ደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ውስጥ በተከፈተ ተኩስ ቢያንስ 12 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ ከተማ ውስጥ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ 12 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ፖሊስ አስታወቁ።
ክሌቭላንድ በተባለው የከተማዋ አካባቢ ማክሰኞ ምሽት በተፈጸመው ጥቃት ከሞቱት በተጨማሪ ሌሎች ዘጠኝ ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን፣ የጥቃቱ ፈጻሚዎችን ለመያዝ ፖሊስ አሰሳ እያካሄደ ነው።
ፖሊስ ባወጣው መግለጫ እንዳለው "ከአስር በላይ ጥቃቱን ፈጽመዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች በመኪና መጥተው በአካባቢው ከሚገኝ የነዳጅ ማደያ አጠገብ ከወረዱ በኋላ" ተኩስ ከፍተዋል።
"የጥቃቱ ፈጻሚ ተጠርጣሪዎች ሕገወጥ ወደ ሆነው የመኖሪያ አካባቢ በመግባት እየተዘዋወሩ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በነዋሪዎች እና በአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት ላይ ተኩስ ከፍተው ጉዳት ካደረሱ በኋላ በመጡበት መኪና ከቦታው ተሰውረዋል" በማለት የፖሊስ መግለጫ አመልክቷል።
ደቡብ አፍሪካ በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ግድያ ከሚፈጸምባቸው አገራት መካከል እንዷ ስትሆን፣ በአማካኝ በቀን ወደ 60 የሚጠጉ ሰዎች ይገደሉባታል ይባላል።
በሕገወጥ የመኖሪያ አካባቢዎች ውስጥ በጦር መሳሪያ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ በተደጋጋሚ የሚከሰት ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜም በወሮበላ ቡድኖች እና በግለሰቦች ጸብ ምክንያት ያጋጥማል።
ጥቃቱ የተፈጸመበት አካባቢ የፖሊስ ጣቢያ ማክሰኞ ምሽት አምስት ሰዓት አካባቢ "ተኩስ እየተካሄደ መሆኑን የሚገልጽ ሪፖርት" ለፖሊስ መኮንኖቹ እንደደረሰው አስታውቋል።
ጥቃቱን ተከትሎ የአደጋ ጊዜ የሕክምና አገለግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች የተጎዱ ሰዎችን ለማከም ወደ ስፍራው ተልከው ነበር።
ፖሊስ እንዳለው ስምንት ወንዶች እና ሦስት ሴቶች በጥቃቱ ስፍራ እንዳሉ መሞታቸውን እና አንደኛው ግለሰብ በደረሰበት ጉዳት ሆስፒታል ከገባ በኋላ ሕይወቱ አልፏል።
በተጨማሪም ቢያንስ ሌሎች ዘጠኝ ሰዎች በጥይት ቆስለው ሕክምና እንዲያገኙ ወደ ተለያዩ የሕክምና ተቋማት መወሰዳቸው ተነግሯል።
ለበርካታ ሰዎች ሞት እና ጉዳት ምክንያት ለሆነው ጥቃት "ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር እንደሌለ እና ይህም እየተካሄደ ያለው ምርመራ አካል" መሆኑን የፖሊስ መግለጫ ጠቅሷል።
ባለፈው ዓመት እዚያው ጆሃንስበርግ ውስጥ በአንድ መጠጥ ቤት ላይ በተመሳሳይ በተከፈተ ተኩስ ዘጠኝ ሰዎች በጅምላ ተገድለዋል።
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚደርሱ ሕጋዊ የጦር መሳሪያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ቢያንስ ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎች እንዳሉ ከደቡብ አፍሪካ የጦር መሳሪያ ባለቤቶች ማኅበር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።















