የኢቦላ በሽታ ስጋት ባየለበት ወቅት ሦስት ክትባቶች እየበለፀጉ መሆናቸው ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ወደ 250 የሚጠጉ ሰዎችን የገደለውና ብዙም ያልተለመደውን የኢቦላ ዝርያ ለመከላከል የሚረዱ ሦስት ክትባቶች እየበለፀጉ መሆናቸው ተገለፀ።
አንደኛውን ክትባት እየሰራ ያለው ዓለም አቀፉ የኤድስ ቫክሲን ኢንሸቲቭ (አይኤቪአይ) ሲሆን ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና መድሃኒት አምራቹ - ሞደርና ሌሎቹን ሁለት ክትባቶች ለመስራት ምርምር እያካሄዱ ነው።
ምርምር ለሚያካሂዱት እያንዳንዱ ቡድን የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ያለው የወረርሽኝ ዝግጅት ፈጠራዎች ጥምረት እያንዳንዱ "ቀን ትርጉም አለው" ብሏል።
አሁን ላይ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች በቡንዲቡግዮ ቫይረስ መያዛቸው የተጠረጠረ ሲሆን በኡጋንዳ ደግሞ ዘጠኝ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
በግጭት ውስጥ ባለው እና ውስን የጤና መሠረተ ልማት ባሉበት ኮንጎ በሽታው ከተገኘ በኋላ ከአውሮፓውያኑ 2014 እስከ 2016 በምዕራብ አፍሪካ እንደተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
በእነዚህ ጊዜያት ወደ 29 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን ከ11 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሞተዋል።
የአይኤቪአይ ዋና ኃላፊ ዶክተር ማርክ ፌንበርግም "አሁን ላይ የተከሰተው በሽታ ከዚህ ቀደም እንደነበረው የከፋ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ፤ የከፋ ባይሆን እንኳን ክትባት ማበልፀጉ እና ሌሎች የመከላከያ እርምጃዎችን መውሰዱ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው" ብለዋል።
ተቋሙ ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ መሆኑንና በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ በበሽታው የተያዙ ሰዎች መመዝገባቸውን የገለፀውን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ስጋትም አስተጋብቷል።
ለሁሉም የኢቦላ ዝርያዎችም ክትባት መሰራት አለበትም ብሏል።
ኢቦላ ስድስት የቫይረስ ዝርያዎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ መካከል ወረርሽኝ እንደሚፈጥሩ የሚታወቁት ሦስቱ ብቻ ናቸው።
ብዙ የተለመደው ዛየር የሚባል ሲሆን ክትባት አለው። አሁን ላይ የተፈጠረው በሽታ ግን ቡንዲቡግዮ በሚባል ሌላ የቫይረስ ዝርያ የሚመጣ ነው።
በሽታው ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ የታየ ሲሆን እስካሁን የተረጋገጠ ክትባት የለውም።
አይኤቪአይም ይህንን ቫይረስ ለመከላከል የሚያስችል የዛየር ኢቦላ ክትባትን ለማሻሻል እየሰራ ነው።
በሙከራ ላይ ያለው ክትባቱ በዝንጀሮዎች ላይ የተፈተሸ ሲሆን መቶ በመቶ ሊባል በሚችል መልኩ በሽታውን ተከላክሏል።
ዶ/ር ፌንበርግ ያሉት ማስረጃዎች ክትባቱ በሽታውን በመከላከል አቅሙ ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል። ሆኖም ምንም እንኳን በፍጥነት ለመስራት እየሞከሩ ቢሆንም ክትባቱን ለክሊኒካል ሙከራ ለማዘጋጀት ከሰባት እስከ ዘጠኝ ወራት ሊደወስድ ይችላል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ መድሃኒት አምራቹ ሞደርና ክትባቱን በፍጥነት ለማምረት በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ጥቅም ላይ የዋለውን ኤምአርኤንኤ የተባለ ቴክኖሎጂ እየተጠቀመ ይገኛል።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲም የኢቦላን ክትባት ለመስራት የራሱን የክትባት ማምረቻ ቴክኖሎጂ እየተጠቀመ መሆኑን ገልጿል።ይህም ከሁለት እስከ ሦስት ወር ባሉት ጊዜያት ለክሊኒካል ሙከራ ዝግጁ ይሆናል ብሏል።
ተቋማቱ የሚጠቀሙት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች እና የቫይረሱ ዝርያ ከሰውነት የበሽታ መከላከያ ሥርዓት ጋር ለማሰልጠን የሚጠቀሙት ዘዴ መለያየት የመከላከል አቅሙ እና የሚያስፈልገው የክትባት መጠን ላይ ተፅዕኖ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ግን በክሊኒክ መሞከር ይኖርበታል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የቡንዲቡግዮ ቫይረስ ክትባት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እንዲሁም ወደፊት ለሚከሰቱ ወረርሽኞች የሚደረገውን ዝግጁነትን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።















