ቀጥታ, ኢራን ከአሸማጋዮች የሰላም እቅድ እንደቀረበላት አስታወቀች

አሜሪካ እና ኢራንን በድጋሚ ወደ ተኩስ አቁም ለመመለስ ያቀዱት አሸማጋዮች አዲስ የሰላም እቅድ ማቅረባቸውን ቴህራን አስታወቀች። አሸማጋይ አገራት የ10 ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቅ የሰላም እቅድ ማቅረባቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. አንዲ በርንሃም የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ

    አንዲ በርንሃም በፈቃዳቸው ከሥልጣን የለቀቁትን የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ተክተው የአገሪቱ መሪ ሆኑ።

    የግሬተር ማንችስተር ከንቲባ የነበሩት በርንሃም፣ ዩናይትድ ኪንደግም ለመምራት በአምስት ዓመታት ውስጥ የተሾሙ ስድተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል። በአስር ዓመት ውስጥ ደግሞ ሰባተኛው የአገሪቱ መሪ ናቸው።

    አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመጀመሪያ ንግግራቸው፤ “አገራችን ውስጥ የሚታየው የጎዳና አዳር እንዲያበቃ [አደርጋለሁ]” ብለዋል።

    ይህንን ለማስፈጸምም በአምስት ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ 340 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚመደብ ተገልጿል።

    በዚህ ገንዘብ አማካኝነት 1,200 ቤቶች እንደሚገነቡ እንዲሁም በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ለ3,000 ሰዎች “ከፍተኛ ድጋፍ” እንደሚደረግ ጽሕፈት ቤታቸው አስታውቋል።

    በርንሃም፤ መንግሥታቸው “ለሰዎች ውድቀት ከመክፈል ይልቅ፣ ስኬታቸው ላይ ኢንቨስት” እንዲያደርግ እንደሚፈልጉ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

    በተያዘው 2026 መጨረሻም አገሪቱ የምትመራበት አዲስ የ10 ዓመት ዕቅድ ይፋ እንደሚደረግ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "የሕይወት መሠረታዊ ፍላጎቶችን በሕዝብ ቁጥጥር ስር ማድረግ" የሚያስችል ኢኮኖሚ እንደሚገነቡም ተናግረዋል።

    ከአውሮፓውያን 2016 ወዲህ የተሾሙ ሰባተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን በደንብ እንደሚገነዘቡ በመጥቀስም፤ “መለስ ብሎ መመልከቻ እና አዲስ ውሳኔ” ላይ መድረሻ ጊዜ እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል። ብሪታኒያ መረጋጋት ማግኘት እንዳለባትም በአጽንኦት አንስተዋል።

    ፖለቲከኞች “በበቂ ሁኔታ ጥሩ አልነበሩም” በማለት የተቹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተሻለ ለመሆን ቃል ገብተዋል። ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ ያልታዩ ከፍተኛ ለውጦችን እንደያደርጉም ተናግረዋል።

  2. ሩሲያ በጭነት መርከብ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 10 ሰዎች ተገደሉ

    ሩሲያ፣ ወደ ዩክሬኗ ከተማ ኦዴሳ ሲጓዝ በነበረ የጭነት መርከብ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 10 ሰዎች ተገደሉ።

    ዩክሬን አየር ኃይል እንደገለጸው፣ በጊኒ ቢሳው ሰንደቅ ዓላማ የሚንቀሳቀሰው መርከብ በሩሲያ የክሩዝ ሚሳዔሎች የተመታው ትናንት እሁድ ነው። የደረሰው ጥቃት እሳት አስነስቷል።

    ከእሁድ ምሽት አንስቶ መርከቡ ላይ የነበሩ ሰዎችን ለመታደግ እና ለማግኘት የነፍስ አድን ሥራ እየተከናወነ ነው። የዩክሬን የባሕር ወደቦች ባለሥልጣን ሰኞ ጠዋት ይፋ ባደረገው መረጃ፤ ዘጠኝ ባሕረተኞች እንዲሁም ከካፒቴኖቹ አንዱ መገደላቸውን አስታውቋል።

