ቀጥታ, ትራምፕ ጦራቸው በወሽመጡ ላይ ፈንጂ የሚያጠምዱ ጀልባዎች ላይ እንዲተኩስ ትዕዛዝ ሰጡ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ ፈንጂ የሚያስቀምጥ ማንኛውንም ጀልባ “ተኩሳችሁ ግደሉ” ሲሉ ለባሕር ኃይላቸው ትዕዛዝ ሰጡ። “ምንም ማመንታት አያስፈልግም” ያሉት ትራምፕ የአሜሪካ ፈንጂ “አስወጋጆች” ወሽመጡን “አሁን” እያጠሩ ነው ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ስለሰነዘሩት ዛቻ ሲጠየቁ “ምንም ነገር ብል፤ ጥሩ እየሰራ ይመስለኛል” አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ቢቢሲ በኢራን ላይ ስለሰነዘሩት ዛቻ ሲጠይቃቸው “ምንም ቢሆን የማደርገው፣ በጣም ጥሩ እየሰራ ይመስለኛል” ሲሉ መለሱ።

    የቢቢሲ የሰሜን አሜሪካ ኤዲተር ሳራ ስሚዝ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ባደረገችው አጭር የስልክ ቃለ መጠይቅ በዚህ ወር መጀመርያ ላይ የኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያን በመቃወም በሰጡት ማስጠንቀቂያ “ዛሬ ምሽት ሙሉ ስልጣኔ ይጠፋል” ማለታቸውን አስታውሳለች።

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ በምላሻቸው “ሌላኛው ወገን ከስምምነት ለመድረስ እየተሟሟተ ነው” ካሉ በኋላ “ስለዚህ ምንም ነገር ብል፣ ወይም ምንም ነገር ባደርግ ጥሩ እየሰራ ይመስለኛል። በጣም አመሰግናለሁ” ብለዋል።

    ትራምፕ የሰሜን ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ)ን በሚመለከት ከኢራን ጋር በሚያደርጉት ጦርነት “ፈጽሞ አልፈልጋቸውም ነበር” ካሉ በኋላ “ነገር ግን እዚያ መገኘት ነበረባቸው” ብለዋል።

    ቢቢሲ ኔቶ ጦርነቱን እንዲቀላቀል ለምን እንደፈለጉ ሲጠይቃቸው፣ “ምክንያቱም ይሳተፉ እንደሆን እና እንዳልሆነ ማየት እፈልጋለሁ” ብለዋል።

    አሜሪካ ምንጊዜም ከዩኬ እና ኔቶ ጎን መሆኗን የጠቀሱት ትራምፕ፣ ዩኬ “ትንሽ እንኳ ጥረት፤ ቢያንስ ጥሩ ቃል” አለመሞከሯን በመጥቀስ ተችተዋል።

    አክለውም "ከዩናይትድ ኪንግደም የመጡ ብዙ ሰዎች" አገራቸው በጦርነቱ ውስጥ ላለመሳተፍ መወሰኗ "በሚገርም ሁኔታ መጥፎ ውሳኔ" እንደሆነ መናገራቸውን ጠቅሰዋል።

    ዩናይትድ ኪንግደም አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ለምታካሄደው ጦርነት ለ"መከላከያ" የአየር ጥቃቶች ብቻ እንድትጠቀም ፈቅዳለች።

    ቀደም ሲል ትራምፕ ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ጋር ያላቸው ግንኙነት በተመለከተ ሲናገሩ "የሰሜን ባህርን ከከፈተ" እና "የስደት ፖሊሲያቸው ጠንካራ ከሆነ" "ያገግማል" ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

    ነገር ግን "ይህንን ካላደረገ፤ ዕድል ያለው አይመስለኝም" ብለዋል።

  2. ሊባኖስ፣ ከዋሺንግተኑ ድርድር በፊት አሜሪካ “እስራኤል ላይ ያላትን ተጽዕኖ” እንድትጠቀም ትፈልጋለች

    የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ መንግሥታቸው አሜሪካ ከዋሺንግተኑ ንግግር በፊት “እስራኤል ላይ ያላትን ተጽዕኖ” እንድትጠቀም እንደሚፈልግ ለዋሺንግተን ፖስት ተናገሩ።

    ናዋፍ ሳላም ለጋዜጣው “አሜሪካ ወደጠራችው ወደዚህ ድርድር እየገባን ያለነው በእስራኤል ላይ ተጽዕኖ ማድረግ የምትችል መሆኑን በማመን ነው” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሚናቸው ወሳኝ ነበር። ያላቸውን ተጽዕኖ እስራኤል ላይ መጠቀማቸውን ይቀጥላሉ ብለን እናምናለን” ብለዋል።

