ኢትዮጵያ የሱዳን ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ አገሪቷን ለቅቀው እንዲወጡ አዘዘች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ ስድስት የሱዳን ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቷን አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘገበ።
እርምጃው አንዳቸው የሌላቸውን "ጠላት በመደገፍ" በመካሰስ ግንኙነታቸው እየሻከረ የመጣውን የሁለቱን አገራት ውጥረት የበለጠ ያባብሰዋል ተብሎ ተሰግቷል።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጦር ጋር እየተፋለመ የሚገኘውን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን (አርኤስኤፍ) በመደገፍ በሱዳን የምትከሰስ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በበኩሏ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የሚገኙ አማጺያንን በመደገፍ ሱዳንን ትወነጅላለች።
ሆኖም ሁለቱም ወገኖች የሚቀርብባቸውን ክሶች ያስተባብላሉ።
ኢትዮጵያ አማጺያንን በመደገፍ ኤርትራን እና ግብፅንም የከሰሰች ሲሆን፤ ከኤርትራ ጋር ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጧ ይታወሳል። ኢትዮጵያ እና ግብፅ አንዳቸው የሌላኛቸውን ዲፕሎማት ከአገር እንዲወጡ መወሰናቸውም አይዘነጋም።
ግብፅ እና ኤርትራ የቀረበባቸውን ክስ ያስተባብላሉ።
የሱዳን እና ኢትዮጵያ ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱ በየአገራቱ የሚካሄደውን ጦርነት ሊስፋፋ እንዲሁም ወደ ቀጣናው ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
እሑድ ዕለት የሱዳን መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እና ለአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት አቤቱታ ማቅረቡን አስታውቋል።
ሱዳን፣ ኢትዮጵያ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) በሱዳን መሠረተ ልማቶች ላይ ለሚፈፅማቸው የድሮን ጥቃቶች መነሻ ግዛቷን እንዲጠቀም ፈቅዳለች ስትል ትከስሳለች።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ የሱዳን ዲፕሎማቶችን ማባረሯን በተመለከተ ሮይተርስ የዜና ወኪል ከኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ አስተያየት መጠየቁን የገለጸ ሲሆን ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጡም።
ቢቢሲ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አስተያየት ጠይቆ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጡም።
ሮይተርስ አንድ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ኢትዮጵያ የሱዳን አዋሳኝ በሆነችው እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መቀመጫ በሆነችው አሶሳ የሚገኘው የሱዳን ቆንስላ ስድስት ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ አገሪቷን ለቅቀው እንዲወጡ አዝዛለች።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ባለሥልጣኑ ውሳኔው በምን ምክንያት እንደተላለፈ አልገለጹም።
በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከምትገኘው ሱዳን ጋር በሚጎራበተው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የአማጺው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሥልጠና ካምፕ መገንባቱን ከምንጮች እና ከሳተላይት ምሥሎች ማረገጋጡን ሮይተርስ የካቲት ወር ላይ መዘገቡ ይታወሳል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሥልጠና ትሰጥበታለች በተባለው በዚህ ካምፕ ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ምልምሎች ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ ምንጮች መናገራቸውንም የዜና ወኪሉ ዘግቦ ነበር።
ኢትዮጵያ ግን በሱዳን ጦርነት ውስጥ የሚፋለመውን አርኤስኤፍ በመደገፍ የቀረበባትን ክስ አስተባብላለች።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችም በሱዳን ጦርነት ውስጥ '"በማንኛውም መንገድ" ተሳትፎ እንደሌላት በተደጋጋሚ ገልጻለች።
በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የተቀሰቀሰው ፕሬዚደንት ኦማር ሁሴን አልበሽር በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ አገሪቷን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ በተደረገው ጥረት በተፈጠረ የሥልጣን ሽኩቻ ነበር።
ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት በተቀሰቀሰው በዚህ ጦርነት ከ14 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት መረጃዎች ያመለክታሉ። ጦርነቱ በዓለም ላይ ከተከሰቱ አስከፊ ሰብአዊ ቀውሶች አንዱን አስከትሏል።

































