ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሞያሌ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት የነዋሪዎች ሕይወት ሲጠፋ፣ በርካቶች ወደ ኬንያ ተሰደዱ
በደቡብ ኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል በሚዋሰኑበት አካባቢ ከእሁድ ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ለግጭቱ ምክንያት የሆነው "ባንዲራ ያልተገባ ቦታ መተከሉ ነው" ያሉ ሲሆን ከ10 ዓመት ታዳጊ ጀምሮ በርከት ያሉ ነዋሪዎች በሁለቱም ወገን መገደላቸውን ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል በኩል የሞያሌ ከተማ ከንቲባ አቶ ገልማ ኮርቻ ረቡዕ ዕለት ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ግጭቱ ጥቅምት 8/2019 ዓ.ም መቀስቀሱን ተናግረዋል።
ከንቲባው የሶማሌ እና የኦሮሚያ ክሎች በሚዋሰንበት አካባቢ ሶማሌዎች "ድንበራቸውን አልፈው፣ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ገብተው የራሳቸውን አስተዳደር ባንዲራ ተክለዋል" ብለዋል።
ከንቲባው ባንዲራውን "የሚመለከተው አካል ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ አንሱ" ማለታቸውን አስታውሰው፣ በዚህ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት አንዲት የ13 ዓመት ታዳጊ "በጥይት ተመትታለች" ብለዋል።
ታዳጊዋ ሆስፒታል ከገባች ከአራት ቀን በኋላ መሞቷን ገልጸው አስከሬን ለቤተሰቦቿ እንዳልተሰጠም አስረድተዋል።
"ልጅቷን ሐኪም ቤት ወስደው አራት ቀን ካቆይዋት በኋላ የራሳችን ልጅ ናት ብለው እናት እና አባት ሰይመውላት ቀበሯት። አስከሬን ስጡን ብንል የእኛ ናት ቀበርናት አሉን" ብለዋል።
ቢቢሲ ሶማልኛ ያነጋገራቸው እና በእርዳታ ድርጅት ውስጥ የሚሠሩት አብድርሃማን ካራማ በበኩላቸው በአካባቢው አዲስ አስተዳዳር ተዋቅሮ እንደነበር ይናገራሉ።
የተቋቋመው አዲስ አስተዳደር ቢሮ ተከራይቶ እንደነበር ገልጸው "ሆኖም ከኦሮሚያ በኩል የተከራየው ቤት የእኛ ነው ሲሉ ተቃወሙ። በሶማሌ በኩል ሌላ ቤት እንዲፈልጉ ተነግሯቸው ችግሩ በስምምነት ተፈትቶ ነበር" ይላሉ።
ሁኔታው በዚህ እንዳለ በኦሮሚያ በኩል "የሚሊሻ እንቅስቃሴ ተጀመረ" ያሉት አቶ አብድርሃማን "ከዚያም ዛሬ ጠዋት [ሐሙስ] ተኩስ ተከፈተ። ከባድ ጉዳት ነው የደረሰው። በርካታ ቤቶች ተቃጥለዋል፤ ነዋሪዎችም ከተማውን ለቀው ወጥተዋል፤ በኋላ ላይ ነው የአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ለማረጋጋት የገቡት" ሲሉ ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት በኦሮሚያ ክልል በኩል የሚኖሩ ግለሰብ የሶማሌ ክልል የሞያሌ አስተዳደር ባንዲራ ሰቅሏል የተባለበት ቤት ከግለሰብ የተከራየው መሆኑን ተናግረዋል።
ነዋሪው አክለውም "መጀመርያ እዚህ አልነበረም አሁን ለምን እዚህ ተተከለ የሚል ጥያቄ ተፈጠረ" ሲሉ ያስረዳሉ።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲነሳ ጥያቄ አቅርበው "ምንም ተኩስ ሳይፈጠር መንግሥት መሃል ይግባ እና ይነሳ ተባለ" በማለት የነበረውን ሁኔታ ይናገራሉ።
ከዚህ በኋላም ሌላ ቦታም የግለሰብ ቤት ላይ ባንዲራው መተከሉን ገልጸዋል።
"መጀመርያም እነሱ የሆነ ነገር አስበው ነው ባንዲራ የሚተክሉት" የሚሉት ነዋሪው "ግጭት እንዲቀሰቀስ ይፈልጋሉ" ሲሉ ይከስሳሉ።
ግለሰቡ ባንዲራው የተተከለበትን ምክንያት እንደማያውቁ ተናግረው "ይህ የኦሮሚያ ድንበር ነው ለምን ይተከላል" በማለት አስረድተዋል።
የአራት ልጆች አባት መሆናቸውን እና ልጆቻቸውን ከጉብታ ስር ጥይት እንዳያገኛቸው ደብቀው እንደሚገኙ የተናገሩ ሌላ ግለሰብ ደግሞ "የሶማሌ ክልል ባንዲራ የማይገባ ቦታ ላይ አቁመው አንሱ ሲባል አናነሳም አሉ" በማለት የግጭቱን መነሻ ይናገራሉ።
ሐሙስ ቀን ላይ ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸው ለደኅንነታቸው ሲባል እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪ ደግሞ መጀመርያ ላይ ባንዲራው የተሰቀለበት አካባቢ የፌደራል መንግሥቱ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ማንሳታቸውን ያስታውሳሉ።
ነገር ግን ከሁለት ቀን በኋላ "ቦታ ቀይረው አንድ ኪሎ ሜትር የማይርቅ ስፍራ ላይ ተከሉ" በማለት የግጭቱን መነሻ አብራርተዋል።
በሞያሌ ከተማ ልዩ ስሙ 02 ቀበሌ በተባለ አካባቢ ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ ግጭቶች መቀጠላቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ከረቡዕ ዕለት ጀምሮ በከተማዋ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለመኖሩን ያስረዱት ነዋሪዎች ከሞያሌ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድም መዘጋቱን ይናገራሉ።
