ብራዚል በኢቦላ የተጠረጠሩ ሁለት ታካሚዎችን እየተከታተልኩ ነው አለች

የደም ናሙና ምርመራ ሲደረግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የብራዚል የጤና ባለሥልጣናት በአገሪት ሁለት ግዙፍ ከተሞች ሳኦ ፓውሎ እና ሪዮ ዴ ጄኔሮ ሁለት በኢቦላ ቫይረስ ተይዘው ሊሆን ይችላል የተባሉ ታካሚዎችን እየተከታተሉ መሆኑ ተነገረ።

ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመጣ የ37 ዓመት ወንድ ታካሚ ትኩሳትን ጨምሮ ሌሎች ምልክቶች እንዳሳየ የሳኦ ፓውሎ ግዛት መንግሥት ተናግሯል።

የሪዮ ግዛት የጤና ቢሮ ከኡጋንዳ የመጣ ቤልጂየማዊ ዜጋ "ሳል፣ ብርድ ብርድ ማለት እና ተቅማጥ የመሰሉ ምልክቶችን" ማሳየቱን ተከትሎ የደኅንነት መመሪያዎች መተግበር እንደጀመሩ አስታውቋል።

የሁለቱም ታካሚዎች የምርመራ ውጤት በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚታወቅ ይጠበቃል።

ታካሚዎቹ በውጤታቸው በኢቦላ ቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቫይረሱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከአፍሪካ አህጉር ውጭ የተገኘ ኬዝ ይሆናል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አንድ ሺህ በኢቦላ ቫይረስ የተጠረጠሩ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፤ 246 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል። ኡጋንዳ ዘጠኝ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን እና አንድ ሰው ደግሞ እንደሞተ አረጋግጣለች።

አሁን የተቀሰቀሰው የኦቦላ ቫይረስ 'ቡንዲቡጋዮ' በተባለ ዝርያ የተከሰተ ነው። ዝርያው እስካሁን የተረጋገጠ ክትባት የሌለው እና በቫይረሱ የተያዙ አንድ ሦስተኛዎችን የሚገድል ነው።

በብራዚል ተጠርጥረው ክትትል እየተደረገባቸው ያሉት ሁለቱ ታካሚዎች በሌላ በሽታ መያዛቸውም ተነግሯል። በሳኦ ፓውሎ ከዲሞክራቲክ ሪፐንሊክ ኮንጎ የመጣው ታካሚ ማጅራት ገትር እንደተያዘ እና ከባድ ሁኔታ ላይ መሆኑ ተነግሯል። በሪዮ የሚገኘው የቤልጂየም ዜጋ ደግሞ ወባ እንደተገኘበት ተነግሯል።

የብራዚል ባለሥልጣናት ታካሚዎቹ ላይ ቀደም ብለው የተገኙት በሽታዎች በኢቦላ ያለመያዛችውን እድል ዝቅ አያደርግም ብለዋል።

ኢቦላ ቫይረስ እንስሳትን በዋናነት ደግሞ የሌሊት ወፍን የሚይዝ በሽራ ሲሆን፤ በሰዎች ላይ በሽታው የሚከሰተው በቫይረሱ የተያዙ እንስሳትን ሲመገቡ አሊያም ሲይዙ ነው።

ኢቦላ በቀጥታ ንኪኪ ከተያዙ ሰዎች በሚወጣ የሰውነት ፈሳሽ አማካኝነት የሚተላለፍ ሲሆን፤ ይህም ላብ፣ ምራቅ፣ ደም፣ የዘር ፈሳሽ፣ ሰገራ፣ ሽንት እና ትውከትን ያካትታል።

ቅዳሜ ዕለት ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በፍጥነት የተዛመተው ቫይረሱ "አሳሳቢ ሁኔታ" መፍጠሩን የገለፀ ሲሆን፤ በሽታው እንደተቀሰቀሰ ያልተጠበቀ የኬዞች ቁጥር መገኘቱን ተናግሯል።

የዓለም የጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በቫይረሱ ክፉኛ በተጎዳው ኢቱሪ ግዛት ጉብኝታቸውን የቀጠሉ ሲሆን፤ የቁጥጥር ጥረቱን እየተከታተሉ ነው።

ምንም እንኳ ቫይረሱ ከአፍሪካ ውጭ ሊገኝ የሚችልበት እድል ቦኖርም የዓለም የጤና ድርጅት በተደጋጋሚ በዓለም የሚኖረው ስርጭት ዝቅተኛ ነው ብሏል።