ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የባሕር ላይ ወንበዴዎች በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ የነዳጅ መርከብ አገቱ
የባሕር ላይ ወንበዴዎች በሶማሊያ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ ሲጓዝ የነበረ የነዳጅ ጫኝ መርከብን እና 17 ሠራተኞቹን አግተው መውሰዳቸውን በርካታ የደህንነት ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናገሩ።
ኃላፊዎቹ እንዳሉት ኦነር 25 የተሰኘችው መርከብ ረቡዕ ዕለት በባሕር ዳርቻው አካባቢ በስድስት ታጣቂዎች በቁጥጥር ሥር ውላለች።
በአንድ ወቅት አደገኛ በሆነ እገታ ይታወቅ በነበረው የሕንድ ውቅያኖስ ክፍል የባሕር ላይ ውንብድና ጠፍቶ የነበረ ቢሆንም ከሦስት ዓመት በፊት ግን ዳግም ብቅ ብሏል።
ከዚያ በኋላም የዓሳ አጥማጅ ወይም ኮንቴይነር ጫኝ መርከቦች ዒላማ ሲደረጉ ቆይተዋል።
ወደ ሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ የሚያመራ የነዳጅ ጫኝ መርከብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ከኢራን ጦርነት በኋላ የነዳጅ ዋጋ በሦስት እጥፍ በጨመረባት ከተማ ጭንቀትን ሊጨምር ይችላል።
የሶማሊያ ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደር የሆነችው ፑንትላንድ የደኅንነት ባለሥልጣናት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የታገተችው መርከብ 18,500 በርሜል ነዳጅ ጭና ነበር።
መርከቧ በርበራ ወደብን ለቅቃ የሄደችው የኢራን ጦርነት ከመጀመሩ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ፣ እአአ የካቲት 20 ሲሆን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ የደረሰችው ደግሞ ጦርነቱ በተጀመረባቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ መሆኑን የሺፕአትላስ ድረ ገጽ መረጃ ያሳያል።
ከዚያም በሆርሙዝ ወሽመጥ መግቢያ አቅራቢያ ስትሽከረከር ቆይታ እአአ ሚያዚያ 2 ወደ ሞቃዲሾ መምጣቷን ድረገጹ ያሳያል።
መርከቧ በባሕር ላይ ወንበዴዎች ቁጥጥር ስር ስትውል 10 ፓኪስታናውያን እና አራት ኢንዶኔዢያውያን እንዲሁም አንድ ሕንዳዊ፣ አንድ ስሪላንካዊ፣ እና አንድ የምያንማር ዜጋን ይዛ ነበር።
መርከቧ በሻፉን እና ባንደር ቤይላ የዓሣ ማጥመጃ ከተሞች መካከል በሚገኘው የሶማሊያ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ እንድትቆም ተደርጎ 17 የመርከቧ ሠራተኞች በአጋቾቹ መወሰዳቸውን የደኅንነት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ምንጮች እንደገለጹት አምስት ተጨማሪ የታጠቁ ሰዎች ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኦነር 25 አጋቾችን ተቀላቅለዋል።
ባለሥልጣናቱ አጋቾቹ ከባንደር ቤይላ አቅራቢያ ካለ ሩቅ ስፍራ መምጣታቸውን ይናገራሉ። የነዳጅ ጫኝ መርከቡን እንዴት መቆጣጠር እንደቻሉ ግልፅ አይደለም።
የሶማሊያ ባለሥልጣናትም ሆኑ በውቅያኖሱ ላይ የሚካሄደውን የባሕር ላይ ውንብድናን ለመከላከል ኃላፊነቱን የተረከበው የአውሮፓ የባሕር ኃይል ስለ እገታው መግለጫ አልሰጡም።