በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎች ከአሜሪካ ይልቅ ለቻይና እንደሚያደሉ ጥናት አሳየ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም ዙሪያ በበርካታ አገራት ውስጥ ሰዎች ከአሜሪካ ይልቅ ቻይናን በተመለከተ አዎንታዊ ምልከታ እንዳላቸው ፒው የተሰኘው የምርምር ማዕከል ያወጣው አዲስ ጥናት አመላከተ።
ተቋሙ በሚያደርጋቸው ጥናቶች እንዲህ ዓይነት ግኝት ላይ ሲደርስ ይህ የመጀመሪያው ነው።
መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ገለልተኛው ቲንክ ታንክ በጥናቱ እንዳሳየው፤ ለቻይና ያደላ ዕይታ ያለባቸው አገራት ብዛት ከፍተኛ ቁጥር ላይ ደርሷል። በአንጻሩ ሰዎች ለአሜሪካ ያላቸው ምልከታ የበለጠ የከፋ ሆኗል።
በጥናቱ ጥቅል ውጤት መሠረት፤ ተሳታፊዎች በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይም ሆነ በቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ላይ ያላቸው መተማመን ዝቅተኛ ነው። ነገር ግን ዢ ከትራምፕ የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል።
ግላዊ ነጻነትን ከማክበር አንጻር አሜሪካ ከቻይና የተሻለች ሆና ብትገኝም፤ ቤጂንግ ከአሜሪካ በተሻለ በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የማትገባ ተደርጋ ተወስዳለች።
'ፒው ሪሰርች ሴንተር' ከየካቲት እስከ ግንቦት ባለው ጊዜ ውስጥ ይህንን ጥናት ያከናወነው በ36 አገራት ውስጥ የሚገኙ ከ42 ሺህ በላይ ሰዎችን በማሳተፍ ነው።
የጥናቱ ተሳታፊዎች፤ ስለ ሁለቱ ልዕለ ኃያላን ያላቸውን ምልከታ እጅግ አዎንታዊ፣ በመጠኑ አዎንታዊ እንዲሁም በመጠኑ አሉታዊ እና በጣም አሉታዊ በሚሉት አማራጮች እንዲገልጹ ተጠይቀዋል።
ተቋሙ በጥናቱ ካሳተፋቸው 36 አገራት መከካል በ25 ያህሉ አገራት ውስጥ ከአሜሪካ ይልቅ ለቻይና ያደላ ዕይታ ያላቸው ሰዎች ቁጥር ከፍ ብሎ ተገኝቷል።
ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ ሰዎች ስለዓለም ልዕለ ኃያላን ያላቸውን ምልከታ ሲያጠና የቆየው የምርምር ማዕከሉ፤ በበርካታ አገራት ውስጥ ይህንን ዓይነት ውጤት ሲያገኝ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ከአጥኚዎቹ አንዱ የሆኑት ጆናታን ሹልማን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ የሥልጣን ዘመን መጠናቀቅ በኋላ በአውሮፓውያኑ 2008 እንዲሁም በ2017 በትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን መባቻ ላይ ለአሜሪካ አዎንታዊ ምልከታ ያላቸው ሰዎች ቁጥር አሽቆልቁሎ ነበር።
በእነዚያ ጊዜያትም ቢሆን ለቻይና በጎ ዕይታ ያላቸው ሰዎች ቁጥር ከአሜሪካ እኩል ወይም በመጠኑ ያነሰ እንደነበር ሹልማን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በከፍተኛ መጠን ምልከታቸው ወደ ቻይና ተቀይሮ ከታዩ አገራት መካከል ስፔን፣ ኢንዶኔዥያ፣ ጣሊያን፣ ግሪክ እና ካናዳ ይገኙበታል።
በዘንድሮው ጥናት አሁንም ለአሜሪካ ያደሉ ሆነው የቀጠሉት ስድስት አገራት ፖላንድ፣ ፊሊፒንስ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሕንድ፣ ጃፓን እና እስራኤል ናቸው። ከእነዚህ አገራት ውስጥ አብዛኛዎቹ የአሜሪካ የቅርብ አጋሮች ናቸው።
በሌላ በኩል በ20 አገራት ውስጥ ለአሜሪካ ያደላ ምልከታ ያላቸው ሰዎች አማካይ ቁጥር ባለፉት ዓመታት እየቀነሰ መጥቷል።ለቻይና በጎ ዕይታ ያላቸው ሰዎች አማካይ ብዛት ደግሞ እያደገ መጥቷል።
ከዚህ ቀደም ባልታየ መጠን ለቻይና ያደላ ምልከታ ከተመዘገበባቸው አገራት መካከል ጣሊያን፣ ስፔን፣ ኮሎምቢያ፣ ሜክሲኮ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ማሌዥያ፣ ናይጄሪያ እና ቱርክ ይጠቀሳሉ።
በአጠቃላይ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ለቻይና አዎንታዊ አመለካከት ሲኖራቸው፤ ሀብታም ሀገራት ግን ይበልጥ አሉታዊ ዕይታ እንደያዙ አጥኚዎቹ ደርሰውበታል።
ሲንጋፖር ከዚህ ተቃራኒ ሆና ተገኝታለች። በጥናቱ ከተካተቱ አገራት መካከል ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ቢኖራትም፤ በከፍተኛ መጠን ለቻይና ያደላ ምልከታ እንዳለ ጥናቱ አሳይቷል።















