ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢራን ውሳኔዎችን የሚያስተላልፈው ማን ነው?
ቴህራን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት ከመጀመሪያ ድብደባ አንስቶ አገሪቱን በተመለከተ የሚመላለስ አንድ ቀላል ጥያቄ አለ። ማን ነው አገሪቱን የሚመራት?
መደበኛ በሆነ መልኩ መልሱ ግልጽ ነው። ሞጅታባ ኻሜኒ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን አባታቸው አሊ ኻሜኒ ከተገደሉ በኋላ የጠቅላይ መሪነቱን ስፍራ ተረክበዋል።
በእስላማዊ ሪፐብሊክ ስርዓት ውስጥ ይህ ሥልጣን ወሳኝ ነው። ጠቅላይ መሪው ስለ ማንኛውም ወሳኝ ነገሮች ማለትም ስለ ጦርነት፣ ስለ ሰላም እና ስለ ግዛቲቱ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ የመጨረሻው ይኹንታን ሰጪ ነው።
በተግባር ግን ይህ ምስል የበለጠ ደብዛዛ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን አመራርን "የተፍረከረከ" ሲሉ ገልጸውታል፤ አሜሪካም ቴህራን "የተደራጀ ሀሳብ" እንድታቀርብ እየጠበቀች መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢራን መሪዎች ሐሙስ ምሽት "ኢራን ውስጥ ለዘብተኛ ወይም ወግ አጥባቂ የሚባል ነገር የለም፤ አንድ አገር ብቻ ነበር፣ አንድ አካሄድ" የሚል መልዕክት ሲልኩ ወደ ኢራናውያን ሞባይል ስልክ ሲልኩ አንድነት በእርግጠኝነት በአእምሮአቸው ውስጥ ነበር።
የማይታየው መሪ
ሞጅታባ ኻሜኒ ሥልጣን ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ በአደባባይ ታይተው አያውቁም። የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደተዘጋ እንደሚቆይ የተናገሩበት ጨምሮ ጥቂት የጽሑፍ መግለጫዎችን ከመስጠት ባለፈ፣ የዕለት ተዕለት ቁጥጥራቸውን በተመለከተ ቀጥተኛ ማስረጃ የለም።
የኢራን ባለሥልጣናት በመጀመሪያዎቹ ጥቃቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ቢናገሩም ከዚህ በላይ መረጃ መስጠት አልፈለጉም። ኒው ዮርክ ታይምስ የኢራን ምንጮችን ጠቅሶ በዚህ ሳምንት እንደዘገበው፣ ፊታቸው ላይ ብዙ ጉዳቶች አጋጥመዋቸው ሊሆን ይችላል፣ ይህም መናገርን አዳጋች አድርጎባቸው እንደሚሆን ገምቷል።
ፊት ለፊት አለመታየታቸው ብዙ ነገር ያጎድላል። በኢራን የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ሥልጣን ተቋማዊ ብቻ ሳይሆን ተተግባሪ፣ ተከዋኝም ነው። ሟቹ አሊ ኻሜኒ ዓላማቸውን እና ፍላጎታቸውን በንግግሮቻቸው፣ በተመጠኑ እንቅስቃሴዎቻቸው እና በክፍፍሎች መካከል በሚኖራቸው አሸማጋይነት አሳይተዋል። ያ ምልክት አሁን በአብዛኛው ጠፍቷል።
ውጤቱም በትርጉም ላይ ክፍተት ፈጥሯል። አንዳንዶች ሞጅታባ ኻሜኒ ወደ መሪነት የመጡት ጦርነቱ እንደተጀመረ በመሆኑ የራሳቸውን ሥልጣን እና ቁጥጥር ለመገንባት ጊዜ አላገኙም ሲሉ ይከራከራሉ። ሌሎች ደግሞ ስለጉዳቱ የወጡ ዘገባዎችን በመጠቆም ስርዓቱን በንቃት ማስተዳደር ስለመቻላቸው ይጠይቃሉ።
ያም ሆነ ይህ ውሳኔ መስጠት ከጦርነቱ በፊት ከነበረው ባነሰ መልኩ ማዕከላዊ የሆነ ይመስላል።
ሲፈለጉ ብቻ ክፍት የሚሆኑት የዲፕሎማሲ በሮች