    ባለፉት ሳምንታት ኦዴሳ ግዛት ተከታታይ ጥቃቶችን አስተናግዷል። ሩሲያ ሐምሌ ላይ ብቻ በግዛቱ ላይ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች 28 ሰዎች መገደላቸውን የግዛቱ ዋና አስተዳዳሪ ኦሌህ ኪፐር ሰኞ ዕለት ለዩክሬን ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

    ሩሲያ በጥቁር ባሕር ላይ የሚጓዙ የጭነት መርከቦች ላይ የምትፈጽማቸው ጥቃቶችን ጨምረዋል።

    ከእነዚህ ጥቃቶች ውስጥ ብዙ ሰዎች የሞቱበት፣ እሁድ ዕለት በጊኒ ቢሳው ሰንደቅ ዓላማ የሚንቀሳቀሰው መርከብ ላይ የተፈጸመው ነው።

    ዓለም አቀፍ ባሕርተኞችን ይዘው በአብዛኛው በውጭ ሰንደቅ ዓላማ ሥር የሚንቀሳቀሱት እነዚህ የጭነት መርከቦች የሚጓዙት፣ ዩክሩን በቀራት ብቸኛ የኤክስፖርት ኮሪደር በኩል ነው። በሮማኒያ እና ቡልጋሪያ የባሕር ዳርቻዎች በኩል ከዩክሬን ወደ ቱርክ ያጓጉዛሉ።

    የሩሲያ ሙሉ ወረራ ከተጀመረ አንስቶ ላለፈው ከአራት ዓመት ተኩል በላይ የሚሆን ጊዜ በጥቁር ባሕር ላይ የሚደረገው ውጊያ በአብዛኛው አሸናፊ የነበረበት አይደለም።

    የሩሲያ ጦር አብዛኛውን የባሕር ዳርቻ በመቆጣጠሩ የዩክሬን መርከቦች በኦዴሳ ዙሪያ ወዳሉ አካባቢዎች ርቀው መጓዝ አይችሉም። ይሁን እንጂ ዩክሬን የምትፈጽማቸው የድሮን ጥቃቶች ሩሲያ ወታደራዊ አቅሟን በጥቁር ባሕር ምሥራቃዊ ክፍል ከሚገኙ የባሕር ኃይል ካምፖች እንዳታንቀሳቅስ አድርጓታል።

    ሩሲያ አሁን በዚህ ባሕር ላይ የምትፈጽመው ጥቃት ያጠናከረችው፤ የውጭ አገር ኩባንያዎች የዩክሬን ምርቶችን እንዳይገዙ እና የጥቁር ባሕር መተላለፊያን እንዳይጠቀሙ ለማድረግ እንደሆነ ይታመናል።

  3. ኢራን ከአሸማጋዮች የሰላም ዕቅድ እንደቀረበላት አስታወቀች

    አሜሪካ እና ኢራንን በድጋሚ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ለመመለስ ያቀዱት አሸማጋዮች፣ አዲስ የሰላም ዕቅድ ማቅረባቸውን ቴህራን አስታወቀች።

    ሰኔ ላይ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራመው የነበሩት ሁለቱ አገራት፣ ላለፉት ሁለት ሳምንት ገደማ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ከባድ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ስምምነቱ አብቅቷል ብለዋል።

    ይህንን ስምምነት ዳግም ለመመለስ ያቀዱት አሸማጋይ አገራት የ10 ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቅ የሰላም ዕቅድ ማቅረባቸውን ዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ዛሬ ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀዋል። አሸማጋዮች ያዘጋጁትን ዕቅድ ለኢራን እንዳሳወቁ ቃል አቀባዩ አረጋግጠዋል።

