በአንድ ወር ወደ 100 የሚጠጉ የአሜሪካ ወታደሮች በኢራን ጥቃት መጎዳታቸውን የዋሽንግተን ባለሥልጣናት ተናገሩ
ኢራን በዚህ ወር በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ላይ በፈፀመቻቸው በርካታ የአየር ጥቃቶች 100 የሚጠጉ የአሜሪካ ሠራዊት አባላት ጉዳት እንደደረሰባቸው የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ።
የፔንታጎን ኃላፊ ቃል አቀባይ ሲን ፓርኔል የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ በላኩት መግለጫ ቁጥሩን ያረጋገጡ ሲሆን ከሰኔ መጨረሻ ወዲህ 100 የሚሆኑ ሠራተኞቹ የተለያየ መጠን ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።
አብዛኛው ጉዳት ቀላል መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ 96 በመቶ የሚሆኑት ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰዋል ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት ብቻ በርካታ የአሜሪካ ወታደራዊ ሠራተኞች በዮርዳኖስ የጦር ሠፈር መጎዳታቸው ተዘግቧል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ሁለት የአሜሪ ካወታደሮች በዮርዳኖስ በሚገኝ የጦር ሠፈር መገደላቸው እና ሌላ ወታደር የት እንደገባ አለመታወቁን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ገልጿል።
ሌላ ወታደር ደግሞ ኢራቅ ውስጥ ተገድሏል።
በአሁን ወቅት በርካታ ወታደራዊ ሠራተኞች መጎዳታቸው የተሰማው፣ ትራምፕ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረሰው እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ያስችላል የተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት "አብቅቷል" ካሉ በኋላ በአገራቱ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ተባብሶ በቀጠለበት ጊዜ ነው።
የአሜሪካ ጦር ከአንድ ሳምንት በላይ በተከታታይ በኢራን ዒላማዎች ላይ የምሽት ጥቃቶችን ፈፅሟል።
ጥቃቱን የሚፈፅመው ኢራን በንግድ መርከቦች ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ለማስቆም እንደሆነ ገልጿል።
ኢራን በበኩሏ አሜሪካ ለምትፈፅምባት ጥቃት በዮርዳኖስ ፣ ኩዌት፣ ባሕሬን እና ሌሎች የአሜሪካ አጋር አገራት ላይ ጥቃት በመሰንዘር የአፀፋ ምላሽ እየሰጠች ነው።