በወረቀት ላይ ዲፕሎማሲው ከመንግሥት ጎን ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ስር በመሆን ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ውይይት ቴህራንን መወከላቸውን ቀጥለዋል።
ነገር ግን ሁለቱም የድርድሩን አቅጣጫ መልክ የሚያስይዝ ስልታዊ አካሄድ እየነደፉ አይመስሉም። የኢራን ልዑካን ቡድን የሚመራው በፓርላማ አፈ ጉባኤው መሐማድ ባገር ጋሊባፍ በመሆኑ ሥልጣናቸው የበለጠ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
የአራግቺ ሚና አቅጣጫ ከመስጠት ይልቅ ማስፈጸም ይመስላል። ሆርሙዝ የሚከፈትበትንም ሆነ የሚዘጋበትን በተመለከተ የተናገሯቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀይረዋል።
የመጀመሪያ በባሕር መስመሩ ላይ የትራንስፖርት እንቅስቃሴው እንደቀጠለ መሆኑን ቢናገሩም ይህ ግን በፍጥነትተቀልብሷል።
ይህም ዲፕሎማሲያዊው መስመር በወታደራዊ ውሳኔዎች ላይ ቁጥጥር እንደሌለው በጨረፍታ ያሳያል።
ፔዜሽኪያን ግን በግልጽ ሳያሳዩ ራሳቸውን ከአገዛዙ ሰፊ አቅጣጫ ጋር አስተካክለዋል። በአንጻራዊ ሁኔታ ለዘብተኛ እንደሆኑ ስለሚቆጠር እስካሁን ድረስ የራሳቸውን ገለልተኛ መስመር በማስመር ጫና ከማድረግ ተቆጥበዋል።
በኢስላማባድ ከአሜሪካ ጋር ይደረጋል ተብሎ የነበረው ሁለተኛው ዙር ድርድር ጉዳዩን የበለጠ ያጠናክራል። የዲፕሎማሲ በሮች ክፍት ቢሆኑም እንኳ ሥርዓቱ ያንን ለማክበር ወይንም ለመታዘዝ ፈቃደኛ አይመስልም።
እየሰፋ የመጣው የወታደሩ ሚና
የሆርሙዝ ወሽመጥን መቆጣጠር የኢራን የመደራደሪያ አቅም ምንጭ ነው። ነገር ግን ወሽመጡን ለመዝጋት የሚተላለፉ ውሳኔዎች የሚሰጡት በዲፕሎማሲ ቡድኑ ሳይሆን በአህመድ ቫሂዲ በሚመራው እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ነው።
ይህም እውነተኛ ኃይልን ከጀርባ ሆነው አመራሩን በሚዘውሩት ተዋናዮች እጅ ውስጥ መሆኑን ያመለክታል። ከቀደሙት ቀውሶች በተለየ እነዚህ ወሳኝ እርምጃዎች በግልፅ በማን እንደሚተላለፉ ለማወቅ የሚቻልበት መንገድ የለም። በምትኩ በተደጋጋሚ የሚስተዋለው በመጀመሪያ እርምጃ መውሰድ በኋላ መልዕክቶችን ማስተላለፍ የሚለው ሲሆን ይህም ቢሆን ሁልጊዜ ወጥነት የለውም።
በተግባር የሆርሙዝን ወሽመጥ መዘጋት ወይም በባሕረ ሰላጤው ውስጥ ያሉ ዒላማዎችን ማጥቃት የአብዮታዊ ዘቡ ኃላፊነት ሲሆን ይህም የቀውሱን ፍጥነት ይወስናል። ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ምላሾች ብዙውን ጊዜ ከመምራት ይልቅ የሚከተሉ ናቸው።
ይህ ማለት በመንግሥት የተለያየ የአስተዳደር እርከኖች ውስጥ መፍረክረክ አለ ማለት አይደለም። ነገር ግን ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በሌለበት ጊዜ የአብዮታዊ ዘቡ የአሠራር ነፃነት ቢያንስ ለጊዜው እየሰፋ መምጣቱን ይጠቁማል።
ወደፊት የመጡት ጋሊባፍ
መሐመድ ባገር ጋሊባፍ አገሪቱ እንዲህ ትርምስምሷ በወጣበት ወቅት ከመካከል ተገኝተዋል።
ጋሊባፍ አሁን የፓርላማ አፈ ጉባኤ ቢሆኑም ከዚህ በፊት የአብዮታዊ ዘቡ አዛዥ ነበሩ። በዚህ ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር አገራቸው በምታደርገው ጦርነት ውስጥ በጉልህ ከሚታዩ ባለሥልጣናት መካከል ናቸው።
የኢራንን ተደራዳሪ ልዑክ የሚመሩ ሲሆን የአገራቸውን አቋም ለሕዝቡ ይፋ የሚያደርጉ፣ አንዳንዴ ጦርነቱን በርዕዮተ ዓለም ሳይሆን በተግባር የሚያስረዱ ናቸው።
