ይድነቃቸው ተሰማ፡ የአፍሪካ የእግር ኳስ አባት

የፎቶው ባለመብት, Tadele Yidnekatchew Tessema
ሞሮኮ፣ ስታደ ማኒሲፓል የተሰኘውን ስታዲም ስያሜውን ወደ ስታደ ተሰማ በመቀየር አቶ ይድነቃቸው ተሰማን ዘክራለች።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2011 ዓ. ም. የኮከብ ተጫዋቾች ሽልማት ወቅት አቶ ይድነቃቸው ተሰማን የሕይወት ዘመን ተሸላሚ በማድረግ አስታውሷቸዋል።
መጋቢት 5 ቀን 2009 ዓ. ም. በስማቸው የተሰየመው እና በ70 ሚሊዮን ብር የተገነባው ይድነቃቸው ተሰማ የወጣቶች እግር ኳስ አካዳሚ ተመርቋል።
ትናንት ኅዳር 9 ቀን 2019 ዓ. ም. ደግሞ በአዲስ አበባ በመገንባት ላይ በሚገኘው የአደይ አበባ ስታዲየም ፊት ለፊት ይድነቃቸው ተሰማን የሚዘክር ሐውልት ቆሞላቸዋል።
ለመሆኑ የአፍሪካ እግር ኳስ አባት በመባል የሚታወቁት ይድነቃቸው ተሰማ ማን ናቸው? ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ እግር ኳስ ያበረከቱት አስተዋጽኦስ ምን ይመስላል?

የፎቶው ባለመብት, Tadele Tessema
አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የዘመን መለወጫ ዕለት መስከረም 1 ቀን 1914 ዓ. ም. በጅማ ከተማ ነው የተወለዱት።
የቄስ ትምህርት ቤት በመግባት ፊደል ከቆጠሩ በኋላ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ፣ በተፈሪ መኮንን እንዲሁም በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ፊታቸውን ወደ ስፖርቱ ዓለም አዙረዋል።
በትምህርት ቤት ቆይታቸው በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ይሳተፉ ነበር።
ሩጫ፣ ብስክሌት፣ ቦክስ እና እግር ይጠቀሳሉ።
ከሁሉም አብልጠው የሚወዱት ግን እግር ኳስን ነበር። እናም ትኩረታቸውም ሕይወታቸውም እግር ኳስ ሆነ።
ይድነቃቸው በእግር ኳስ ተጫዋችነት ሕይወታቸው ለ23 ዓመታት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ተሰልፈው ተጫውተዋል።
በክለቡ በነበራቸው ቆይታ ተጫዋችም አሠልጣኝም ሆነው አሳልፈዋል። በተጫዋችነት ዘመናቸው ቡድኑን በአምበልነት መርተዋል።
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም 15 ጊዜ ተሰልፈው ለመጫወት ችለዋል።
የተጫዋችነት ሕይወታቸውን ካጠናቀቁ በኋላም ይድነቃቸው ከእግር ኳሱ ዓለም አልራቁም።
የኢትዮጵያ 3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ስታዘጋጅ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ነበሩ።
በጥሎ ማለፍ መልኩ በተከናወነው ውድድር ላይ ብሔራዊ ቡድኑ ቱኒዚያን በማሸነፍ ለፍጻሜ ለመድረስ በቅቷል።
በፍጻሜው ግብፅን የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስቶ በተጨማሪ ሰዓት ባስቆጠራቸው ጎሎች 4 ለ 2 በማሸፍ የአፍሪካ ሻምፒዮን ሆነ።
ብሔራዊ ቡድኑ ይህንን ብቸኛ ድል ያስመዘገበው በይድነቃቸው የአሠልጣኝነት ዘመን ነው።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተመሠረተው በ1944 ዓ. ም. ነበር።
ይድነቃቸውም የመጀመሪያው ዋና ጸሐፊ በመሆን ተመርጠው ማገልገል የጀመሩት በዚሁ ጊዜ ነው።
ቀጣይ መዳረሻቸው ደግሞ አህጉራዊ ኮንፌዴሬሽን መመሥረት ሆነ።

