ኢትዮጵያ በ2070 በክርስቲያኖች ብዛት ከዓለም 3ኛ፣ በሙስሊሞች ብዛት ደግሞ 7ኛ ደረጃን እንደምትይዝ ተተነበየ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2070 በክርስቲያኖች ብዛት ከዓለም በሦስተኛ ደረጃ እንደምትቀመጥ እንዲሁም ከፍተኛ ሙስሊም ሕዝብ ቁጥር ያለባቸውን የዓለም 10 አገራት ዝርዝር እንደምትቀላቀል ተተነበየ።

በ44 ዓመት ጊዜ ውስጥ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሕዝብ ብዛት ውስጥ የእስልማ እምነት ተከታዮች ድርሻ አሁን ካለበት 36 በመቶ ወደ 46 በመቶ ገደማ እንደሚጨምር ፒው የተሰኘው ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋም በዚህ ሳምንት ያወጣው ትንበያ አሳይቷል።

'ፒው ሪሰርች ሴንተር' ረቡዕ ኅዳር 9 ቀን 2019 ዓ.ም. ባወጣው ጥናት፣ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2035 እስልምና በአማኞች ብዛት የዓለም ቁጥር አንድ እምነት እንደሚሆን ትንበያውን አስቀምጧል። በትንበያው መሠረት፣ አሁን በአማኞች ብዛት ቀዳሚ የሆነው ክርስትና ቁጥሩ እያደገ የሚሄድ ቢሆንም የሙስሊሞች ብዛት በፍጥነት ያድጋል።

2035 ላይ የእስልምና አማኞች ብዛት 2.57 ቢሊዮን እንደሚሆን የተገመተ ሲሆን ክርስቲያኖች ደግሞ በ50 ሚሊዮን በማነስ 2.52 ቢሊዮን ይሆናል የሚል ትንበያ ተቀምጧል።

በአውሮፓውያኑ 2070 ግን በሁለቱ ግዙፍ ሃይማኖቶች መካከል ያለው ልዩነት ወደ 680 ሚሊዮን ከፍ ይላል። እስልምና ከ44 ዓመት በኋላ 3.64 ቢሊዮን አማኞችን በመያዝ ቀዳሚነቱን እያስጠበቀ እንደሚሄድ ትንበያው ያሳያል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመዘገበው ፈጣን የእስልምና አማኞች ብዛት እድገት ኢትዮጵያ ውስጥም እንደሚጠበቅ የ'ፒው ሪሰርች ሴንተር' ግኝት አመልክቷል። ከአውሮፓውያኑ 2020 እስከ 2070 ድረስ ያለውን ጊዜ በሚሸፍነው የተቋሙ ትንበያ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከ44 ዓመት በኋላ ከ280 ሚሊዮን በላይ ይሆናል።

በዚህ ጊዜ ውስጥም ኢትዮጵያ በአብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታዮች የሚኖሩባት አገር መሆኗ ይቀጥላል። እንዲያውም፣ በክርስቲያኖች ብዛት በ2020 የነበረችበትን ከዓለም ስምንተኛ ደረጃ ታሻሽላለች።

በ2070 ኢትዮጵያ ከ150 ሚሊዮን በላይ የክርስትና አማኞችን በመያዝ በክርስቲያኖች ብዛት ከዓለም በሦስተኛ ደረጃ እንደምትቀመጥ ተተንብይዋል።

አንደኛ ደረጃ ላይ እንደምትቀመጥ የምትገመተው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ስትሆን፣ አሜሪካ በሁለተኛነት ትከተላለች።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የክርስትና አማኞች ብዛት ከአጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ ያለው ድርሻ እየቀነሰ፣ የሙስሊሞች ድርሻ ደግሞ እየጨመረ ይሄዳል።

በትንበያው መሠረት ከስድስት ዓመት በፊት 61.6 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ቁጥር በ2070 ወደ 53.7 በመቶ ይቀንሳል። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከአጠቃላይ ሕዝቡ ውስጥ የሚኖራቸው ድርሻ ደግሞ ከ36.2 በመቶ ወደ 45.8 በመቶ ያድጋል።

ይህ አይነቱ የክርስቲያን አማኞች ድርሻ የመቀነስ አዝማሚያ ከ10 በላይ በሆኑ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ውስጥም እንደሚመዘገብ ትንበያው አሳይቷል።

በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት የሚመዘገበው የሙስሊሞች እድገት፣ ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2070 በእልምና እምነት ተከታዮች ብዛት የዓለም 10 አገራትን እንድትቀላቀል ያደርጋታል። በትንበያው መሠረት፣ ኢትዮጵያ 128.3 ሚሊዮን ሙስሊሞችን በመያዝ ከዓለም ሰባተኛዋ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚገኙባት አገር ትሆናለች።

ናይጄሪያ ሦስተኛ፣ ግብፅ ስድስተኛ እንዲሁም ሱዳን ስምንተኛ ደረጃን የሚይዙ የአፍሪካ አገራት እንደሚሆኑ ተገምቷል። በትንበያው መሠረት በ2070 ፓኪስታን ኢንዶኔዢያን በመብለጥ በሙስሊሞች ብዛት ቀዳሚዋ አገር ትሆናለች።

የፒው የምርምር ማዕከል ሪፖርት እንደሚያሳየው እስልምና በቀጣዮ ዘጠኝ ዓመት ውስጥ ትልቁ ሃይማኖት የሚሆነው እንዲሁም መሪነቱን እያሰፋ የሚሄደው፣ ከወሊድ ምጣኔ ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው።

"የወሊድ ምጣኔ ልዩነቶች በሕዝብ ብዛት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ይኖረዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙስሊሞች ከሌሎች ዋና ዋና የሃይማኖት ቡድኖች በበለጠ ብዙ ልጆችን የመውለድ አዝማሚያ አላቸው" ሲል አስፍሯል።

ከአውሮፓውያኑ 2020 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ የአንዲት ሙስሊም ሴት አማካይ የወሊድ ምጣኔ 3.1 ነበር። ሙስሊም ያልሆኑ ሴቶች የወሊድ ምጣኔ ደግሞ 2.0 እንደነበር ጥናቱ አመልክቷል።