    የእስራኤል ጦር በደቡብ ሊባኖስ የሚያካሄደውን ዘመቻ እንደቀጠለ ሲሆን ሳላም አገራቸው እስራኤል ግዛታቸውን ሙሉ በሙሉ ለቅቃ እንድትወጣ እንደሚፈልጉ ተናግረው “የደህንነት ቀጣና ከሚባለው ጋር መኖር አንችልም” ብለዋል።

    እስራኤል ሄዝቦላህ ትጥቁን እንዲፈታ እንድምትፈልግ ተጠይቀው “በአንድ ሌሊት የሚከናወን ነገር አይደለም። ነገር ግን ዋናው ነገር ምንድን ነው ቁርጠኛ መሆናችንን አሳይተናል” ብለዋል።

  3. ትራምፕ የባሕር ኃይሉ ፈንጂ የሚያሰቀምጡ ጀልባዎች ላይ “እንዲተኩስ እና እንዲገድል” አዘዙ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ ፈንጂ የሚያስቀምጥ ማንኛውንም ጀልባ “ተኩሳችሁ ግደሉ” ሲሉ ለባሕር ኃይላቸው ትዕዛዝ ሰጡ።

    “የአሜሪካ ባሕር ኃይል ማንኛውም ጀልባ ላይ እንዲተኩስ እና እንዲገድል አዝዣለሁ፤ ትናንሽ ጀልባዎች ምንም እንኳን ... በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ፈንጂዎችን እያስቀመጡ ይሆናል" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ልጥፋቸው ላይ አስታውቀዋል።

    “ምንም ማመንታት አያስፈልግም” ያሉት ትራምፕ የአሜሪካ ፈንጂ “አስወጋጆች” ወሽመጡን “አሁን” እያጠሩ ነው ብለዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ የባሕር ኃይላቸውን ፈንጂ የሚያጠምድ ማንኛውም የኢራን ጀልባ ላይ “ተኩሱና ግደሉ” ካሉ በኋላ፣ ኢራናውያን “መሪያቸው ማን እንደሆነ ለማወቅ ተቸግረዋል” ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፈዋል።

    ትራምፕ በአገሪቱ ውስጥ “ወግ አጥባቂ” እና “ለዘብተኛ” በሆኑ ባለሥልጣናት መካከል ፍትጊያ መኖሩን ጨምረው ተናግረዋል።

    አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን ሙሉ በሙሉ “እየተቆጣጠረች ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ ካለ አሜሪካ ፈቃድ አንድም መርከብ እንደማይገባ እና እንደማይወጣ አስታውቀዋል።

  4. ሕይወት “ጦርነትም ሰላምም በሌለባት” ኢራን

    አሜሪካ ከቴህራን ጋር የጀመረችውን የተኩስ አቁም ካራዘመች በኋላ በኢራን መደበኛ ሕይወት ቀጥሏል። የኢራን ሪፐብሊክ መንግሥት እስካሁን ድረስ በሁለተኛው ዙር የተኩስ አቁም ስለመሳተፉ በይፋ ያለው ነገር የለም።

    የተባበሩት መንግሥታት የልማት ኃላፊ አሌክሳንደር ዴ ክሮ ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኢራን ጦርነት በነዳጅ እና በማዳበሪያ አቅርቦት መስተጓጎል ወደ ድህነት ይገፋሉ ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    አብዛኛው የዓለም ማዳበሪያ የሚመረተው በመካከለኛው ምሥራቅ ሲሆን አንድ ሦስተኛው የዓለም አቅርቦቶች በሆርሙዝ ባህር ወሽመጥ በኩል ያልፋሉ። ኢራን እና ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ወሽመጡን ለመቆጣጠር እየተፋለሙ ነው።

    ኢራናውያን የምግብ እና የመሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ማሻቀቡን ይናገራሉ። ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ ኢንተርኔት እንደተቋረጠ ነው።

  5. የቀድሞው የአሜሪካ ዲፕሎማት ኢራን በጦርነት ውስጥ 'የመቆየት አቅም' አላት አሉ

    የቀድሞው የአሜሪካ ዲፕሎማት ዴቪድ ሳተርፊልድ፣ ኢራን የምጣኔ ኃብት ጫና ከአሜሪካ እና ዶናልድ ትራምፕ የበለጠ የመቋቋም አቅም አላት አሉ።

    ዲፕሎማቱ አሜሪካ ከኢራን ጋር የምታደርገው ጦርነት ውጤት የሚወሰነው “ማን ረዥም ጊዜ [ጦርነት ውስጥ] ይቆያል” በሚለው ነው ብለዋል።

