ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በትግራይ ከተሞች እየተካሄደ ያለው ተከታታይ ስብሰባ ስለ ፖለቲካዊው ውጥረት ምን ይነግረናል?
በቅርቡ በትግራይ ክልል የተካሄዱት ሕዝባዊ ስብሰባዎች እና መግለጫዎች ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለውን ውጥረት ሊያባብሱና ሁኔታውን ወደ ጦርነት ሊገፉ ይችላሉ የሚል ስጋት ፈጥረዋል።
'እምቢኝ ለብሔር እልቂት' በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ከተሞች እየተካሄዱ ያሉት እነዚህ ስብሰባዎች የሚመሩት በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ነው።
በክልሉ እነዚህ ስብሰባዎች በዘመቻ መልክ እየተካሄዱ የሚገኙት በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ያለው ፖለቲካዊ ውጥረት እየተካረረ በመጣበት ወቅት ነው።
አንዳንድ ታዛቢዎች የህወሓት መግለጫዎች እና ስብሰባዎች ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ያለውን ውጥረት ወደ ሌላ ጽንፍ የሚያሸጋግሩ ይሆናሉ ብለው ይፈራሉ። ሌሎች ደግሞ ከነዋሪዎች ጋር መመካከር አዎንታዊ ውጤት ሊያስገኝ እና ወደ መፍትሄ ሊያመራ እንደሚችል ተስፋ ያደርጋሉ።
በካናዳ ካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑትን ፕሮፌሰር ጌታቸው አሰፋ "በሚያሳዝን ሁኔታ ወደ ጦርነት እንደተቃረብን እንደሆነ ይሰማኛል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የህወሓት መሪዎች በሚሰጡት መግለጫዎች እና ንግግሮች ውስጥ "በጄኖሳይዳል ስርአት መቃብር ላይ" የሚለውን ሐረግ መጠቀማቸው እንዲሁም ከዚህ በፊት በነበረው ጦርነት ልጆቻቸውን ያጡ ቤተሰቦች የቀሩ ልጆቻቸውን ለጦርነት እንዲያቀርቡ የሚያሳምን እና ሚገፋፋ ይመስላል ብለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት ሁለት ወይም ሦስት ቀናት ውስጥ ከማዕከላዊው መንግሥት ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መከፈቱን አስተውያለው ይላሉ።
"ስለዚህ የመጨረሻ የሚመስል ሁኔታን እየተመለከትን ነው፤ ነገር ግን ምናልባት [ጦርነት የሚቀርበት] ዕድል የለም ማለት አልፈልግም" ብለዋል።
በክልሉ ያለውን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት አቶ ጌታቸው እንደ አዎንታዊ ዕድል የሚያዩት አንዱ እርምጃ ከአሜሪካ መንግሥት እና ከአውሮፓ ኅብረት የሚመጣን ግፊት እና የሰላም አውርዱ ጫና ነው።
የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ባለፈው ሳምንት መቀለ ከተማን ጎብኝተው ከህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተነጋግረዋል። አምባሳደሩ በቅርቡ ወደ መቀለ እንደሚመለሱም ተገልጾ ነበር።
ይህ ለፕሮፌሰር ጌታቸው አዎንታዊ አካሄድ ቢሆንም፣ ለህወሓት ግን ሌላ የተሳሳተ መልዕክት እያስተላለፈ ሊሆን ይችላል ብለው ይሰጋሉ።
"ይህ በሁለት መንገድ ሊታይ ይችላል፤ በአንድ በኩል ወደ ጦርነቱ መጠጋት እንዳለ ያመለክታል። ሁለተኛ ነገር ደግሞ እየተካሄዱ ካሉት ስብሰባዎች እንደምንሰማው 'የቀድሞ ምክር ቤታችንን መመለሳችን እና ኃይላችን ማሳየታች እየተመላለሱ እንዲያዩን አድርጓል' የሚል ፕሮፖጋንዳ እየተጠቀሙ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።
ስለዚህ ይህ ጦርነቱን ለማባባስ እና ጫና ለመፍጠር ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ "እስካሁን ስንማው የነበረ ከ[የኤርትራ መንግሥት]፣ ከፋኖ እና ከኦሮሞ ነፃ አውጪ ጦር ጋር ያለውን ግንኙነት ገሃድ እያደረጉት ያሉ ይመስላሉ፡" ብለዋል።
"ስለዚህ እንደ ተስፋ ምናልባት የዲፕሎማሲ ስኬትን ለማሳደግ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለኝ፤ ነገር ግን በተለይም ከአራት ኪሎ የሚሰማው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ፣ ጦርነቱ በጥቂት ቀናት ወይ ሳምንታት ውስጥ ሊጀመር ይችላል፤ አቀይርም።"
በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት እና ህወሃትን በመደገፍ አስተያየቶች በመስጠት የሚታወቁት አቶ አብርሃ ተክሉ ስብሰባው "አካታች" እንደነበር ተናግረዋል።
