ሊባኖስ፣ ከዋሺንግተኑ ድርድር በፊት አሜሪካ “እስራኤል ላይ ያላትን ተጽዕኖ” እንድትጠቀም ትፈልጋለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ መንግሥታቸው አሜሪካ ከዋሺንግተኑ ንግግር በፊት “እስራኤል ላይ ያላትን ተጽዕኖ” እንድትጠቀም እንደሚፈልግ ለዋሺንግተን ፖስት ተናገሩ።
ናዋፍ ሳላም ለጋዜጣው “አሜሪካ ወደጠራችው ወደዚህ ድርድር እየገባን ያለነው በእስራኤል ላይ ተጽዕኖ ማድረግ የምትችል መሆኑን በማመን ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሚናቸው ወሳኝ ነበር። ያላቸውን ተጽዕኖ እስራኤል ላይ መጠቀማቸውን ይቀጥላሉ ብለን እናምናለን” ብለዋል።
የእስራኤል ጦር በደቡብ ሊባኖስ የሚያካሄደውን ዘመቻ እንደቀጠለ ሲሆን ሳላም አገራቸው እስራኤል ግዛታቸውን ሙሉ በሙሉ ለቅቃ እንድትወጣ እንደሚፈልጉ ተናግረው “የደህንነት ቀጣና ከሚባለው ጋር መኖር አንችልም” ብለዋል።
እስራኤል ሄዝቦላህ ትጥቁን እንዲፈታ እንድምትፈልግ ተጠይቀው “በአንድ ሌሊት የሚከናወን ነገር አይደለም። ነገር ግን ዋናው ነገር ምንድን ነው ቁርጠኛ መሆናችንን አሳይተናል” ብለዋል።























