ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰሜን ኮርያ ጠላፊዎች ለምን በዓለም ግዙፉ የተባለው የባይናንስ ዝርፊያ ዋነኛ ተጠርጣሪዎች ሆኑ?
በዓለማችን ትልቁ የክሪፕቶከረንሲ መገበያያ የሆነው ባይናንስ በተፈጸመበት ምንተፋ 6.3 ቢሊዮን ዶላር ተዘርፏል።
"ውስብስብ" በሆነው ምንተፋ (ሃኪንግ) ከተዘረፈው የዲጂታል ሀብት ውስጥ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚሆነውን እንዳይንቀሳቀስ ማገድ ችሏል። ቀሪው ከግማሽ በላይ የሆነ ሀብት ግን ሊመለስ ስለመቻሉ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም።
ሁለት ዋና ዋና የብሎክቼይን ተንታኝ ኩባንያዎች፣ እስከዛሬ ከተፈጸሙ ዝርፊያዎች ውስጥ ግዙፉ ሊሆን ይችላል በተባለለት በዚህ ጠለፋ ውስጥ፣ በሰሜን ኮሪያ መንግሥት የሚደገፍ ቡድን ዋነኛ ተጠያቂ መሆኑን የሚያመላክት መረጃ እንዳላቸው ገልጸዋል።
'ላዛሩስ ግሩፕ' ወይም 'ትሬደርትሬይተር' ስያሜ የሚታወቀው የሰሜን ኮሪያው የጠላፊዎች ቡድን፣ ተጠርጣሪ ስለመሆኑ "ከፍተኛ እርግጠኝነት" መኖሩን ቲአርኤም ላብስ እንዲሁም ቼይናሊሲስ የተባሉት ኩባንያዎች ተናግረዋል።
ከዓለም ደሃ አገራት አንዷ የሆነችው እና የኢንተርኔት አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ የተገደበባት ሰሜን ኮሪያ ከእንዲህ አይነቱ ዝርፊያ ጋር ስሟ ሲነሳ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
ባለሙያዎች፣ በኪም ጆንግ ኡን የሚመራው የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ገንዘብ ለማግኘት የሳይበር ወንጀል ይፈጽማል የሚል ክስ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ፒዮንግያንግ ግን ይህንን ውንጀላ በተደጋጋሚ አስተባብላለች።
ገንዘብ ከማግኘት ጋር የተያያዘ ባይሆንም፣ አስደናቂ የሚባለው የሰሜን ኮሪያ ሳይበር ጥቃት የተፈጸመው በአውሮፓውያኑ 2014 ነው። በዚህ ጥቃት ዒላማ የተደረገው፣ የአገሪቱ መሪ ኪምን ለመግደል ስለሚወጠን ሴራ የሚያሳየውን 'ዘ ኢንተርቪው' የተሰኘ የሆሊዉድ ፊልም ያዘጋጀው ሶኒ ፒክቸርስ ነበር።
በዚህ የሳይበር ጥቃት፣ የስቱዲዮው ከፍተኛ አመራሮች የተለዋወጧቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ አሳፋሪ የኢሜይል መልዕክቶች ይፋ ሆነዋል።
የአሜሪካ የፌዴራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ባለፈው ዓመት ባወጣው መረጃ፣ ባይቢት በተሰኘው የዲጂታል ገንዘብ መገበያያ ላይ ለተፈጸመው የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ዝርፊያ ተጠያቂዋ ሰሜን ኮሪያ መሆኗን ገልጾ ነበር።
እንደ ኤፍቢአይ ገለጻ፣ ትሬደርትሬይተር የተባለው የመንታፊዎች ቡድን የተዘረፉትን ንብረቶች ሕጋዊ ገንዘብ ለማድረግ እና ለመበታተን በፍጥነት ተንቀሳቅሷል። በመጨረሻ የተዘረፈውን ዲጂታል ሀብት ወደ ተጨባጭ ገንዘብ ለመቀየር ሲል ወደ ቢትኮይን እና ሌሎች ዲጂታል ሀብቶች ለውጧቸዋል።