    “በአሸማጋዮች ስለዘተጋጁት ዕቅዶች ገለጻ ተደርጎል፤ ዕቅዱም ደርሶናል። ነገር ግን ለአሁኑ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ባንገባ ይሻላል” ሲሉ ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    ባለፉት ቀናት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፤ “በአንዳንድ አሸማጋዮች የቀረቡ ዕቅዶች ለኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መድረሳቸው የተረጋገጠ ነው” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደፊት ለመደራደር የሚጠይቁ ከሆነ የኢራን ምላሽ ምን እንደሚሆንም ጥያቄ የቀረበላቸው ቃል አቀባዩ ኢስማኤል ባጋይ፣ “ዲፕሎማሲ ወይም ጦርነት” የሚል አማራጭ ለኢራን “ጠቃሚ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

    “ራስን መከላከል ከዲፕሎማሲ ጋር አይጣጣምም ብሎ ማሰብ ትክክለኛ አመክንዮ አይደለም። [የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ] ሰይድ አባስ አራግቺ የሚያከናውኑት ሥራ እና [የመከላከያ ሚኒስትሩ] ሰይድ መጂድ የሚፈጽሙት ተግባር ተመሳሳይ ግብ የሚያሳኩ ናቸው” ብለዋል።

    ባለፈው ሳምንት በመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት ላይ የነበሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፤ ከጉዟቸው ሲመለሱ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ዋሽንግተን “አሁንም ከኢራን ጋር ለሚደረግ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ በሯ ክፍት” መሆኑን ተናግረው ነበር።

    “ሁሌም ለዲፕሎማሲ ክፍት የሆንን ይመስለኛል። [መፍትሔው ግን] እውነተኛ መሆን አለበት። ልንገዛበት ፈቃደኛ የምንሆነው መሆን አለበት” ብለዋል።

    ኢራን ሰኔ ላይ ለተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት እንዳልተገዛች በመጥቀስ የከሰሱት ሩቢዮ፤ ሆርሙዝ ክፍት መሆን እንደነበረበት እንዲሁም በወሽመጡ የሚጓዙ መርከቦች ከጥቃት እና ከክፍያ ነጻ መሆን እንደነበረባቸው ገልጸዋል።

    አሜሪካ ለዲፕሎማሲ ክፍት ስለመሆኗ የተነሳላቸው የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ፣ “አሜሪካ ዲፕሎማሲ የምትለው ማስገደድ፣ ማስፈራራት፣ ዛቻ እና ማዕቀብ ነው” በማለት ተችተዋል።

  4. አሜሪካ ወሳኝ የኢራን የነዳጅ ዘይት ማዕከል የሆነችውን ደሴት ለመቆጣጠር እንዳታስብ ቴህራን አስጠነቀቀች

    አሜሪካ ወሳኟን የኢራን የነዳጅ እና የጋዝ መተላለፊያ ደሴት ኻርግ ለመቆጣጠር ጭራሽ እንዳታስብ እና ወረራ ለመፈጸም የምትሞክር ከሆነ ከባድ ምላሽ እንደሚጠብቃት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስጠነቀቀ።

    አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈጽመው ጥቃት በቀጠለበት እና ኢራን የአጸፋ ጥቃት እርምጃ በአጎራባች አገራት ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ እየወሰደች ባለበት በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ የኢራንን ግዛት የምትይዝ ከሆነ ጦርነቱ ይባባሳል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

    ከዚህ ቀደም ዶናልድ ትራምፕ በደቡባዊ ኢራን የምትገኘውን ኻርግ ደሴት የመቆጣጠር ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረው የነበረ ሲሆን፣ ግጭቱ በተባባሰበት ጊዜ አሜሪካ ይህንን ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ ኢራን ራሷን እንደምትከላከል አስታውቃለች።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ እንደተናገሩት “እንዲህ ያለው ጀብደኝነት ከባድ መዘዝን ያስከትላል” ሲሉ አሜሪካን አስጠንቅቀዋል።