"የመድረኩ ዓላማ በትግራይ እና በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ማስረዳት እና ለወደፊት የፖለቲካ እና ወታደራዊ እርምጃዎች መዘጋጀት ነው" ብለዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ ጦርነቱ አላቆመም ሲሉ የሚከራከሩት አቶ አብርሃ፣ በክልሉ ላይ የተጣሉትን የበጀት፣ የነዳጅ እና የደመወዝ ክልከላዎች እና በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ስር የሚገኘውን የምዕራብ ትግራይ ይዞታዎች ጉዳይን እንደ ማስረጃ ይጠቅሳሉ።
ምንጮች ለቢቢሲ ትግርኛ እንደገለጹት በእነዚህ የህዝብ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙት አብዛኛዎቹ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ናቸው።
አቶ አብርሃ ውጥረቱ እየተባባሰ የመጣ ይመስላል ከሚለው የፕሮፌሰር ጌታቸው ትንተና ጋር ይስማማሉ።
በክልሉ ስለሚካሄደው ወታደራዊ ስልጠና እና ምልመላ ሲጠየቁ ደግሞ "ይህ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች ሳያሳምኑ የግዳጅ እርምጃ የወሰዱ አሉ፤ ይህ ድርጊት ያለውን መንፈስ የሚረብሽ እንደነበር ግልጽ ነው" ሲሉ ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ፣ ይህ በትግራይ ያልተለመደ እና ከላይ አቅጣጫ ያልተሰጠው ነው ሲሉ ይከራከራሉ። የሰሞኑ ውይይት ዓላማ ደግሞ በጉዳዩ ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል።
የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በዚህ ሳምንት ባደረጉት ንግግር ክልሉ ራሱን ከኢትዮጵያ መንግሥት ለመከላከል ከሌሎች ኃይሎች ጋር ጥምረት መፍጠሩን ገልጸዋል።
በንግግራቸው የጠቀሷቸውን ሌሎች ኃይሎችን በስም ያልዘረዘሩ ሲሆን የአገር ውስጥ ወይም የውጭ ኃይሎች ስለመሆናቸውም አልተገለጸም።
ይሁን እንጂ "የጋራ ጠላታችን" ብለዉ የጠሩት የኢትዮጵያን መንግሥትን ሲዋጉ የቆዩ ቡድኖች ናቸው ብለዋል።
"ዛሬ እንደበፊቱ ብቻችንን አይደለንም፤ ብዙ ወዳጆች አሉን" ብለዋል። ይህም ከኤርትራ ጋር እንደፈጠሩ የሚገለጸውን 'ጽምዶ' የሚያመለክት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
"ብልጽግና ከአሁን በኋላ ትግራይን ብቻ አይገጥምም። አገዛዙን እንደ ስጋት የሚቆጥሩ ሌሎች ኃይሎች አሉ። ምንም እንኳን በራሳችን ብንተማመንም፣ ይህንን ስርዓት ለማስወገድ የሚፈልጉ አጋሮች አሉን" ብለዋል።
በንግግራቸውም የኢትዮጵያ መንግሥት ቀውሱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ እንዳልሆነ በማንሳት ወቅሰዋል።
"ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ካልቻልን በኃይል መፍታት አለብን። ለዚህም ሠራዊታችንን በማጠናከር አቅማችንን እንገነባለን" ሲሉ ተደምጠዋል።
ከዚህ ቀደም ህወሓት የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶሪያን ስምምነት በመጣስ በባንክ፣ በነዳጅ አቅርቦት፣ በበጀት፣ በመድኃኒት እና በሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶች ገደቦችን ጥሏል የሚል ክስ ሲያሰማ ቆይቷል።
መንግሥት ህወሓት ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለጦርነት እየተዘጋጀ ነው ሲል ወንጅሏል።
ከወደብ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተቃረነው የኤርትራ መንግሥት ግን ክሱን ውድቅ አድርጎታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሐምሌ 7/2018 ዓ.ም. በተካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ መዝጊያ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ "ህወሓትም ጭምር ቀልብ ከገዛ. . . ለመነጋገር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።
"በትግራይ ክልል ጦርነቱ እንዲነሳ ሰፊ ፍላጎት አለ፤ እምቢ ያልንበት ምክንያት ትርፍ የለውም ብለን ነው" ሲሉም ተናግረዋል።