ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዓመት ከ600 ቶን በላይ የከበሩ ማዕድናትን የማጣራት አቅም ያለው ፋብሪካ ሥራ ማስጀመራቸውን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአዲስ አበባ፣ ቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ ሥራ ማስጀመራቸውን ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቅዳሜ መስከረም 30/2019 ዓ.ም. ሥራ ያስጀመሩት ይህ ፋብሪካ በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማጣራት አቅም እንዳለው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ መካከል በተደረገ ስምምነት በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባው ይህ ፋብሪካ ኢትዮጵያን "በውድ ማዕድናት ማጣሪያ ረገድ ቀጣናዊ ማዕከል ለማድረግ" እንደሚያስችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ዛሬ በይፋ ሥራ መጀመሩ የተገለጸው ይህ ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ ከአገር ውስጥ ባሻገር "ሰፊውን የምሥራቅ አፍሪካና አጠቃላይ የአፍሪካ ገበያን" የመሳብ አቅም እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ "በአፍሪካ ውስጥ ዓለም አቀፍ ተዓማኒነት ያለው የማጣራትና የፍተሻ አገልግሎት" እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን ይህም በቀጣናው የሚገኙ የማዕድን ኩባንያዎች ወርቃቸውን ከአህጉሪቱ ውጭ መላክ ሳያስፈልጋቸው "ለማጣራት፣ ለዕውቅና ማረጋገጫ ሰርተፊኬት፣ ለተጨማሪ እሴትና ለሽያጭ" ወደ ኢትዮጵያ እንዲያመጡ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ፋብሪካው በአገር ውስጥ ምርት ላይ እሴት ለመጨመር እንዲሁም የኢትዮጵያን የማዕድን ዘርፍ ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም በተጨማሪ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የፋብሪካው ሥራ መጀመር ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢን ለማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የጌጣጌጥ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ፣ እንዲሁም ተወዳዳሪ የሆነ የወርቅ እሴት ሰንሰለት ለመገንባት መንግሥት ጠንክሮ እየሠራ መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
ከማዕድን ማውጣት እስከ ኢንዱስትሪ ሽግግር ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ የላቀ እሴት እየፈጠርን እንገኛለን ሲሉም በይፋዊ የኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የወቅ ማጣሪያውን ባስመረቁበት ወቅት እንደተናገሩት ጥሬ ዕቃ ልኮ ያለቀላቸው ምርቶችን ማስገባትን ለማስቀረት መንግሥታቸው የያዘውን ዕቅድ ተከትሎ ፋብሪካው መገንባቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት 5.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ወርቅ ወደ ውጭ መላኳን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ይህ የማጣራት አቅም ከዚያ በፊት ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ቢያንስ 10 ቢሊዮን ሊሆን ይችላል" ሲሉ አስረድተዋል።
አንድ ኪሎ ወርቅ ከኢትዮጵያ ሲላክ "እንደ ወርቅ አይወሰድም [አይቆጠርም]" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መጀመርያ ማጣራት ተደርጎ ከዚያ ውስጥ "ቢበዛ 70 በመቶው ነው ወርቅ የሚባለው" ሲሉ አስረድተዋል።
30 በመቶ ያህሉ እንደ ቆሻሻ የሚደፋ ይሆናል ሲሉ ያብራሩት ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ "ነገር ግን ያ ቆሻሻ ተብሎ የሚደፋው ነገር ብር ሊሆን ይችላል። ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ሊሆኑ ይችላሉ" ሲሉ ያለውን ጥቅም አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ መጀመሩን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሚቀጥሉት አምሰት ዓመታት ኢትዮጵያ "ጥሬ እየላኩ የበሰለ ማስገባት የምታቋርጥበት ዘመን ይሆናል" ብለዋል።
ይህ የወጪ ንግዳችን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተጽዕኖ ይኖረዋል ካሉ በኋላም በወርቅ ላይም "ከእጥፍ ያላነሰ የዋጋ ጭማሪ" እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ወርቅ ተጣርቶ ሲላክ የተሻለ ዋጋ እንደሚኖረው በማስረዳትም ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌላ አፍሪካ አገራት የሚመረት ወርቅ ወደ አገር ውስጥ በመምጣት የማጣራት ሥራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ አቅም ያለው የወርቅ ማጣሪያ መገንባቷን ተናግረው ከብዙ የአፍሪካ አገራት ማዕድናት እየመጡ ሊጣራ ይቸላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የገነባችው የወርቅ ማጣሪያ "ከአፍሪካ አንደኛው ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በዓመት እስከ 80 ቢሊዮን ዶላር ወደ ውጪ መላክ የሚያስችል አቅም እንዳለው ተናግረዋል።
"ይህ ማጣሪያ ያለው አቅም እስከ 80 ቢሊዮን ዶላር በዓመት ኤክስፖርት ማድረግ የሚያስችል ነው።"
በርካታ የሠው ኃይል ወደ ተለያዩ አገራት ቀደም ብሎ ተልከው ሰልጥነው መምጣታቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአብዛኛው በኢትዮጵያውያን የሚተዳደር ፋብሪካም እንደሆነም አስረድተዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር በ49 በመቶ ሽርክና የሚሰራው ሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ ኩባንያ በዓለም ላይ ካሉ ተመሳሳይ ሥራ ከሚሰሩ ሁለት ሦስት ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ ነው ሲሉም አብራርተዋል።




