ቤቶች መቃጠላቸውን እንዲሁም ቀኑን ሙሉ ተኩስ እየተሰማ መሆኑን ተናግረዋል። ቢቢሲ ነዋሪዎቹን ባነጋገረበት ወቅት ከጀርባ የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር።
እሁድ ዕለት የ13 ዓመት ልጅ ከፀጥታ አካላት በተተኮሰ ጥይት መገደሏን የተናገሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የከተማው ነዋሪ፣ ሐሙስ ዕለትም "በሕንጻዎች ላይ ስናይፐር እና ዲሽቃ የደገኑ" የፀጥታ አባላት ስላሉ በመንገዱ ላይ ማንም አይንቀሳቀስም ሲሉ ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል።
ሐሙስ ዕለት ወደ ስድስት ሰው ሞቷል ያሉት ነዋሪው በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን ገልጸው የፀጥታ ኃይሎች ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዳቸውን ተናግረዋል።
በሞያሌ ከተማ የሚገኙት እና ቢቢሲ ያነጋገራቸው አብዱርሃማን በበኩላቸው "በሶማሌ በኩል በርካታ ቤቶች ወድመዋል። እስካሁን አራት ሰዎች ተገድለዋል፤ 11 ሰዎችም ቆስለዋል። የተጎዱት ወደ ሕክምና ተወስደዋል። የሞቱትም የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ተፈፅሟል" ብለዋል።
ቢቢሲ በግጭቱ ስለሞቱት ነዋሪዎች ቁጥር ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም። ከሶማሌ ክልል ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
ቢቢሲ ሐሙስ ምሽት ላይ ያነጋገራቸው የሞያሌ ከተማ ነዋሪ ከሌሊት ጀምሮ እየተተኮሰ መሆኑን ተናግረዋል።
"ዛሬ ሌሊት ነው የተጀመረው። እስካሁን እየተተኮሰ ነው። ቅድም አንድ መንገደኛ የ10 ዓመት ልጅ ገደሉ፤ እስካሁን ድረስ እየተታኮሱ ነው"
በከተማዋ የሚገኙ የንግድ ሱቆች መዘጋታቸውን ተናግረው "ሕዝቡ ቤቱን ዘግቶ ሸሽቷል" ብለዋል።
ኢትዮጵያን ከኬንያ ጋር በምታዋስንበት የንግድ መዳረሻዋ ሞያሌ ከተማ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በኢትዮጵያ እና በኬንያ ደንበር በምትገኘው ሞያሌ ከተማ በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ኬንያ መግባታቸውን የአገሪቱ ቀይ መስቀል እና ባለሥልጣናት መናገራቸው ተዘግቧል።
በከተማዋ ግጭት የተቀሰቀሰው ረቡዕ ዕለት ነው ያለው ሮይተርስ፣ በኢትዮጵያ ድንበር በኩል የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ ነዋሪዎች መናገራቸውን ገልጿል።
የኬንያ ቀይመስቀል ኮሚሽነር ስታሌይ ካማንዴ "በመቶዎች የሚቆጠሩ ከኢትዮጵያ የመጡ ሰዎች ተቀብለናል፤ በዋናነት ሕፃናት እና ሴቶች ናቸው" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ኮሚሽነሩ አክለውም "አብዛኛዎቹ በኬንያ በኩል ባለው የሞያሌ የተለያዩ መንደሮች ዘመዶቻቸው ጋር መጠለላቸው" ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋራቸው ነዋሪዎችም ግጭቱ ሐሙስ ዕለትም ቀጥሎ መዋሉን ተናግረው ነዋሪዎች ቤታቸውን ዘግተው ወደ ጫካ እና ወደ ኬንያ መሸሻቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ በፊትም በሞያሌ ከተማ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች መካከል ግጭት ሲከሰት እንደነበር የተናገሩ አንድ ነዋሪ ነዋሪው የአሁኑ እጅግ ከበድ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
"ዛሬ ግን ዲሽቃ፣ ሞርታር ምናምን ይኸው ሕዝቡ ከሌሊት ጀምሮ እየሸሸ ነው። ወደ ጫካ እና ድንበር አልፈው ወደ ኬንያ እየገቡ ነው። ምግብ የለም፤ ሕጻናት እና ሕዝቡ በረሃብ እየተሰቃዩ ነው። በጣም እየተቸገሩ ነው " ብለዋል።
የሰዎች እንቅስቃሴ አለመኖሩን እና የንግድ ሱቆች ዝግ መሆናቸውን እና ነዋሪዎችም ወደ በኬንያ በኩል ወዳለው የሞያሌ ከተማ መሸሻቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።
አዛውንት፣ ወጣቶች እና ሴቶች ወደ ኬንያ መሸሻቸውን "እኛም መሸሺያ አጥተን ተደብቀናል" ብለዋል።
የኬንያ ቀይ መስቀል ማኅበር በበኩሉ የግጭቱ ሰለባ የሆኑ ምን ያህል ሰዎች ናቸው የሚለውን እና ምን ያስፈልጋቸዋል የሚለውን ለማወቅ ሁኔታውን እያጠና መሆኑን ገልጿል።
ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ እየገቡ ያሉ "ተፈናቃዮችን ለማስተናገድ የመጠለያ ካምፕ አልተዘጋጀም፤ ነገር ግን በዚሁ ላይ በትኩረት እንሠራለን" ሲሉ ኢብራኤ ጆን የተባሉ የቀይ መስቀል ባለሥልጣን ተናግረዋል።