ለአንድ ወር ገደማ ባሕር ላይ ሲንሳፈፉ ከነበሩ ስደተኞች ውስጥ ከ80 በላዩ ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ለ27 ቀናት ሲንሳፈፍ በነበረው ጀልባ ላይ ተሳፍረው ከነበሩ ስደተኞች ውስጥ ጨቅላ ሕፃንን ጨምሮ ከ80 በላይ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተገለጸ።
ስደቶቹን የጫነው ጀልባ ረቡዕ ዕለት በስፔን የባሕር ላይ ነፍስ አድን ቡድኖች የተገኘው ከግራን ካናሪያ የባሕር ዳርቻ ከተማ አርጊኔ በስተደቡብ ምዕራብ 65 ናውቲካል ማይልስ ርቀት ላይ ነው።
ጀልባው ውስጥ በሕይወት የተረፉ 44 ሰዎች እና አምስት አስከሬኖች ተገኝተዋል።
ጀልባው በሐምሌ መጨረሻ 127 ሰዎችን አሳፍሮ ከምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋምቢያ እንደተነሳ ይታመናል።
'ካሚናንዶ ፍሮንቴራስ' የተባለው የስፔን የበጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሄሌና ማሌኖ ጋርዞን 83 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ተናግራለች።
ስደተኞቹ በተገኙበት ወቅት አስቸጋሪ የባሕር ሁኔታ ስለነበረ ጀልባ ውስጥ የነበሩት አምስት አስከሬኖችን እዚያው ለመተው እንደተገደደ የስፔን የባሕር ነፍስ አድን አስታውቋል።
ድርጅቱ ከጅምሩ ጀልባው ላይ ምን ያህል ሰዎች ተስፍረው እንደነበር ማረጋገጥ አልቻለም።
በሕይወት የተረፉት 44 ያህሉ ሰዎች ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት የመጡ ወንዶች መሆናቸውን የባሕር ላይ ነፍስ አድን ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
"የመታደግ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ በስፍራው የነበረው አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ጀልባው ውስጥ የተገኙትን አምስት አስከሬኖች ማውጣት የማይቻል አድርጎታል" ሲል ከፍተኛ ነፋስ እና ማዕበል ከተሰቱን አስረድቷል።
በሕይወቱ ከተገኙት ውስጥ ሦስቱ አስጊ ሁኔታ ላይ ስለነበሩ በሄሊኮፕተር ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጿል።
ቀሪዎቹ ደግሞ በባሕር ጉዞ ወደ ግራን ካናሪያ ተወስደው፣ ሐሙስ ጠዋት ወደ ደሴቱ ደርሰዋል።
የካናሪ ደሴቶች መንግሥት ኃላፊ የሆኑት ፈርናንዶ ክላቪሆ "የሰዎች ሕይወት መጥፋት መቀጠሉ ሊታገሱት የማይቻል ነገር ነው። አትላንቲክ ውቅያኖስ የሞት ወጥመድ ሆኖ መቀጠሉን የካናሪ ደሴቶች ሊላመዱት ወይም ሊቀበሉት አይችሉም" ሲሉ ኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
የአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የሚገኘው ከምዕራብ አፍሪካ ወደ ካናሪ ደሴቶች የሚወስድ የባሕር መስመር፣ ዓለም ላይ ካሉ እጅግ አደገኛ የስደተኞች መሻገሪያዎች አንዱ ነው።
በዚህ መስመር ላይ በማዕበል፣ በኃይለኛ ሞገድ እና በረጅም ርቀት ምክንያት የሚፈጠሩ አደጋዎች ቢኖሩም፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ የስፔን ግዛት ለመድረስ ሲሉ በየዓመቱ ይህንን አደገኛ ጉዞ ለማድረግ ይሞክራሉ።















