ሁለቱ የኢሕአፓ ፖለቲከኞች እና ጠበቃ አበራ ንጉሥ በዋስ እንዲፈቱ ፍርድ ቤት ወሰነ

ይሳቅ ወልዳይ (ግራ)፣ አበበ አካሉ (መሃል) እና ጠበቃ አበራ ንጉሥ (ቀኝ)
የምስሉ መግለጫ, ይሳቅ ወልዳይ (ግራ)፣ አበበ አካሉ (መሃል) እና ጠበቃ አበራ ንጉሥ (ቀኝ)
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

"በሽብር ወንጀል" የተጠረጠሩት ፖለቲከኞቹ አበበ አካሉ እና ይሳቅ ወልዳይ እንዲሁም ጠበቃ አበራ ንጉሥ እያንዳንዳቸው በ50 ሺህ ብር ዋስ እንዲፈቱ ፍርድ ቤት ወሰነ።

ፖሊስ በጠየቀው የ14 ቀን ተጨማሪ የምርማራ ጊዜ ቀጠሮ ላይ ትላንት ሐሙስ ነሐሴ 28/2018 ዓ.ም. ክርክር ከተደረገ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠት ለዛሬ አርብ 9 ሰዓት ቀጥሮ ነበር።

በዚህም መሠረት ጉዳዩን በመከታተል ላይ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፣ የፖሊስን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ እያንዳንዳንዳቸው ተጠርጣሪዎች የ50 ሺህ ብር ዋስ አስይዘው እንዲፈቱ መወሰኑን ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠበቃው እንደገለፁት፣ ፍርድ ቤቱ ባለፈው ችሎት "የመጨረሻ" ያለውን የአንድ ሳምንት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ነበር ለፖሊስ የሰጠው።

ሆኖም፣ የፌዴራል ፖሊስ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንዲሰጠው ለችሎቱ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ባቀረበው ማመልከቻ ጠይቋል።

እስከ ነሐሴ 28/2018 ዓ.ም በተሰጠው ጊዜ ውስጥ፣ የስድስት ሰዎችን የምስክርነት ቃል መቀበሉን፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የፎረንሲክ ማስረጃዎችን ማስመጣቱን፣ እንዲሁም ከ11 ባንኮች እና ከመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የጠየቃቸውን ማስረጃዎች መቀበሉን ፖሊስ ገልጿል።

በተጨማሪም ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ የዘይሴ ብሔረሰብ ቀበሌዎች ውስጥ ተጠርጣሪዎቹ ባደራጁት ታጣቂ ኃይል ተገድለዋል ስላላቸው 23 ንፁኃን ዜጎች እና ስለደረሰው ጉዳት የማጣራት ሥራ ማከናወኑንም አስታውቋል።

ይሁን እንጂ ቀሪ የምስክሮችን ቃል የመቀበል፣ የሆስፒታል ማስረጃዎችን ውጤታ ማስመጣት፣ እና ሌሎችም የሚቀሩት ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሶ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው አመልክቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚህ በተጨማሪም፣ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ በምስክሮች ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንዲሁም ከአገር ሊወጡ እንደሚችሉ ስጋቱን ገልጾ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው፣ ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ያቀረበው ምክንያት ከዚህ ቀደም ካቀረበው ጋር ተመሳሳይ መሆኑን በማንሳት ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ብለው ሐሙስ በነበረው የቀጠሮ ችሎት ላይ መከራከራቸውን አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ተናግረዋል።

ፖሊስ የተለየ ነገር ያቀረበው በዋስ ቢወጡ ከአገር ሊሸሹ ይችላሉ የሚል ብቻ ነው ያሉት አቶ ሰለሞን፣ ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ አበበ አካሉ "እንኳን ከአገር ሊሸሹ ፓስፖርትም የላቸውም" ብለዋል።

ፖሊስ ከአገር ይሸሻሉ የሚል ስጋት ካለው ለኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ደብዳቤ በመጻፍ ሊያሳግዳቸው እየቻለ ይህን በምክንያትነት መቅረብ የለበትም ብለው መከራከራቸውንም አክለዋል።

ፍርድ ቤቱ ከሳምንት በፊት ነሐሴ 21 ቀን በነበረው ችሎት ለፖሊስ "የመጨረሻ" ያለውን ተጨማሪ ጊዜ የሰጠው ቀሪ የምስክር ቃል የመቀበል ሥራዎችን እንዲሠራ በሚል መሆኑን በማስታወስም፣ አሁንም ተመሳሳይ ምክንያት ማቅረቡ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም ብለዋል።

በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸው ጉዳያቸውን ከእስር ቤት ውጪ ሆነው እንዲከታተሉ አመልክተዋል።

ሐሙስ ዕለት በነበረው የችሎት ውሎ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ዛሬ አርብ ከሰዓት ፖሊስ የቴክኒክ እና የፎረንሲክ ማስረጃ ቀድሞ ማምጣቱን በማረጋገጡ እና የምስክሮችን ቃል ለመቀበል በተሰጠው የመጨረሻ የጊዜ ገደብ ውስጥ የስድስት ምስክሮችን ቃል መቀበሉን ከቀረበለት ሰነድ ማረጋገጡን ስለመግለፁ ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።

ይህም፣ ፖሊስ የምርመራ ሥራውን ማጠናቀቁን የሚያመለክት መሆኑን በመጥቀስ፣ ተጠርጣሪዎቹ በእስር መቆየታቸው አላስፈላጊ ነው በማለት የዋስትና ብይን መስጠቱን አክለው ገልፀዋል።

በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩት ሁለቱ የኢሕአፓ ፖለቲከኞች አቶ አበበ አካሉ እና አቶ ይሳቅ ወልዳይ እንዲሁም ጠበቃ አበራ ንጉሥ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከአንድ ወር በፊት ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም. ነበር።

ፖሊስ ሦስቱን ተጠርጣሪዎች "ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ በማሰብ" የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ተብለው ከተጠቀሱት ከህወሓት፣ "ፅምዶ" ተብሎ ከሚጠራው ኃይል እና በስም ያልተጠቀሱ ሌሎች "ፀረ-ሰላም ኃይሎች" ጋር ተቀናጅተው እንደሚንቀሳቀሱ ወንጅሏል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረ በሚገኙ የኘው የዘይሴ ብሔረሰብ ውስጥ "ታጣቂ ኃይሎችን አደራጅተው" ለሰላማዊ ሰዎች ሞት እና ለንብረት ውድመት ምክንያት ሆነዋል የሚለውም ፖሊስ ካቀረበባቸው ውንጀላዎች መካከል አንዱ ነው።