ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአርጀንቲናው ፕሬዝዳንት የብራዚሉን ፕሬዝዳንት 'ሌባ' ማለታቸው ውዝግብ አስነሳ
የአርጀንቲና ፕሬዝዳንት ሀቪየር ሚሌይ የብራዚሉን ፕሬዝዳንት "ሌባ" እና "የተፈረደበት ወንጀለኛ" ማለታቸው በሁለቱ አገራት መካከል ውዝግብ አስነስቷል። ብራዚልም በቦነስ አይረስ የሚገኙ አምባሳደሯን ጠርታለች።
ትናንት እሑድ በሳዎ ፖሎ በተካሄደ ሰልፍ ላይ ለቀኝ ዘመሙ ብራዚላዊ እጩ ፍላቪዮ ቦልሶናሮ ንቅናቄ ተደርጓል። በዚህ ንቅናቄ ላይ የተገኙት የአርጀንቲና ፕሬዝዳንትም የብራዚልን ፕሬዝዳንት ወርፈዋል።
የፊታችን ጥቅምት በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ የሚወዳደሩትን ቦልሶናሮ ሲደግፉም ታይተዋል።
የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሳልቪቫን በስም ባይጠሯቸውም "የብራዚል ፕሬዝዳንት" ብለው ንግግራቸውን አሰምተዋል።
ለቦልሶናሮ ጎን ሆነው ባደረጉት ንግግር "ሉላን ማስቆም የሚችለው እሱ ብቻ ነው" ብለዋል።
የብራዚል ዲፕሎማቶች በሰጡት አስተያየት የአርጀንቲናው ፕሬዝዳንት የብራዚሉን መሪ፣ ሕዝቡን እና የአገሪቱን ዲሞክራሲ "ሰድበዋል" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሉላ "ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት መምራት እንደሚቀጥሉ" ትናንት ተናግረዋል።
"በብራዚል ማንም በማይገባው ቦታ መግባቱን አንቀበልም" ብለዋል።
ኤኤፍፒ እንደዘገበው፤ በአርጀንቲና የብራዚል አምባሳደር ሁሊዮ ቢቴሊ እሑድ አልያም ሰኞ ወደ አገራቸው ይመለሳሉ።
ፍላቪዮ ቦልሶናሮ የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት ሀቪየር ቦልሶናሮ ልጅ ናቸው።
የቀድሞው የብራዚል ፕሬዚዳንት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በማድረግ የተፈረደባቸውን የ27 ዓመት የእስር ቅጣት እንዲጀምሩ እንደተወሰነባቸው ይታወሳል።
ሉላ ምርጫውን ካሸነፉ በኋላ ቦልሶናሮ ሥልጣን ላለማስረከብ በመሞከራቸው ነበር የተከሰሱት።
በቦልሶናሮ ላይ ብይን የሰጡት የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አሌክሳንድሬ ደ ሞራዬስ ናቸው።
የአርጀንቲናው ፕሬዝዳንት ዳኛውን "መላጣ ቆሻሻ" ሲሉ ተሳድበዋል።
የአርጀንቲናው ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ በቁል እስር ላይ ስላሉ ለመጎብኘት ያቀረቡትን ጥያቄ ዳኛው ውድቅ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
በአውሮፓውያኑ 2018 ሉላ በመጠነ ሰፊ ሙስና እና ጉቦ የመቀበል ቅሌት የ12 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው ነበር።
ሆኖም 18 ወራት ታስረው ተፈትተዋል።
በ2021 የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሉላ ላይ የተላለፈውን ብይን ውድቅ አድርጓል።
በቀጣዩ ዓመት በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በጠባብ የድምጽ ልዩነት (50.9%) ሥልጣን ላይ የነበሩትን ቀኝ ዘመሙ ቦልሶናሮን አሸንፈዋል።