    ጨምረውም አሜሪካ እግረኛ ጦሯን አሰማርታ ወረራ የምትፈጽም ከሆነ የአገሪቱ መሪዎች “አቀባበል ሊያደርጉላቸው ደቂቃዎችን እየቆጠሩ ነው” በማለት የአገራቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።

    የኢራን የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪ ዋነኛ ማዕከል የሆነችው ኻርግ ደሴት ከኢራን የባሕር ዳርቻ በ55 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

    ከወራት በፊት ጦርነቱ በተባባሰበት ጊዜ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደሴቱቱን በመቆጣጠር የኢራንን የነዳጅ ምርት በእጃቸው እንደሚያስገቡ በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደነበር ይታወሳል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ንግግር ለመጀመር በአሸማጋዮች በኩል የዲፕሎማሲያዊ መልዕክት ልውውጥ እየተካሄደ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

  5. ኢራን ላይ አዲስ ጥቃት የተፈፀመው ለተገደሉ አሜሪካውያን ወታደሮች ‘ክብር’ እንደሆነ ትራምፕ ተናገሩ

    ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ “ከባድ ጥቃት” እንደደረሰ እና ይህም ሰሞኑን ለተገደሉ ሦስት አሜሪካውያን ወታደሮች “ክብር” ሲባል የተፈፀመ እንደሆነ ተናገሩ።

    ሦስቱ ወታደሮች የተገደሉት ኢራን በዮርዳኖስ እና በኢራቅ በፈፀመቻቸው ጥቃቶች ነው።

    ጥቃቱ ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት እንደቀጠለ እና ትናንት ምሽት አዲስ ጥቃት እንደተከፈተ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ገልጿል።

    በመላው ኢራንም ከፍተኛ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።

    ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል እንደዘገበው አሜሪካ በፈፀመቻቸው ጥቃቶች ታብሪዝ፣ ቻባሃር፣ ኮናራክ፣ ባንዳር ባንዳር ማህሻህር እና ባንዳር ኢማም ኻሜኒን ጨምሮ በርካታ ከተሞች ተመትተዋል።

    በሌላ በኩል ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ወሽመጡን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ፍንዳታ እንዳጋጠማቸው የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ዘብ፣ መርከቦቹ “ደኅንነቱ ባልተጠበቀ እና አደገኛ በሆነው ደቡባዊ መስመር እየተጓዙ ሳሉ ፍንዳታ አጋጥሟቸዋል” ብሏል።

    ሴንትኮም ግን ይህን አስተባብሏል።

    አሜሪካ ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በመርከቦች ላይ የምትፈፅመውን ይህንን ጥቃት ለማስቆም “ወታደራዊ ሥፍራዎችን እና የመገናኛ ኔትዎርኮችን” ዒላማ እንዳደረገች ገልጻለች።

    ኢራን በበኩሏ ለጥቃቱ በሶሪያ ድንገተኛ ጥቃት በመፈፀም እና በዮርዳኖስ አቃባ አየር ማረፊያ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላንን ዒላማ በማድረግ አፀፋ መስጠቷን ገልጻለች።

    በቀጠናው ያለው ግጭት ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን የኩዌት ወታደራዊ ኃይል የኢራንን የድሮን ጥቃት አክሽፌያለሁ ብሏል።

  6. ኢራን በኩዌት እና በባህሬን የሚገኙ የአሜሪካ ይዞታዎችን መምታቷን አስታወቀች

    አሜሪካ በኢራን ላይ ለተከታታይ ዘጠነኛ ቀን ጥቃት መፈጸሟን ካስታወቀች በኋላ የኢራን አብዮታዊ ዘብ በኩዌት እና በባህሬን ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎችን መምታቱን አስታወቀ።