በፓርላማ ውስጥም ሆነ በወግ አጥባቂ ቡድኖች መካከል አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ለድርድር መቀመጧ የማይዋጥላቸው ሰዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።
አክራሪ ቡድኖች የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ከጊዜ ወደጊዜ እየጎሉ መጥተዋል። በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እና በይፋ በሚደረጉ ቅስቀሳዎች ለድርድር መቀመጥ በአገሪቱ ጠላቶች ፊት ደካማ መሆን ነው የሚሉ ንግግሮች እየተደመጡ ነው።
ስለዚህ ጋሊባፍ ያሉበት ሁኔታ ግልጽ አይደለም። ጠቃሚ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ በድርድር በመሳተፍም ሆነ መልዕክቶችን ለሕዝቡ በማስተላለፍ ረገድ ከፊት ቢታዩም ነገር ግን በዚህ መንገድ ለመቀጠል ሙሉ ይፋዊ ሥልጣን አላቸው ወይ የሚለው አይታወቅም።
እርምጃዎቻቸው ከሞጅታባ ኻሜኒ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ መሆኑን ቢናገሩም ነገር ግን አሁንም በቀጥታ በትብብር ስለመስራታቸው የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ የለም።
ከላይ በሚመጡ ትዕዛዞች ላይ የተመሰረተ ሥርዓት ውስጥ ያለው አሻሚነት ግልጽ ነው።
እንደሚባለው አንድነት አለ?
እነዚህ ሁኔታዎች ሁሉ ከግምት ውስጥ ሲገቡ ሥርዓቱ እየሰራ መሆኑን ይናገራሉ፤ ነገር ግን እየተመራ ያለው በተቀናጀ መልኩ አለመሆኑንም ያሳብቃሉ።
የጠቅላይ መሪ ሥልጣን አለ፤ ነገር ግን በግልጽ ተግባር ላይ አይውልም። ፕሬዚዳንቱ ከስርዓቱ ጋር እጅ እና ጓንት ናቸው ነገር ግን አመራር አይሰጡም። ዲፕሎማሲ አለ ግን ወሳኝ አይደለም።
ንግግሮች እና ድርድሮች እየተካሄዱ ነው ነገር ግን ግልጽ ውጤት አያመጡም። ወታደሩ ቁልፍ መደራደሪያዎች ይይዛል፣ ነገር ግን በግልጽ የሚታይ መሪ የለውም። የፖለቲካ ሰዎች ወደፊት ሲመጡ ይታያል፣ ነገር ግን ቅቡልነታቸው ላይ ጥያቄ ይነሳል።
ይህ መፈራረስ አይደለም። እስላማዊው ሪፐብሊክ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ነገር ግን የበለጠ ስውር የሆነ ነገር መኖሩን ይጠቁማል።
ሥርዓቱ የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋት የመሰሉ ቁልፍ መደራደሪያዎች በእጁ ናቸው። ነገር ግን በተለይ ሁኔታዎች በሚካረሩበት ወቅት ይህንን አቅሙን በግልጽ እና በውጤታማ ዕቅድ ለመምራት ሲውተረተር ይስተዋላል።
አሁንም በብዙ ግንባሮች ላይ እርምጃ ሊወስድ ይችላል፤ ነገር ግን ወደ ራሱ የሥልጣን ማዕከላት ግልጽ አቅጣጫ ለመስጠት ይቸገራል።
በኢራን የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ምልክት መሆን ወጥነት የሚጠበቅበት አንዱ መንገድ ነው።
ለጊዜው ሥርዓቱ ቁጥጥርን በማድረግ ረገድም ሆነ እየጨመረ በሚመጣ ጫና ውስጥ ባለመከፋፈል የተረጋጋ ነው። ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ አንድነት እየተተገበረ ነው ወይስ እንዲሁ በአፍ ብቻ የሚነገር የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል።