ለፌደራል መንግሥት የ2019 በጀት ከ2.3 ትሪሊየን ብር በላይ ቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለፌደራል መንግሥት ለቀጣዩ 2019 ዓ.ም. በጀት ከ2.3 ትሪሊየን ብር በላይ አጸደቀ።
ዛሬ ሰኔ 2/2018 ዓ.ም. በተካሄደው 56ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በቀረበው የፌደራል መንግሥት የ2019 ረቂቅ በጀት ላይ "በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል" ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ተገልጿል።
ለመደበኛ ወጪዎች፣ ለካፒታል ወጪዎች፣ ለክልል መንግሥታት ድጋፍ እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ የሚውል 2,339,268,126,738 (ሁለት ትሪሊዮን፣ ሦስት መቶ ሰላሳ ዘጠኝ ቢሊዮን፣ ሁለት መቶ ስድሳ ስምንት ሚሊዮን፣ አንድ መቶ ሀያ ስድስት ሺ፣ ሰባት መቶ ሰላሳ ስምንት ብር) በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቦ መጽደቁ ተገልጿል።
የፌደራል መንግሥት ለ2018 ዓ.ም. በጀት ዓመት የመደበው 1.93 ትሪሊዮን ብር ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባወጣው መግለጫ የ2019 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥት በጀት የ2018 ዓ.ም. በጀት ዓመት "የፕሮግራም በጀት አፈጻጸምን መነሻ በማድረግ" መዘጋጀቱን ይገልጻል።
በቀጣይ ሊኖር የሚችለው "የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎችና ዓላማዎች" እንዲሁም በመንግሥት የተቀመጡ "ግቦችን ለማሳካት የመንግሥትን የፋይናንስ አቅም እና አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ከተሰጣቸው ተልዕኮ እና ኃላፊነት አንጻር የሚያስፈልገውን ወጪ በመገምገም" ተዘጋጅቶ መቅረቡ ተመልክቷል።
ምክር ቤቱ ከ2019-2023 ዓ.ም. በሚኖረው የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍ ላይ እንደተወያየ ጠቅሶ፤ "የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ካሉበት ተግዳሮቶች እየተላቀቀ እና የኢኮኖሚው መሠረቶችም እየተጠናከሩ መጥተዋል" ብሏል።
"በኢኮኖሚ ሪፎርሙ የተገኙ አበረታች ውጤቶችን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል" እንዲሁም "ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊስካል ታሳቢዎች ላይ በመመሥረት" የ2019 ዓ.ም. በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት በጀት መነሻ መሆኑም ተጠቅሷል።