    ዘቡ ባወጣው መግለጫ በአሜሪካ ሠራዊት ይዞታ ላይ በፈጸመው የአጸፋ የድሮን ጥቃት “የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ የራዳር ሥርዓትን” ጨምሮ የተለያዩ ዒላማዎችን ማጥቃቱን እና “የጠላት የራዳር ሥርዓትን ሙሉ ለሙሉ” ማውደሙን ገልጿል።

    ጨምሮም እዚያው ኩዌት ውስጥ አሊ አል-ሳሌም ጦር ሰፈር ላይ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት የድሮኖች መጠለያን እና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ዒላማ ማድረጉን አመልክቷል።

    ዛሬ ማለዳ ኢራን በአካባቢው አገራት ውስጥ ያሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ በማድረግ ጥቃት መፈጸሟን የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ሲሆን ኩዌት እና ባህሬን ለነዋሪዎቻቸው ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል።

    የባሕሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እየተፈጸመ ካለው ጥቃት አንጻር ሕዝቡ “ተረጋግቶ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጥቃት መከላከያ ቦታ እንዲሸሸግ” አሳስቧል።

    የኩዌት ጦር ሠራዊትም ከኢራን በኩል የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶችን ለማክሸፍ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቆ፤ በአገሪቱ ውስጥ ከባድ የፍንዳታ ድምጽ የተሰማው ጥቃቱን ለማክሸፍ በሚወሰድ እርምጃ ምክንያት መሆኑን ለሕዝቡ አስታውቋል።

    መልሶ ካገረሸ ሳምንት ባለፈው የአሜሪካ እና የኢራን ጦርነት አሜሪካ በተከታታይ ዙር በኢራን ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎችን መምታቷን ስታስታውቅ፣ ኢራን ደግሞ በምላሹ በኩዌት እና ባህሬን የሚገኙ የአሜሪካ ይዞታዎችን ማጥቃቷን እየገለጸች ነው።

    የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ ሌሊት ላይ ዘጠነኛ ዙር ጥቃት መፈጸሙን የገለጸ ሲሆን፣ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ደግሞ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ዘግበዋል።

  7. ኢራን በሰሜን ኢራቅ በፈጸመችው ጥቃት የአሜሪካ ወታደር ተገደለ

    ኢራን በሰሜን ኢራቅ በፈጸመችው ጥቃት አንድ የአሜሪካ ወታደር እንደተገደለ እና ሌላ ወታደር እንደቆሰለ የአገሪቱ ማዕከላዊ ዕዝ አስታወቀ።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እንደገለጸው፤ ወታደሩ የተገደለው ተመትቶ የወደቀ የኢራን ድሮንን “ለማፈንዳት በተደረገ ሙከራ” ወቅት ነው።

    ሌሎች ብዙ የአሜሪካ ወታደሮች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተገልጿል።

    ኢራን እና አሜሪካ ለተከታታይ ስምንት ቀናት የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

    ባለፉት ቀናት ሁለቱም ወገኖች መሠረተ ልማቶች ላይ በደረሱ ጥቃቶች አንዳቸው ሌላቸውን ሲከስሱ ቆይተዋል።

    ዋሽንግተን በኢራን ወደቦች ላይ እገዳ ስትጥል ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታለች።

    ኢራን በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ቀጥላለች።

    የአሜሪካ ጦር እንዳለው፤ በኢራን ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ “አገሪቱ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት የምታደርስበትን አቅም ለማዳከም” ያለመ ነው።

    ኢራን በዮርዳኖስ ባደረሰችው ጥቀት ሁለት የአሜሪካ ወታደሮች ሲገደሉ አንድ ወታደር የደረሰበት እንዳልታወቀ መገለጹ ይታወሳል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በዮርዳኖስ ላደረሰው ጥቃት “በጽኑ እንደሚቀጣም” አክሏል።

    እስካሁን ድረስ የተገደሉ የአሜሪካ ወታደሮች ቁጥር 17 ደርሷል።