    “በእኔ እምነት ኢራን ረዥም ጊዜ [ጦርነት ውስጥ] መቆየት ትችላለች” ሲሉ ለቱዴይ ፕሮግራም ተናግረዋል።

    ዲፕሎማቱ አሜሪካ ሁለቱም ወገኖች ግጭቱ እንዲባባስ በሚያደርጉበት “ቅርቃር” ውስጥ ልትገባ ትችላለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ሳተርፊልድ አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃዎችን የምታጠናክር ከሆነ ኢራን በፍጥነት በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ አገራት ላይ የበለጠ ጉዳት ታደርሳለች ብለዋል።

  6. የአሜሪካ ጦር በሕንድ ውቅያኖስ የምትቀዝፍ ማዕቀብ የተጣለባት የኢራን መርከብን መያዙን ገለጸ

    የአሜሪካ ጦር ከኢራን ነዳጅ የጫነች ማዕቀብ የተጣለባት መርከብን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

    የመከላከያ ቢሮ በኤክስ ገጹ ላይ “የአሜሪካ ጦር ማዕቀብ በተጣለባት አገር አልባ መርከብ፣ ኤም/ቲ ማጅስቲክ ኤክስ፣ በሕንድ ውቅያኖስ በኩል ከኢራን ነዳጅ በማጓጓዝ ላይ ሳለች አስቁሞ ፍተሻ አካሄዷል" ብሏል።

    ቢሮው ለኢራን “የቁስ ድጋፍ ያደርጋሉ” ተብለው የሚጠረጠሩ መርከቦችን አስቁሞ መፈተሹን አንደሚቀጥል አስጠንቅቋል።

    የባሕር ትራንስፖርት ክልከላ ማለት ሕግ ተላልፏል ወይም ስጋት ነው ተብሎ የተጠረጠረ መርከብን መፈተሽ ወይም በቁጥጥር ስር ማዋልን ያካትታል።

    አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ እገዳ ከጣለች ጀምሮ በርካታ መርከቦች እንዲመለሱ ወይንም እንዲቆሙ አድርጋለች።

    መርከቧ ከኢራን ርቃ በሕንድ ውቅያኖስ ላይ እየቀዘፈች የነበረ እንደሆነ ተገልጿል።

  7. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ከሚያልፉ መርከቦች ክፍያ መሰሰብብ መጀመሯን አስታወቀች

    ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ከሚተላለፉ መርከቦች የተሰበሰበ የመጀመሪያው የገንዘብ ክፍያ ወደ አገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ አካውንት መግባቱን የኢራን ፓርላማ ምክትል አፈ ጉባኤ አስታወቁ።

    ታስኒም የተባለው የኢራን ዜና ወኪል ምክትል አፈ ጉባኤው ሃሚድሬዛ ሐጂ ባቤ ገንዘቡ ገቢ መደረጉን እንጂ ከማን እና እንዴት እንደተሰበሰበ ዝርዝር ማብረሪያ እንዳልሰጡ ዘግቧል።

    ክፍያው መሰብሰቡን በተመለከተ ከባለሥልጣኑ ባሻገር ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገኖች ማረጋገጥ አልቻለም።

    ከአሜሪካ ጋር የተኩስ አቁም ከመደረጉ በፊት ኢራን በወሳኙ ሆርሙዝ በኩል “ወዳጅ” አገራት ብቻ እንዲተላለፉ የፈቀደች ሲሆን፣ በወሳኙ የባሕር ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦችም እንዲከፍሉ እንደምታደርግ ስትገልጽ ነበር።

    ይህ የኢራን ውሳኔ በአገሪቱ ፓርላማ ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም የሚከፈለው የገንዘብ መጠን ግን ግልጽ ሳይሆን ቆይቷል።

    ባለፈው መጋቢት ኢራን አስከ ሁለት ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እያስከፈለች ነው በሚል ክስ የቀረበባት ሲሆን በሕንድ የሚገኘው ኤምባሲዋ ግን ዜናውን አስተባብሏል።

    ሌላ የኢራን ፓርላማ አባል “ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ከሚተለላፉ መርከቦች ገንዘብ መሰብሰቧን ከአስተማማኝ ምንጮች ሰምቻለሁ” ሲሉ ለታስኒም ዜና ወኪል አረጋግጠዋል።

    ጨምረውም “ከእያንዳዱ መርከብ የሚሰበሰበው የገንዘብ መጠን መርከቦቹ የያዙት ጭነት ዓይነት እና መጠንን መሠረት ደያረገ ሲሆን፣ ክፍያውም በኢራን የሚወሰን ነው” በማለት አገራቸው ያወጣችው መመሪያ ተግባራዊ እየሆነ መሆነን አመልክተዋል።

