"ከሞትንም አብረን ነው የምንሞተው"- በራየንኤር አየር መንገድ በረራ ላይ አንገቱ ተስቦ ሊወድቅ የነበረው መንገደኛ ባለቤት

ሁለት ጥንዶች ወደ ካሜራ እያዩ

የፎቶው ባለመብት, Facebook/Karovic Ljubisa

የምስሉ መግለጫ, ጥንዶቹ ከእረፍት እየተመለሱ እያለ ነው አደጋው የደረሰው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ባለፈው አርብ በራየንኤር አየር መንገድ በረራ ላይ በመስኮት አንገቱ ተስቦ ሊወድቅ የነበረውን ባለቤቷን እግር ይዛ የታደገችው መንገደኛ፤ "የቀኝ ትከሻው እና ራሱ ከአውሮፕላኑ ውጭ ነበሩ" ብላለች።

ሰቫትላና ግሪኮቪች ማክሲሞቪች ከባለቤቷ ልጁቢሳ ካሮቪች ጋር ከግሪክ ቴሳሎኒኪ ወደ ጀርመን ሚምንግን እየበረሩ እያለ አስደንጋጭ አደጋ ገጥሟቸዋል።

ሌሎች ሁለት መንገደኞች ለሁለት ደቂቃ ያህል ባለቤቷን ጎትተው አንገቱ እንዲመለስ ማገዛቸውን ለቢቢሲ ሰርቢያ ተናግራለች።

"በጋራ ጎትተን አስገባነው። ሙሉ ፊቱ ተበላሽቶ ነበር እና ከአፉ እና አፍንጫው ደም እየፈሰሰ ነበር።"

ለክስተቱ ወዲያው ምላሽ በመስጠት የባለቤቷን እግር እንደያዘች ኖቫ ለተባለ የሰርቢያ መገናኛ ብዙኃን ተናግራለች።

"ከሞትን አብረን ነው የምንሞተው ብዬ አሰብኩ" ብላለች።

ሰቫትላና ግሪኮቪች ማክሲሞቪች ለግሪክ መገናኛ ብዙኃን የአውሮፕላኑ የሞተር ክፍል የተሰበረ እንደሚመስል፤ ይህም አየር እንዲጠፋ እንዳደረገ ተናግራለች።

ሌሎች መንገደኞችም ፍንዳታ የመሰለ ድምፅ መስማታቸውን ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቤተሰቡ የተሰየሙ የቴክኒክ አማካሪ የአውሮፕላኑ የቀኝ ሞተር መስራት በማቆሙ አደጋው እንደጀመረ ጠቁመዋል። ይህም የአየር እጥረት ከማድረሱ በፊት ፍርስራሹ መስኮቱን እንደሰበረ ገልፀዋል።

ይህ ግምገማ በመርማሪዎች የተረጋገጠ አይደለም።

መንገደኞች አደጋው የደረሰበት ሠው የመቀመጫ ቀበቶውን አስሮ እንደነበረ እና ይህም አንገቱ እና ትከሻው ውጭ በነበረበት ወቅት ሌሎች መንገደኞች ጎትተው እንዲስቡት እንዳገዘ ተናግረዋል።

ሰቫትላና የ61 ዓመቱ ባለቤቷ "ከባድ ጉዳት እና ድንጋጤ ደርሶበታል" ብላለች።

"በሕይወት መትረፉ ለእኔ በጣም ወሳኝ ነው። . . .በተለይ እጁ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል እና ተቃጥሏል። መነጋገር አይችልም፤ ሙሉውን ሁነት አያስታውስም።"

"ስለ አውሮፕላን በሰማ ቁጥር መንቀጥቀጥ ይጀምራል" ስትል ባለቤቷ ስላለበት ሁኔታ ኢአርቲ ለተባለ የግሪክ መገናኛ ብዙኃን ተናግራለች።

"እኔም በጣም መጥፎ በሆነ ስነ ልቦናዊ ጭንቀት ውስጥ ነኝ። . . .ለሕይወታችን እፈራለሁ። አውሮፕላኑ ይወድቃል ብዬ ፈርቼ ነበር" ስትልም አክላለች።

ሰቫትላና ግሪኮቪች ማክሲሞቪች ስለ አደጋው ማሰብ ማቆም እንዳልቻለችም ተናግራለች።

"አሁን ጥያቄው ከዚህ በኋላ ዳግም አውሮፕላን ውስጥ እንገባ ይሆን የሚለው ነው።"

ራየንኤር በድንገት ከፍታውን ቀንሶ ወደ መሬት ሲወርድ ለ10 ደቂቃዎች ያህል አየር ላይ እንደነበር የክትትል መረጃዎች አሳይተዋል።

ባለፈው አርብ ንብረትነቱ የአየርላንድ አየር መንገድ የሆነው ራየንኤር ባወጣው መግለጫው አውሮፕላኑ "ከመነሳቱ ከአጭር ጊዜ በኋላ በረራ ላይ የመንገደኛ መስኮት ከቦታው በመነሳቱ" እንደተመለሰ አስታውቋል።

"አውሮፕላኑ በመደበኛነት አርፏል እና መንገደኞችም ወደ ተርሚናል ተመልሰዋል። አንድ መንገደኛ የሕክምና እርዳታ ጠይቀው እንዲያገኙ ተደርጓል" ብሏል።

አውሮፕላኑ 18 ዓመት እድሜ ያለው እንደሆነ የታመነ ሲሆን ራየንኤር በሚል አርማ የሚበር በማልታ ኤር ስር የሚገኝ ነው።

የአደጋው ምክንያትን ለማወቅ እየተደረገ ያለው ምርመራ እንደቀጠለ የግሪክ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

አውሮፕላኑ አሜሪካ ሰራሹ ቦይንግ 737-800 በመሆኑ እና አደጋው በሰሜን መቄዶኒያ የአየር ክልል በመድረሱ ምርመራውን የበርካታ አገራት የአቪየሽን ባለሥልጣናት መርማሪዎች እያገዙ ነው።