በትዳር ውስጥ ለምን ሴቶች ላይ የሥራ ጫና ይበረታል? እንዴትስ ማቅለል ይቻላል?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ስቴሲ ማቲያስ የሦስት ልጆች እናት ናት። "አእምሮዬ ሁሌም እንደተወጠረ ነው። የምተኛው ማድረግ ያለብኝን ነገር ዝርዝር እያሰብኩ ነው" ትላለች።

ማቀድ፣ ማሳለጥ፣ ማስታወስ፣ ቤትን በአግባቡ መያዝ እና ሌሎችም ሴቶች ላይ የተጣሉ ጫናዎች 'ሜንታል ሎድ' ይባላሉ።

ልጆች መቼ የትምህርት ቤት ጉዞ እንደሚሄዱ ማስታወስ፣ የወላጆችን ዋትስአፕ ግሩፕ መከታተል፣ ልጆች መተኛታቸውን ማረጋገጥ፣ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ ማሰፋት፣ ቤት መቼ መጸዳት እንዳለበት መወሰን እና ሌሎችም ኃላፊነቶች ይጣሉባቸዋል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኃላፊነቶች ሴቶች ላይ የሚጣሉት ባልተመጣጠነ ሁኔታ ነው። ኃላፊነቶቹ ክንውኖችን የማስታወስ እና የማድረግ ብቻ አይደሉም። ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎችም ለሴቶች ይተዋሉ።

በተለያየ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ያለው የኑሮ ዘዬ የተለያየ ቢሆንም በአብዛኞቹ ግንኙነቶች ሴቶች ላይ ጫና ይበረታል።

የ37 ዓመቷ ስቴሲ "ሁሌም ማስታወስ ያለብኝ ነገር አለ። በተለይ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ሲመለሱ ኃላፊነቱ ይበዛል" ትላለች።

ቀኑን ሙሉ ያሉባት ኃላፊነቶች ዝርዝር አእምሯዋን ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠረዋል።

"የሆነ ሰው የማያግዘኝ ከሆነ ከቁጥጥር ውጪ ይሆናል" ትላለች።

በአሜሪካ፤ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ባት እና ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሜልቦርን የተሠራው 3,000 ወላጆች የተሳተፉበት ጥናት እንደሚያሳየው 71% የቤት ውስጥ ኃላፊነት እናቶች ላይ ይወድቃል።

አንሶላ መቀየር፣ ፎጣ ማጠብ፣ ፍሪጅ ውስጥ የተቀመጠ ምግብ ማለቁን ተከታትሎ መሸመትን የመሰሉ ኃላፊነቶች አሉባቸው።

አባቶች መኪና እንደማሳደስ ያሉ በተደጋጋሚ የማይደጉ ሥራዎችን ያከናውናሉ።

ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሜልቦርን የሚሠሩት ፕ/ር ሊያ ሩፓነር እንደሚሉት፤ ሴቶች ላይ ያለው አእምሯዊ ጫና ገደም አልባ እና የማይታይ ነው።

"ያልታጠበ እቃ ይዞ ሥራ አይገባም። አእምሯዊ ጫናው ግን ሁሉም ቦታ ይከተላቸዋል" ይላሉ።

ሴቶች ያለባቸውን የተለያየ ኃላፊነት እንዴት ማመጣጠን እንደሚችሉ እና እንዴት ከባሎቻቸው ጋር ስለ ጉዳዩ መወያየት እንዳለባቸው ምክር ለመጠየቅ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ፊታቸውን ያዞራሉ።

ትምህርት ቤቶች ለወላጆች በሚፈጥሯቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ በብዛት እናቶችን ያሳትፋሉ።

የ35 ዓመቷ እናት ሶፊያ እንደምትለው፤ ለልጆቿ የትምህርት ቤት ክፍያ ለመፈጸም ወይም ምሳ ለማዘዝ መተግበሪያ ትጠቀማለች። ባሏ ግን መተግበሪያውን በስልኩ አልጫነም።

ስላለባት የአእምሮ ጫና ለባሏ ለማስረዳት በተደጋጋሚ ሞክራለች። ግን አልተረዳትም። እንዲያውም ሥራዋ "በቀላሉ የሚያልቅ" እንደሆነ ይነግራታል።