    ይህ ኢራን በወሽመጡ በኩል በሚያልፉ መርከቦች ላይ ክፍያ እንደምትሰበስብ ካስታወቀች በኋላ አሜሪካ ተቃወሞ ከማሰማቷ ባሻገር ፕሬዝዳንት ትራምፕ መርከቦች ለኢራን ምንም ዓይነት ክፍያ እንዳይፈጽሙ አስጠንቅቀው ነበረ።

  8. ኢራን፤ አሜሪካ እና እስራኤል በባህረ ሰላጤው እና በወሽመጡ ላይ 'የጸጥታ መደፍረስ ምንጭ' ናቸው አለች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአሜሪካ እና የእስራኤል "ጥቃት" በባህረ ሰላጤ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ "የጸጥታ ችግር ምንጭ" ነው አሉ።

    የኢራን መንግሥት በኤክስ ገፁ ላይ በተከታታይ ባጋራቸው ልጥፎች አባስ አራግቺ በቴህራን ከደቡብ ኮሪያ ልዩ መልዕክተኛ ጋር እንደተገናኙ ገልጿል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አገራት "እነዚህን ጥቃቶች በማውገዝ ግልፅ እና ጠንካራ አቋም እንዲወስዱ" ማሳሰባቸውን ጠቅሷል።

    ኢራን ደኅንነቷን እና ጥቅሟን ለመከላከል በዓለም አቀፍ ሕግ እርምጃዎችን ወስዳለች ማለታቸውም በልጥፉ ተካትቷል።

    አራግቺ አክለውም ለሚደርሰው ሁሉ “ኃላፊነቱ የሚወስደው ጥቃት ፈጻሚው ነው” ብለዋል።

    ኢራን በወሽመጡ ሁለት መርከቦችን "መያዟን" እና ሦስተኛ የጭነት መርከብ ላይም ጥቃት መሰንዘሯ ተገልጿል።

  9. የሰላም ስምምነት ሳይፈጸም የንግድ መርከቦች ጉዞ እንደማይጀምሩ የነዳጅ ጫኝ ኩባንያ ኃላፊ ተናገሩ

    የሲውዲን ነዳጅ አጓጓዥ ኩባንያ የሆነው ‘ስቴና በልክ’ ዋና ስራ አስፈጻሚ በአሁኑ ሰዓት የኩባንያው መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉበት “ምንም ዕድል” እንደሌለ ተናገሩ።

    የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤሪክ ሃኔል ከቢቢሲ ሬዲዮ 4 'ቱዴይ' ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ "ይህንን አይነት እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት” በውሃ መስመሩ በኩል በሰላም ለማለፍ “ከሁለቱም፤ ከኢራን እና አሜሪካ የደኅንነት ዋስትና ያስፈልገናል" ብለዋል።

    የንግድ መርከቦች በድጋሚ ጉዞ እንዲጀምሩ የሚያስችለው አስፈላጊ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችለው የሰላም ስምምነት ሲፈረም ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

    "ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣ እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ ባለው ጊዜ በአንድ ሳምንት ገደማ ውስጥ እንድናልፍ የሚያደርግ አንድ ነገር ይፈጠራል የሚል ተስፋ ነበረን" ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ አሁን ግን ሁኔታው "የተቆለፈ" ሆኗል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

  10. ኢራንን እየመራ ያለው ማን ነው?

    በኢራን በሚከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ የመጨረሻውን ውሳኔ እንደሚያሳልፉ ይታወቃል።

    ነገር ግን በመጋቢት ወር ከተሾሙ ወዲህ በፎቶም ሆነ በቪዲዮ ለሕዝብ ታይተው አያውቁም። የኢራን መንግሥት ተደራዳሪዎች እየሠሩ ያሉት በኻሜኒ “ትዕዛዝ” መሠረት ነው።

    ጠቅላይ መሪው በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ላይ የሚደረጉ ድርድሮችን በግልጽ ባያነሱም አሜሪካን ግን ተችተዋል።

    የኢራን ተደራዳሪዎች የሆኑት የፓርላማ አፈ ጉባዔው ሞሐማድ ባጋር ጋሊባፍ እና እንደ አባስ አራጋቺ ያሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድምጻቸው ጎልቶ እየተሰማ ነው።

    ጋሊባፍ ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ጥብቅ ትስስር አላቸው።

    የአብዮታዊ ዘቡ በተለይ በጦርነት ወቅት ከመደበኛው መከላከያ ከፍ ያለ ተጽዕኖ ነው ያለው።

    አብዮታዊ ዘቡ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮቹን ቢያጣም ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ትይዩ እየሰራ ነው።

