወሲባዊ ወይም ስሜት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ደርሶባቸዋል።
ጥቃት ከደረሰባቸው ሴቶች ውስጥም 58 በመቶው እገዛ ለማግኘት አልሞከሩም እንዲሁም የተፈጸመባቸውን አልተናገሩም።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ዶ/ር ስኂን እንደሚናገሩት፣ ሴቶች በትዳር ውስጥ የሚፈጸም ድብደባን ተገቢ የሚያደርጉ ምክንያቶች እንዳሉ እንዲያስቡ የሚያደርጓቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ።
ሴቶች ያለ ዕድሜያቸው መዳራቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው እየተመለከቱት ያደጉት ጥቃት መኖሩ እንዲሁም በቂ ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ያላቸው አለመሆኑን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።
በአንዳንድ አካባቢዎች ላይም በሥነ ልቦና እና በአካል ላይ የሚደርሱ እንደ መደብደብ ዓይነት ጥቃቶች እንደ ጥቃት እንደማይቆጠሩም ዶ/ር ስኂን ያነሳሉ።
የስታቲስቲክስ አገልግሎት ጥናት፣ "ትምህርት እና የቤተሰብ ገቢ ሲጨምር፣ ሚስት ላይ የሚፈጸም ድብደባን የመቀበል አዝማሚያ ይቀንሳል" ይላል።
ትምህርት ካላገኙ የጥናቱ ተሳታፊዎች ውስጥ 63 በመቶው ሚስትን ለመደብደብ የሚያበቃ ምክንያት እንዳለ ያስባሉ። ከሁለተኛ ደረጃ በላይ ትምህርት ካገኙ ሴቶች መካከል ግን እንዲህ የሚያስቡት 29 በመቶው ብቻ መሆናቸውን ጥናቱ ያሳያል።
በከተማ ካሉ በይበልጥ በገጠራማ አካባቢዎች የሚገኙ ሴቶች ባ ልበሚስቱ ላይ ለሚፈጽመው ድብደባ ተገቢ ምክንያት እንዳለ ያምናሉ።
ጥናቱ ከተደረገባቸው ክልሎች ውስጥ ሚስትን ለመምታት አሳማኝ ምክንያት አለ ብለው የሚያምኑ ሴቶች በከፍተኛ መጠን የተገኙበት ሲዳማ ክልል ነው።
በክልሉ 74 በመቶ ሴቶች ይህንን ተቀብለው የተገኙ ሲሆን፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በ71 በመቶ በሁለተኝነት ተቀምጧል። 23 በመቶ ሴቶች ይህንን አመለካከት ይዘው የተገኙበት ሶማሌ ደግሞ አነስተኛ ቁጥር የተመዘገበበት ክልል ሆኗል።
የቤት ውስጥ ጥቃትን ተገቢ የሚያደርጉ ምክንያቶች እንዳሉ የሚያምኑ ሰዎችን አመለካከት ለመቀየር፤ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም የሚያጠናክሩ ተግባራትን ማከናወን እንደ መፍትሔ ተጠቅሷል።
የግንዛቤ መፍጠር ሥራዎችን ማስፋፋት እንዲሁም የሕግ፣ የጤና እና የሥነ ልቦና ድጋፍ አገልግሎቶችን ጥቃት ለሚደርስባቸው ሴቶች ተደራሽ ማድረግንም ጥናቱ በምክረ ሃሳብነት አስቀምጧል።