"ሥራው ቀላል የሚሆነው ሲሠራ ነው። ሥራውን ማቀድ እና መተግበር አለብኝ። ሁሌም 10 እርምጃ መቅደም ያስፈልገኛል" ትላለች።

ሳም ቤሪ የትምህርት ቤት ኃላፊ እና የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪ ነው። የሁለት ልጆች አባት የሆነው ሳም ከባለቤቱ ስለ አእምሯዊ ጫና የሰማበትን ወቅት ያስታውሳል።

የመጀመሪያ ልጃቸው ሲወለድ ዳይፐር ይቀይር፣ ምግብም ያበስል ነበር። ምን ላግዝሽ? ብሎ ሚስቱን መጠየቁ የማሰብ ኃላፊነትን ሚስቱ ላይ የጫነ መሆኑን ይናገራል።

"አንድ ነገር አድርግ ብዬ መጠየቅ ካለብኝ አእምሯዊ ጫናውን ያከብድብኛል ትለኛለች" ሲል ያስረዳል።

ለወራት ያህል ከተወያዩ በኋላ ሳም ኃላፊነቱ ምን እንደሆነ ለመረዳት ችሏል።

አንድን ሥራ ማከናወን ብቻ ሳይሆን ሥራውን መከናወን እንዳለበት ማሰብም እንደሚጠበቅበት አውቋል።

ሳም የሚጠበቅበት እራት ማብሰል ብቻ ሳይሆን እቤት ባለው አስቤዛ ምን መሥራት እንዳለበት ማሰብም ጭምር ነው። የሚያስፈልገውን ግብዓት አውቆም መሸት አለበት።

የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ናታሻ ዋለስ እንደሚሉት ሴቶች ቤት ውስጥ ባለባቸው ኃላፊነት ብዛት ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ።

"አንድ ትልቅ ነገር ብቻ አይደለም የሚያስጨንቃቸው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ትንንሽ ነገሮች ያሳስቧቸዋል። አእምሯቸው እና አካላቸው መቼም ማረፍ አይችልም" ይላሉ።

ያለባቸው ጫና ከራሳቸው ጋር ከመዋሀዱ የተነሳ ሥራ የሚያከናውኑን ጫና ውስጥ መሆናቸውን ሳያስቡ ነው።

ይህም አእምሯቸው ላይ በሚያደርሰው ጉዳት እንቅልፍ ማጣት፣ ብስጩ መሆን እና ድካም ይገጥማቸዋል።

የልጆች አስተዳደግ ባለሙያ አኒታ ክሌር እንደሚሉት አእምሮ በሥራ ሲወጠር ከልክ ያለፈ ድካም (በርንአውት) ያስከትላል።

ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ወንዶች አነስተኛ የቤት ውስጥ ሥራ እንደሚያከናውኑ አንድ ጥናት ያሳያል። በተጨማሪም ያለባቸው አእምሯዊ ጫና ይቀንሳል።

ሴቶች ከፍተኛ ገቢ ሲያገኙ የቤት ውስጥ ኃላፊነታቸው ቢቀንስም አእምሯዊ ጫናው ባለበት ይቀጥላል።

ሴቶች ስለ ቤተሰብ ኃላፊነት ጋር በተያያዘ አለማሰብ የሚችሉበት ዕድል ውስን ነው።

በቤት ውስጥ ኃላፊነት ምክንያት ሥራቸውን ማቋረጥ ወይም የትርፍ ጊዜ ሥራ ብቻ ማከናወን ግዴታቸው ይሆናል። ሌላኛው አማራጭ ሥራ ትቶ የቤት እመቤት መሆን ነው።

አብዛኞቹ ሴቶች እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ እንደሚገደዱ ባለሙያዋ ይናገራሉ።

"የቤት ውስጥ ኃላፊነት ሲቀንስ የአእምሮ ጫና ይቀንሳል። ሥራ ላይ የማተኮር ተነሳሽነት እና አቅም ይጎለብታል" ይላሉ።

አብዛኞቹ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሴቶች በወንዶች እና ሴቶች መካከል ያለው ልዩነት ከወሊድ ፈቃድ እንደሚጀምር ያስረዳሉ።

አኒታ እንደሚሉት ሴቶች የሚሰጣቸው የወሊድ ፈቃድ ከወንዶች ይረዝማል። ይህም ቀዳሚ እንክብካቤ ሰጪ ወላጆች እነሱ መሆናቸውን በተዘዋዋሪ የሚወስን ይሆናል።