    አገሪቱን በሚመለከቱ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግለጫዎችን የሚያወጣ ቢሆንም ምን ያህል አቅም እንዳለው ግን ግልጽ አይደለም።

  11. ትራምፕ ጦርነቱን ለመቋጨት "እንደማይጣደፉ" ተናገሩ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገውን የጦርነት ለመቋጨት “እየተጣደፉ አለመሆኑን” ለፎክስ ኒውስ ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንቴ ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር ባደረጉት የስልክ ቃለ መጠይቅ የኢራን ጋር የተደረሰውን እና ረቡዕ ዕለት የተጠናቀቀውን ተኩስ አቁም ያራዘሙት “የጊዜ ጫና” ኖሮባቸው እንዳልሆነ ገልጸዋል።

    “ጥሩ ስምምነት” ላይ እንዲደረስ እንደሚፈልጉ የተናገሩት ትራምፕ፤ ጦርነቱን ለመቋጨት “እንደማይጣደፉ” አስረድተዋል።

    የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር “መቀጠሉን” እና ፕሬዝዳንቱ “ቀይ መስመሮቻቸውን በእጅጉ ግልጽ” ማድረጋቸውን ገልጸው ነበር። ከትራምፕ ፍላጎቶች አንዱ ኢራን ያበለጸገችውን የዩራኒየም ክምችት ለአሜሪካ አሳልፋ መስጠት አለባት የሚል ነው።

    አሜሪካ ስለ ድርድሩ “ከኢራን አገዛዝ ምላሽ ለማግኘት እየጠበቀች” መሆኑን የተናገሩት ቃል አቀባይዋ፤ “እስካሁን ወጥ የሆነ መልዕክት መላክ አልቻሉም፤ ለዚህም ነው ፕሬዝዳንቱ የተኩስ አቁሙን ለማራዘም የወሰኑት” ብለዋል።

  12. እስራኤል ጋዜጠኛን ዒላማ ያደረገ የአየር ጥቃት ፈጽማለች ስትል ሊባኖስ ከሰሰች

    የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ረቡዕ ዕለት እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ድብደባ አንዲት ጋዜጠኛ ገድላ ሌላ ሰው በማቁሰል የጦር ወንጀል ፈጽማለች ሲሉ ከሰሱ።

    ግድያው የተፈጸመው እስራኤል እና ሊባኖስ ዛሬ በዋሽንግተን ሁለተኛ ዙር ውይይታቸውን ለማድረግ ዝግጅት እያደረጉ ባሉበት ጊዜ ነው።

    የሊባኖስ ባለሥልጣናት ጋዜጠኛ አማል ካሊልን እና ዘይነብ ፋራጅ የመጀመርያው ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ በአንድ ቤት ውስጥ ተጠልለው ባሉበት ወቅት ሆነ ተብሎ ዒላማ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

    እስራኤል አስቀድማ በፈጸመችው ጥቃት አንድ ተሽከርካሪ የመታች ሲሆን በዚህም ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።

    ባለሥልጣናቱ የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት ታይሪ መንደር ውስጥ ጋዜጠኞችን ለማትረፍ እየሄደ የነበረ አምቡላንስ ሆነ ተብሎ ዒላማ መደረጉን ጨምረው ተናግረዋል።

    የ43 ዓመቷ ካሊል በሊባኖስ ለሚታተም አል-አክባር ለሚባል ጋዜጣ ትሰራነበር። በመኪና ውስጥ የነበሩት እና በጥቃቱ የተገደሉት ሁለት ሰዎች ስም አልተገለጸም።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊቱ የሕይወት አድን ቡድኖች ወደ አካባቢው እንዳይደርሱ ከልክሏል መባሉን አስተባብሎ ጋዜጠኞችን ዒላማ እንዳላደረገ ተናግሯል።

  13. የቱርክ ፕሬዚዳንት የኢራን ጦርነት “አውሮፓን ማዳከም” ጀምሯል አሉ

    የቱርክ መሪ ረሲብ ታይብ ኤርዶጋን ከጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዋልተር ስቴህንሚየር ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ወቅት የኢራን ጦርነት “አውሮፓን ማዳከም” ጀምሯል አሉ።

    የቱርክ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባጋራው ጽሑፍ ሁለቱ መሪዎች በስልክ የተወያዩት ረቡዕ ዕለት መሆኑን አስታውቋል።

    ፕሬዚዳንቶቹ በውይይታቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት፣ በኢራን እና የዩክሬን እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶችን አንስተው ተወያይተዋል።

