ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ለዩክሬን 500 የፓትሪዮት ሚሳዔሎችን ሽያጭ አጸደቀች
አሜሪካ እየጨመሩ የመጡትን የሩሲያ የአየር ጥቃቶች ለመከላከል በጣም አስፈላጊ የሆኑ 500 የፓትሪዮት ሚሳዔሎች ለዩክሬን እንዲሸጡ ወሰነች።
ሆኖም የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ እነዚህን ሚሳዔሎች ለማግኘት "በርካታ ዓመታት" ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንዳስታወቀው፣ እነዚህ ዘመናዊ ፒኤሲ-3 የተባሉ ጠላፊ (ኢንተርሴፕተር) ሚሳዔሎች 2.1 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚፈልጉ ሲሆን ይህ ወጪ ሙሉ በሙሉ የኪየቭ አጋር በሆኑ የአውሮፓ አገራት እና በካናዳ የሚሸፈን ነው።
ዜሌንስኪ አርብ ምሽት በድጋሚ አሜሪካ የፓትሪዮት መሣሪያዎችን የመልቀቅ ሂደቱን እንድታፋጥን ጥሪ አቅርበዋል። እነዚህ መሣሪያዎች የሩሲያን አደገኛ ባለስቲክ ሚሳዔሎች ዒላማቸውን ከመምታታቸው በፊት ለመጣል ውጤታማ የሆኑ ብቸኛ መሣሪያዎች እንደሆኑም ገልጸዋል።
አሜሪካ ይህን አዲስ ውሳኔ ያሳለፈችው፣ አሜሪካ የሩሲያን ነዳጅ ለማግኘት በአገሪቱ ላይ የጣለቻቸውን አንዳንድ ማዕቀቦች ማላላቷን ተከትሎ በፕሬዚደንት ቭሎዲሚር ዜሌንስኪ እና ዶናልድ ትራምፕ መካከል ከተፈጠረው ውዝግብ በኋላ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት፣ ዩክሬን ጦርነቱን ለማስቆም ከሩሲያ ጋር ስምምነት ሊያደርግ የሚችል አዲስ መሪ የሚያስፈልጋት ጊዜ ደርሷል ብለው ነበር።
ሞስኮ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ የጀመረችው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በየካቲት 2022 ሲሆን ከዚያ በፊትም ክሬሚያን እና በምስራቅ ዶንባስ ክልል ያሉ አካባቢዎችን ተቆጣጥራ ነበር።
ዜሌንስኪ ከሳምንት በፊት በኦስሎ ከአሜሪካ ልዑካን ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ውጥረቱ በመጠኑ ተረጋግቷል።
አርብ ዕለት የወጣው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መግለጫ "የፓትሪዮት ሚሳዔሎቹ ሽያጭ በአውሮፓ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መረጋጋት ለማስፈን የሚያግዝ እና አጋር አገር ደኅንነትን በማጠናከር የዩናይትድ ስቴትስን የውጭ ፖሊሲና የብሔራዊ ደህንነት ግቦች ሊደግፍ የሚችል ነው" ብሏል።
ዩክሬን የመሣሪያዎቹን የግዥ ገንዘብ "በካናዳ፣ በጀርመን እና በኖርዌይ በሚሰጡ ድጋፎች አማካኝነት" እንደምትከፍልም መግለጫው አክሎ ገልጿል።
የግብይቱ "ዋና ተቋራጭ" የአሜሪካው ኩባንያ ሎክሂድ ማርቲን መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ "በዚህ ሽያጭ ውስጥ የአሜሪካ መንግሥት የሚያወጣው ምንም ገንዘብ የለም" ብሏል።
በሌላ በኩል፣ በ ጂ20 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ መገኘታቸውን በመቃወም የአውሮፓ ዲፕሎማቶች የቡድን ፎቶ ለመነሳት ሳይገኙ ቀርተዋል።
ስብሰባው በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ አስተናጋጅነት በአትላንታ እየተካሄደ ይገኛል።
የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤድ ሚሊባንድ በጉባዔው ላይ ላቭሮቭ ጠቅሰው በሰጡት አስተያየት "ይህን በቀጥታ ለሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልናገር፤ በዚህ ጦርነት ውስጥ ወራሪው ማን እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን" ካሉ በኋላ የሩሲያን መንግሥት በዩክሬን ንጹሃን ሲቪሎችን በመግደል ወንጅለዋል።
ዩክሬን በእጅጉ እየተሟጠጠባት ያለውን ወሳኝ የሚሳዔል አቅርቦት እንድታገኝ አንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ የአሜሪካን ፈቃድ ስትጠብቅ እንደነበር ዜሌንስኪ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ገልጸዋል።
አርብ ምሽት በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ደግሞ የአሜሪካውን ውሳኔ በደስታ ተቀብለው፣ ዩክሬን የፓትሪዮት ሚሳዔሎቹን "በአስቸኳይ" እንደምትፈልግ አመልክተዋል።
ሩሲያ በዋና ዋና የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቷን እያጠናከረች መሆኑንም የገለጹት ዜሌንስኪ፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በዩክሬን የኃይል ተቋማት ላይ "ከ30 በላይ የሩሲያ ጥቃቶች" መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
ምንም እንኳን ኪየቭ ጠላፊ ሚሳዔሎችን በእጅጉ ብትፈልግም፣ አሜሪካ ከኢራን ጋር ባላት ጦርነት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ የእነዚህ ሚሳዔሎች እጥረት እንዳለ ይታመናል።
ለዩክሬን ይቀርባሉ የተባሉት ቀድሞ የተመረቱ ሳይሆኑ አዲስ የሚመረቱ ሚሳዔሎች በመሆናቸው በፍጥነት የመድረሳቸው ዕድል ዝቅተኛ እንደሆነ ተገምቷል።
የፓትሪዮት ሚሳዔሎችን ማምረት ረጅም ጊዜ የሚወስድ ሲሆን፣ በአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት መረጃ መሠረት በዓመት የሚመረቱት 600 ሚሳኤሎች ብቻ ናቸው።