"ሁሉንም ነገር የምታውቀው፣ ሁሉንም ነገር የምታከናውነው ሴቷ ስትሆን በሁሉም ጉዳይ ኃላፊነት ይጣልባታል። ወደ ሥራ ብትመለስም ይሄ አይለወጥም" ይላሉ።

ዩናይትድ ኪንግደምን እንደ ምሳሌ ብንወስድ የሴቶች የወሊድ ፈቃድ 52 ሳምንት፣ የወንዶች 39 ሳምንታት ነው።

አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ተጨማሪ የወሊድ ፈቃድ ለአባቶች ይሰጣሉ።

ሆኖም ግን በወሊድ ፈቃድ ወቅት እናቶችም አባቶችም የሚያገኙት ገቢ ይቀንሳል።

መሥሪያ ቤቶች የወሊድ ፈቃድ ከመስጠት በሻገር በተለያየ መንገድ መደገፍ እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የሦስት ልጆች አባት የሆነው ዛክ ዋትሰን በአሜሪካ ጥንዶች እንዴት ኃላፊነትን መጋራት እንደሚችሉ ሥልጠና ይሰጣል።

አያቱ ፈጽሞ ምግብ አያበስሉም ነበር። አባቱ ደግሞ በጥቂቱም ቢሆን ያበስላሉ።

በመጀመሪያዎቹ አምስት የትዳር ዓመታት አብዛኛውን ጊዜ የምታበስለው ባለቤቱ ነበረች።

ስታበስል የሚያስፈልጋት ነገር እንዳለ ይጠይቃታል። ይህም የሚያሳድርባትን አእምሯዊ ጫና ያከብደዋል።

በሒደት ግን እራት ምን ማብሰል ይቻላል የሚለውን ማሰብ ጀመረ። አንድ እቃ የት እንዳለ ሚስቱን ከመጠየቁ በፊትም ይፈልጋል።

ሳም እንደሚለው አብዛኞቹ ወንዶች ጥሩ አባት እና ባል ቢሆኑም ያለውን የኃላፊነት ልዩነት አይገነዘቡም ወይም በአግባቡ አይገልጹትም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሴቶች ባሎቻቸው ኃላፊነትን ለመወጣት ተነሳሽነት እንዲያሳዩ ይፈልጋሉ።

ሳም በበኩሉ የሥራ ኃላፊነትን መከፋፈልን ይመክራል። ሁሉንም ነገር እኩል መካፈል የጥንዶቹን ፍላጎት ያማከለ መሆን እንዳለበትም ይገልጻል።

የ40 ዓመቷ የሁለት ልጆች እናት አፉዋ ዊልያምስ እንደምትለው የአእምሮ ጫና የሚበዛባቸው ሴቶች የትዳር አጋሮቻቸው ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸው ይሰማቸዋል።

ጫናን እንዴት ማቅለል ይቻላል?

  • በግልጽ መወያየት- ጥንዶች ስሜታቸውን በግልጽ መወያየት አለባቸው። አእምሯዊ ጫና ሲከሰትም መነጋገር ይጠበቅባቸዋል። ችግሩ በይፋ መገለጽ ያለበት በቁጣ ወይም በመሰላቸት ውስት ሳይሆን ጤናማ እና ገንቢ በሆነ ሁኔታ ነው።
  • የትኛውን ጫና ማቃለል እንደሚቻል መለየት- በዚህ ጉዳይ ጥናት የሠሩት አና ካታላኖ ዊክስ እንደሚሉት የትኛውን ጫና ማቃለል እንደሚቻል መለየት ያስፈልጋል።
  • ከትዳር አጋር ጋር መነጋገር- በሳምንት ወይም በወር ከትዳር አጋር ጋር እየተወያዩ መለወጥ ያለባቸውን መለየት ያስፍላል። የጋራ የቀን መቁጠሪያ በማዘጋጀት ኃላፊነትን መጋራት አንደኛው መንገድ ነው።
  • ኃላፊነት መውሰድ- አንድ ሰው ብቻ ጫናውን እንዳይሸከም በራስ ተነሳሽነት ኃላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግም አስታዋሽ አያስፈልግም።