    ጽህፈት ቤቱ በልጥፉ “ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን በቀጣናችን እየተካሄደው ያለው ጦርነት አውሮፓን ማዳከም መጀመሩን አንስተዋል፤ እንዲሁም ሰላም ተኮር በሆነ አቀራረብ የሚቀረፍ ካልሆነ በጦርነቱ ወቅት የሚደርሰው ውድመት እጅግ የባሰ ይሆናል” ሲል የፕሬዝዳንቱን ንግግር ጠቅሷል።

  14. ዋይት ሐውስ ኢራን በየቀኑ 500 ሚሊዮን ዶላር እያጣች ነው አለ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ያራዘሙት በጦርነቱ የተጎዳው የኢራን አመራር በመፍረክረኩ እና ግጭቱን ለማስቆም የሚያስችል ምክረ ሃሳብ ለማቅረብ ጊዜ ስለሚያስፈልገው መሆኑን ተናገሩ።

    በተጨማሪም አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡ ሆነ የሚወጡ መርከቦች ላይ የጣለችው ክልከላ አሁንም ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።

    ይህ እርምጃ ኢራን ላይ ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ለመፍጠር ያሰበ ሲሆን ቴህራን በበኩሏ እንደ ጦርነት እርምጃ ቆጥራዋለች።

    የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ካሮሊን ሌቪት የአሜሪካ ዕቅድ እየሰራ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    "በዚህ እገዳ ኢኮኖሚያቸውን ሙሉ በሙሉ አንቀን ይዘነዋል። በቀን 500 ሚሊዮን ዶላር እያጡ ነው። የኻርግ ደሴት ሙሉ በሙሉ ሞልቷል። የነዳጅ ዘይት ማስገባትም ሆነ ማሰወጣት አይችሉም" ብለዋል።

    "ፕሬዝዳንት ትራምፕ በእነሱ ላይ ባደረሱት በዚህ የኢኮኖሚ ጫና ምክንያት ለሠራተኞቻቸው እንኳን ደመወዝ መክፈል አይችሉም" ሲሉም ገልጸዋል።

    የተራዘመው የተኩስ አቁም ስምምነት የሚያበቃበት ቀን ባይቀመጥም፣ ኢራን የሆርሙዝን የባህር ወሽመጥ ዳግም እንደማትከፍት በመግለጿ ሁለቱ ወገኖች ተፋጥጠዋል።

    ዋይት ሐውስ ትራምፕ በሁኔታው ደስተኛ መሆናቸውን ሲገልጽ አሜሪካ አሁንም ወሽመጡም ሆነ የኢራን ጉዳይ በቁጥጥሯ ሥር እንደሆነ ገልጸዋል።

  15. አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ካራዘመች በኋላ ኢራን ለሰላም ድርድር ክፍት መሆኗን ገለጸች

    ፓኪስታን በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ለሚደረገው ሁለተኛ ዙር የሰላም ድርድር ዝግጅቷን ቀጥላለች።

    ነገር ግን ከአሜሪካ ወይም ከኢራን የተውጣጡ ልዑካን ቡድን ይሳተፉ እንደሆን እስካሁን ማረጋገጥ አልተቻለም።

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ቴህራን አሁንም ለውይይት ክፍት እንደሆነች ቢናገሩም፣ የአሜሪካ "ስምምነቶችን መጣስ፣ እገዳ እና ዛቻዎች ለእውነተኛ ድርድር ዋና ዋና እንቅፋቶች ናቸው" ብለዋል።

    ዓለም "ማለቂያ የሌለውን ግብዝነት የተሞላበት ንግግር እያየ" ነው ሲሉም አክለዋል።

    የአሜሪካን ልዑክ እንደሚመሩ የሚጠበቁት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ አሁንም በአሜሪካ ይገኛሉ።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ሊጠናቀቅ የነበረውን የተኩስ አቁም ስምምነት አራዝመዋል።

    ከኢራን ጋር እያደረጉት ያለው ጦርነት መቼ እንደሚቆም “ የጊዜ ገደብ አልተቀመጠም" ሲሉ አክለዋል።

    የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮላይን ሌቪት እንደተናገሩት የተራዘመው ተኩስ አቁም የሚያበቃበት የጊዜ ገደብ የለውም።

    በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ዙሪያ ውጥረቱ ቀጥሏል። የኢራን ዋነኛ ተደራዳሪ አሜሪካ እና እስራኤል "የተኩስ አቁም ስምምነቱን በግልጽ በመጣሳቸው" ውሳኙ የባሕር መተላለፊያ ሊከፈት "አይቻልም" ብለዋል።

  16. ትራምፕ ከኢራን ጋር በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ሁለተኛው ዙር ድርድር ሊደረግ እንደሚችል ተናገሩ

    ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ሁለተኛ ዙር የሰላም ድርድር አርብ ዕለት “ሊጀመር ይችላል" ማለታቸውን ኒውዮርክ ፖስት ዘገበ።

    ጋዜጣው የፓኪስታን ባለሥልጣናትን ጠቅሶ "ከ36 እስከ 72 ሰዓታት" ባሉት ጊዜያት ውስጥ ውይይቱ ሊጀመር እንደሚችል ዘግቧል።

    የፓኪስታን ባለሥልጣናት ያሉትን በሚመለከት የተጠየቁት ትራምፕ በጽሑፍ መልዕክት "ሊሆን ይችላል!" በማለት መልሰዋል።

    ትራምፕ ረቡዕ ዕለት የሚያበቃውን የሁለቱን አገራት የተኩስ አቁም በትናንትናው ዕለት ሲያራዝሙ የኢራን አገዛዝ ጦርነቱን ለማቆም የሚያስችል "የተቀናጀ ሀሳብ" ለማምጣት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፍለገው ተናግረው ነበር።

  17. ኢራን ምን ያህል የዩራኒየም ክምችት አላት?

    አሁኑ ባለው ድርድር ውስጥ ዋነኛው መነጋገሪያ የኢራን የበለፀገ የዩራኒየም ክምችት ምን መሆን አለበት የሚለው ነው።

    ጦርነቱ ሲጀመር ኢራን 440 ኪሎ ግራም ዩራኒየም እንዳላት እና ይህም 60 በመቶ የበለጸገ መሆኑን አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናግረው ነበር።

    ይህም ጦር መሣሪያ ለማምረት ወደሚያስችለው 90 በመቶ የበለጸገ ዩራኒየም በአንፃራዊነት በፍጥነት ሊያድግ ይችላል።

    ኢራን በተጨማሪም 20 በመቶ ድረስ የበለጸገ 1,000 ኪሎ ግራም፣ እንዲሁም 3.6 በመቶ ገደማ የበለጸገ 8,500 ኪሎ ግራም ዩራኒየም አላት።

    ይህም በተለምዶ ለሰላማዊ አገልግሎት ማለትም ለኃይል ማመንጨት ወይም ለሕክምና ምርምር ይውላል።

    ወደ ኒውክሌር ጦር መሣሪያነት ሊቀየር የሚችለው በከፍተኛ ደረጃ የበለፀገ ዩራኒየም በአብዛኛው በኢስፋሃን እንደተከማቸ ይታመናል። ተቋሙ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ እና በእስራኤል የአየር ድብደባ ዒላማ ከተደረጉት የኢራን ሦስት የመሬት ውስጥ የኒውክሌር ጣቢያዎች አንዱ ነው።

    ይሁን እንጂ በከፍተኛ ደረጃ ከበለፀገው ዩራኒየም ምን ያህል በሌሎች ቦታዎች እንደተከማቸ ግልጽ አይደለም።

    ምንጮች እንደሚሉት ቴህራን ለ20 ዓመት ኒውክሌር እንዳታበለጽግ የተቀመጠውን እገዳ ውድቅ አድርጋለች። በምትኩ ጦርነቱ ከመፈንዳቱ በፊት ያቀረበችውን የአምስት ዓመት ገደብ ለድርድር አቅርባለች።

    በተጨማሪም 440 ኪሎ ግራም የበለፀገውን የዩራኒየም ክምችት እንድታስረክብ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች።

    ይህም ቀደም ሲል 60 በመቶ የበለፀገውን ዩራኒየሟን ለማዳከም በሚለው አቀወማ ጸንታለች።

    የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ራፋኤል ግሮስ ባለፈው ዓመት በጥቅምት ወር ለኤፒ እንደተናገሩት ይህ መጠን የበለጠ ቢበለጽግ 10 የኒውክሌር ቦምቦች ለማምረት በቂ ይሆናል።

  18. የኮንዶም ዋጋ በኢራን ጦርነት ምክንያት በ30 በመቶ ሊጨምር ይችላል ተባለ

    የዓለማችን ግዙፉ የኮንዶም አምራች ኩባንያ ካሬክስ ኃላፊ በኢራን ጦርነት ምክንያት ለምርቶቹ የሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት ማስተጓጎሉን ከቀጠለ ኩባንያው ዋጋውን እስከ 30 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ እንደሚጨምር አስታወቁ።

    የካሬክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጎህ ሚያህ ኪያት ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የምርት ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