ኤፍቢአይ ሰሜን ኮሪያ "ሕገ ወጥ የሳይበር ወንጀል እና ዲጂታል ሀብቶችን የመዝረፍ ድርጊት" ውስጥ ትሳተፋለች የሚል ክስ በስፋት ያቀርባል።
አገሪቱ ተስፋ የተጣለባቸው ተማሪዎችን ከዩኒቨርሲቲዎች በመመልመል እና በሰሜን ኮሪያ የስለላ ድርጅት በሚመሩ የጠላፊዎች ቡድን አባል በማድረግ የሳይበር ዘመቻዎቿን በስልታዊ መንገድ እንዳዋቀረች ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
የቴክኖሎጂ ቡድኖች ትንታኔ እእንደሚያሳየው፣ ከሚካሄዱት የሳይበር ጦርነቶች መካከል የተወሰኑት የሚፈጸሙት ከአገሪቱ ድንበር ወጣ ብሎ በቻይና ግዛት ውስጥ ከሚገኝ ስፍራ ነው።
አብዛኛዎቹ የሰሜን ኮሪያ የጠለፋ እንቅስቃሴዎች ገንዘብ ማግኘት ላይ ያተኮሩ ናቸው። የሰሜን ኮሪያ መንታፊዎች በ2022 የተፈጸመውን የ620 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ክሪፕቶከረንሲ ዝርፊያ አካሄደዋል በሚል ይጠረጠራሉ።
በአሁኑ ዝርፊያ ላይ፣ የሰሜን ኮሪያ መንታፊዎች ያገኙትን ልዩ ፈቃድ በመጠቀም፣ ከኢንተርኔት ጋር የተገናኘ የባይናንስ 'ሆት ዋሌት'ን የዲጂታል ሀብት በቀጥታ ወደ ጠላፊው የሚያስተላልፍበት እንዲሆን አድርገዋል የሚል ውንጀላ ቀርቦባቸዋል።
ባይናንስ ዝርፊያው ከሰሜን ኮሪያ ጋር ይያያዝ እንደሆነ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ በቀጥታ ምላሽ አልሰጠም።
መጀመሪያ ላይ ኩባንያው፣ የአንድ ኢንጅነር ላፕቶፕ ተጠልፎ፣ ፈቃድ የሌለው የገንዘብ ዝውውር ተደርጎ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንደነበረው ገልጿል። በኋላ ላይ ግን ጥቃቱ ከዚህም የሰፋ መሆኑን አስታውቋል።
የባይናንስ ተባባሪ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ሪቻርድ ቴንግ "በተከታይ ያካሄድነው ምርመራ ሰበራ የተደረገባቸውን ተጨማሪ ነጥቦች አግኝቷል" ብለዋል።
የባይናንስ ቃል አቀባይ አርብ ዕለት እንደገለጹት፣ ከተዘረፉት ንብረቶች ውስጥ ወደ 80 በመቶ የሚጠጉት ደኅንነታቸው የተጠበቀ ቢሆንም የቀረው ግን እስካሁን አልተደረሰበትም።
የሚቀርበው ውንጀላ እውነት የሚሆን ከሆነ፣ ይህ በታሪክ ግዙፉ የሆነ ዝርፊያ ተጠርጣሪዎቹ የሰሜን ኮሪያ ጠላፊዎች ምን ያህል አቅም እንዳላቸው የሚያሳይ ይሆናል። ለምንተፋ የሚጠቀሟቸው መሣሪያዎች እያደጉ መምጣታቸውንም ያመለክታል።
ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) መስፋፋት የሳይበር ጥቃት ፈጻሚዎች በኦውቶሜሽን እና በሌሎች መንገዶች አዳዲስ የወንጀል ማድረሻ አማራጮችን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
በዚህ መሠረት፣ በአሁኑ ዝርፊያ ውስጥም ወደ ባይናንስ ሥርዓት ውስጥ ሰርጎ ለመግባት ኤአይ ጥቅም ላይ ውሎ ሊሆን ይችላል የሚለው ግምት ምክንያታዊ ይሆናል።
የብሎክቼይን ኩባንያ ተንታኝ 'ቼይናሊሲስ' እንደገለጸው፣ መንታፊዎቹ ጥቅም ላይ ያዋሉት "ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ" የገንዘብ ዝውውር ስልት ነው።