የፎቶው ባለመብት, Tadele Yidnekatchew Tessema
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን የመመሥረት ጉዳይ በመጀመሪያ ላይ በፊፋ በኩል ድጋፍ አልተሰጠውም ነበር።
ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ሱዳን፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ካርቱም ላይ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን በ1957 መሠረቱ።
ኮንፌዴሬሽኑ በአፍሪካ የተመሠረተ የመጀመሪያው አህጉራዊ ተቋም ለመሆንም በቃ።
በምሥረታው ውስጥ የይድነቃቸው ሚና ጉልህ ነበር።
ዶ/ር አብድላዚዝ አብደላህ ሳሌም ኢሳ የካፍ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ሆነው ሲመረጡ፣ ይድነቃቸው የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመረጡ።
የካፋ መመሪያ ሲዘጋጅም ዋነኛ ሐሳብ አቅራቢ በመሆን ስማቸው የሚነሳው ይድነቃቸው እና የሱዳኑ አብደልራሂም ሻዳድ ነበሩ።
ይድነቃቸው እአአ ከ1957 እስከ 1972 ድረስ የካፍ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግለዋል።
በዚህ ብቻ ያልተወሰኑት ይድነቃቸው በ1965 አራተኛው የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ለመሆን በቅተዋል።
እአአ በ1972 የካፍ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡ ሲሆን፣ እስከ ኅልፈታቸው ማለትም እስከ 1987 ድረስ ይህንኑ ኃላፊነታቸው ሲወጡ ቆይተዋል።
በአጠቃላይ በፕሬዝዳንትነት አሥራ አምስት ዓመታትን አገልግለዋል። በካፍ የነበራቸው ሚና ደግሞ ከሰላሳ ዓመታት የዘለለ ነው።

የፎቶው ባለመብት, CAF
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የነበረውን የዘር መድልዎ በመጋፈጥም ግንባር ቀደምት ከነበሩት የካፍ ሰዎች መካከል ይድነቃቸው ይጠቃሳሉ።
ካፍ በ1954 ዓ. ም. ደቡብ አፍሪካን ከአባል አገርነት በማገድ የመጀመሪያው ስፖርታዊ ተቋም ሆነ።
ውሳኔው ግን በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። ፊፋ እና ዓለም ዓቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ይህንን ውሳኔ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ነው በሚል ተቃውመውት ነበር።
ደቡብ አፍሪካን ወደ ኮንፌዴሬሽኑ ለመመለስ ፊፋ ጥረት ማድረግ ቢጀምርም ይድነቃቸው እና ካፍ ግን አገሪቱን ከፊፋ አባልነት ጭምር እንድትታገድ መወትወት ቀጠሉ።
ይህ ጥረታቸው በ1957 ዓ. ም. በጃፓን ቶክዮ በተደረገው የፊፋ ጠቅላላ ጉባኤ ተቀባይነት አግኝቶ ደቡብ አፍሪካ ከፊፋ አባልትም እንድትሰናበት ተደረገ።
የፊፋ ባለሥልጣናት ግን በውሳኔው ደስተኞች አልነበሩም። በድብቅ ደቡብ አፍሪካን ያካተተ ኮንፈደሬሽን ለማቋቋም ኃላፊዎቹ ያደረጉት ጥረትም በነይድነቃቸው ከሸፈ።
እግር ኳስ ከዘር፣ ከቀለም እና ከሃይማኖት መድልዎ ነፃ እንዲሆንና ይህንን ያልተገበረ ማንኛውም አገር ከአባልነቱ እንዲሰረዝ የሚጠይቀው ሕግም ጸደቀ።
በኋላም ይድነቃቸው የፊፋ ሥራ አስፈፃሚ አባል በመሆን ተመርጠው አገልግለዋል።
በወቅቱ የአፍሪካ አገራት በዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የሚያመች ሁኔታ አልነበራቸውም።
ይህንን ተከትሎም አፍሪካ በዓለም ዋንጫ ወደማትወከልበት ደረጃ የሚወስድ ነው በሚል ቅሬታ ማቅረብ ጀመሩ።
ይድነቃቸው ተሰማ እና የአፍሪካ እግር ኳስ መሪዎች ከ1959ኙ የእንግሊዝ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ራሳቸውን አገለሉ
በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ለአፍሪካ አንድ ሙሉ ኮታ ካልተሰጣት በተሳትፎ እንደማይቀጥሉም በይፋ አስታወቁ።
የአፍሪካ ፌደሬሽኖች ራሳቸውን በማግለላቸው እያንዳንዳቸው 5000 ፍራንክ ቅጣት እንዲከፍሉ ፊፋ ወሰነ።
በኋላ ላይ ግን ውሳኔውን በመቀልበስ ለአፍሪካ አንድ የዓለም ዋንጫ ኮታ መደበ። ይህንን ዕድል በመጠቀም ሞሮኮ በ1963ቱ የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ በቃች።
ይድነቃቸው በካፍ ፕሬዝ ዳንትነት ባገለገሉባቸው 15 ዓመታት በርካታ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አሁንም ድረስ አሻራቸውን ማሳረፍ ችለዋል።
የመጀመሪያው የአፍሪካ የወጣቶች ዋንጫ እና የአፍሪካ የዋንጫ አሸናፊ ክለቦች ውድድር (አሁን የኮንፌዴሬሽኖች ዋንጫ የሚባለው) በይድነቃቸው ጠንሳሽነት የተጀመሩ ውድድሮች ናቸው።
የካፍ ዓመታዊ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ያደገውም በእርሳቸው አመራርነት ወቅት ነበር። በ1974ቱ የሊቢያ የአፍሪካ ዋንጫ የቴሌቪዥን ስርጭት መብት ታይቶ በማይታወቅ መጠን በመሸጡ ተቋሙ ከፍተኛ ገቢ አግኝቷል።

የፎቶው ባለመብት, EBC
አፍሪካ በ1971 ዓ. ም. በዓለም ዋንጫ ያላት ኮታ እንዲጨምር ጥያቄ አቀረበች።
ጥያቄውም በአብዛኛው የፊፋ አባላት ተቀባይነት በማግኘቱ ከ1974ቱ ከዓለም ዋንጫ ጀምሮ የአፍሪካ ኮታ ወደ 2 እንዲያድግ ተፈቀደ። በዚህ ውስጥ ይድነቃቸው ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
ይድነቃቸው የካፍ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት፣ በአፍሪካ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ የትምባሆ እና የአልኮል ማስታወቂያዎችን የሚከለክል ውሳኔ ተግባራዊ አድርገዋል።
ከእነዚህ ማስታወቂያዎች የሚገኘው ገንዘብ ከፍተኛ ቢሆንም ጉዳቱን ቀድመው በመረዳት የወሰኑት ውሳኔ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አትርፎላቸዋል።
ለዚህም ነው የዓለም ጤና ድርጅት የመጀመሪያውን "የትምባሆ አልባ ቀን ሽልማት" ለእርሳቸው እንዲሰጥ የወሰነው።
ከድርጅቱ እውቅና ያገኙ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የስፖርት ሰው ለመሆንም በቅተዋል።
በ1968 በአዲስ አበባ የጀመሩት የሥልጠና ፕሮጀክት በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት እንዲስፋፋ በማድረግ በሺህዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ዳኞች፣ አሠልጣኞች እና ሌሎች ባለሙያዎች እንዲሠለጥኑ አግዘዋል።
ይድነቃቸው የካፍ ዋና ጽሕፈት ቤትን ወደ አዲስ አበባ ለማዞር ጥረት ቢያደርጉም፤ ይህ ተደጋጋሚ ሙከራቸው ግን ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል።
አማርኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እና ጣሊያንኛ ቋንቋን አቀላጥፈው ይናገሩ ነበር።
አረብኛ እና ስዋሂሊ መማራቸውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ላስመዘገቡት ውጤት እንደረዳቸው ይነገራል።
"ይድነቃቸው ተሰማ፤ ዘላቂ፣ የተከበረ፣ እንዲሁም ጽኑ የሆነ ተቋም ለመገንባት እና የአፍሪካ ወጣቶችን ለመደገፍ ሠርተዋል" ሲል ለአስርት ዓመታት ያገለገሉት ካፍ ገልጿቸዋል።
ካፍ የመጀመሪያውን የወርቅ ደረጃ የኮንፌዴሬሽኑን የክብር ሜዳሊያ (Order of Merit) አበርክቶላቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Tadele Yidnekatchew Tessema
በ1979 ዓ. ም. በ65 ዓመታቸው ማለፋቸውን ተከትሎም የካፍ የክብር ፕሬዝዳንትነት ማዕረግን ሰጥቷቸዋል።
ዓለም አቀፉ የአግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ በበኩሉ እአአ በ1988 ከፍተኛው የሆነውን የወርቅ ደረጃ የክብር ሜዳሊያ (Order of Merit) ሸልሟቸዋል።
ይድነቃቸው የኢትዮጵያን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በቀጥታ በሬዲዮ በማስተላለፍም ይታወቃሉ።
የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል በመሆን ለማገልገልም በቅተዋል።
የ1988 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ዛምቢያ፣ አልጄሪያ እና ቱኒዚያን ፍላጎት ከማሳየት ባለፈ ወደ ከፍተኛ አለመግባባት የገቡበት ወቅት ነበር።
ይድነቃቸው እና አመራራቸው በከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሁኔታውን ለመፍታት ችለዋል። ውድድሩንም ሞሮኮ እንድታዘጋጅ አድርገዋል።
ይህንን ተከትሎም የሞሮኮ ንጉሥ ሐሰን ዳግማዊ በካዛብላንካ የሚገኘው የስፖርት ማዕከል በይድነቃቸው ስም እንዲሰየም ወሰኑ።
ዛሬም ድረስ በካዛብላንካ የሚገኘው ስታዲየም "ስታድ ተሰማ" ተብሎ ይጠራል። ስታዲየሙ የተለያዩ አገራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እያስተናገደ ይገኛል።



