    ማሌዥያ የሚገኘው ይህ ኩባንያ በዓመት ከአምስት ቢሊዮን በላይ ኮንዶሞችን ያመርታል።

    ዘንድሮ የኮንዶም ፍላጎት በ30 በመቶ ገደማ ጭማሪ ያሳየ ቢሆንም የጭነት ወጪ በመጨመሩ እና የመርከብ ጉዞ መስተጓጎል እየተባባሰ በመምጣቱ እጥረት መፈጠሩን ጎህ ተናግረዋል።

    "በአስቸጋሪ ጊዜያት ኮንዶም የመጠቀም አስፈላጊነት የሚጨምረው የወደፊት ሕይወትን፣ በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ይኖርዎት እንደሆነ እርግጠኛ ስላልሆኑ ነው" ሲሉ ለብሉምበርግ ተናግረዋል።

    "አሁን ልጅ ከወለዱ፣ ሌላ ተጨማሪ ሰው መመገብ ይኖርብዎታል" ሲል አክሏል።

  19. የሊባኖስ የተኩስ አቁምን ለማራዘም ንግግር እየተደረገ መሆኑን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ገለጹ

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን አገራቸው ከእስራኤል ጋር የጀመረችውን የአስር ቀን “የተኩስ አቁም ስምምነት የጊዜ ገደብ ለማራዘም” ንግግር እየተደረገ መሆኑን ገለፁ።

    ሊባኖስ እና እስራኤል ሐሙስ ዕለት በዋሺንግተን ተገናኝተው ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘዋል። በሁለቱ አገራት መካከል የአስር ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረሰው ባለፈው ሳምንት ነበር።

    አውን በኤክስ ገጻቸው ላይ ውይይቶቹ የተዘጋጁት “የእስራኤል ጥቃት ሙሉ በሙሉ በሚቆምበት፣ እስራኤል ከሊባኖስ ግዛቶች ለቅቃ በምትወጣበት፣ እስረኞችን በመመለስ፣ በዓለም አቀፍ ድንበሮች አካባቢ ወታደሮች በማሰማራት እና በጦርነቱ የወደሙትን መልሶ በመገንባት ላይ ነው።”

    አውን የሊባኖስ አቋምን ሲናገሩ “የምንደራደርበት ግልጽ ነው፤ ከሊባኖስን ሉዓላዊነት እና ጥቅም በስተቀር ምንም ዓይነት ስምምነት፣ ድርድር፣ እጅ መስጠት አይኖርም” ብለዋል።

    ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ልጥፋቸው ላይ ከአሜሪካ የተገኘው ድጋፍ ለሊባኖስ "ማባከን የሌለብንን ዕድል" ፈጥሮልናል ብለዋል።

  20. የነዳጅ ዋጋ በመናሩ የጀመርን አየር መንገድ 20 ሺህ በረራዎችን ሊያቆም ነው

    በነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት የጀርመን አየር መንገድ፣ ሉፍታንዛ፣ በመጪዎቹ ወራት በአውሮፓ ውስጥ የሚያደርጋቸውን 20 ሺህ የአጭር ርቀት በረራዎችን እንደሚያቆም አስታወቀ።

    አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር ጦርነት ከጀመሩ በኋላ የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ በእጥፍ በመጨመሩ የአጭር ርቀት በረራዎችን አክሳሪ አድርጓቸዋል።

    በዚህም ምክንያት በርካታ አየር መንገዶች በረራዎቻቸውን የቀነሱ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ በትኬት ዋጋቸው ላይ ጭማሪ አድርገዋል።

    ጦርነቱ የሚካሄድበት የባሕረ ሰላጤው አካባቢ የአውሮፕላን ነዳጅ ዋነኛው ምንጭ ሲሆን፣ አብዛኛው ነዳጅም በጦርነቱ ምክንያት በተዘጋው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚተላለፍ ነው።

    የአውሮፓ አገራት ያላቸው የአውሮፐላን ነዳጅ ክምችት እየተሟጠጠ ባለበት በአሁኑ ጊዜ፣ ክምችቱ በሳምንታት ውስጥ ሊያልቅ እንደሚችል ዓለም አቀፉ የኤነርጂ ተቋም አስጠንቅቋል።

    ሉፍታንዛ እንዳስታወቀው በአውሮፓ ውስጥ የሚያደርጋቸውን በረራዎች በከፍተኛ መጠን የሚቀንስ ቢሆንም፣ የረጅም ርቀት ዓለም አቀፍ በረራዎቹ ባሉበት ይቀጥላሉ።

    የአየር ትራንስፖርት ተንታኞች እንደሚሉት በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነት ከቀጠለ በአውሮፕላን ትኬት ዋጋ ላይ የበለጠ ጭማሪ እንደሚደረግ እንዲሁም በርካታ በረራዎች እንደሚሰረዙ አስጠንቅቀዋል።