በአፍንጫ በሚገባ ውሃ አማካኝነት የሚከሰተው አንጎልን የሚያጠቃው አስፈሪው ተህዋስ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ስቲቭ ስሜልስኪ በኮስታ ሪካ በደስታ የተሞላ የቤተሰብ ሽርሽር ላይ ነበር።

ከቀናት በኋላ ግን ራሱን ያገኘው በጽኑ ሕሙማን ክፍል ሕይወቱ ካለፈው ብቸኛ ልጁ አልጋ አጠገብ በሐዘን ተውጦ ነበር።

በወቅቱ የ11 ዓመት ታዳጊ የነበረው ጆርዳን ሕይወቱ ያለፈው የአንጎል ቀበኛ አሜባ ተብሎ በሚታወቀው በኔግሌሪያ ፋውለሪ ጥገኛ ተህዋስ በሚከሰት የአንጎል ኢንፌክሽን ነው።

ይህ ተህዋስ በብዛት የሚገኘው በሞቃታማ ሐይቆች፣ ምንጮች፣ ፍል ውሃዎች፣ ወንዞች እንዲሁም ባልተፀዱ የመዋኛ ገንዳዎች ውስጥ ነው።

አንጎልን ከጥቅም ውጪ የሚያደርገው ይህ አሜባ ወደ ሰውነት የሚገባው ሰዎች ወደ ውሃ ውስጥ ዘለው በሚገቡበት ጊዜ በአፍንጫ በኩል በመግባት ነው።

ከዚያም ወዲያውኑ የአንጎል ህዋሳትን ማጥቃት ይጀምራል።

የ67 ዓመቱ ስቲቭ "ጆርዳን አንድ ቀን፣ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የዋኘው፤ አሁን ግን ተለይቶናል" ሲል ለቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ተናግሯል።

ባለፈው ዓመት በሕንድ በዚህ አንጎልን በሚያጠቃ ጥገኛ ተህዋስ የተያዙ ከ200 በላይ ሰዎች ተመዝገበዋል።

ይህ ቁጥር በዓለም በአንድ አገር የተመዘገበው ከፍተኛው ሲሆን ከቅርብ ወራት ወዲህ በአገሪቱ እንዲህ ዓይነት ኬዞች መታየታቸውን ቀጥለዋል።

ከዚህ በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ የበሽታው ክስተቶች ከ500 ያነሱ ነበሩ።

አሁን የተከሰተው ወረርሽኝም በተመራማሪዎች ላይ ስጋትን ፈጥሯል ። ተመራማሪዎች እንደሚሉት ተህዋሱ እምብዛም በማይታይባቸው ቦታዎች ላይ ሁሉ ተገኝቷል።

በዩናይትድ ኪንግደም፣ በኬንት ዩኒቨርሲቲ የጥገኛ ተህዋሳት ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አንስታሲዮስ ቲሲኦሲስ "ወደፊት ተጨማሪ ክስተቶች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ። ይህንንም በዓለም ላይ እናየዋለን" ብለዋል።

" አዕምሯችሁን ነው የሚያሳጣው"

በአሜሪካ ፍሎሪዳ ነዋሪ የሆነው ስቲቭ ከልጁ ጋር በኮስታ ሪካ ከነበሩበት ሆቴል አቅራቢያ ባለ ሙቅ ተፈጥሯዊ ምንጭ እየተንሸራተቱ በመግባት እየተወዳደሩ ሲዝናኑ ነበር።

በዚህ ጊዜ ነበር ጆርዳን ራስ ምታት የጀመረው።

ወደ ቤት ከሄዱ በኋላም ራስ ምታቱ የባሰበት ሲሆን ማስታወክ ጀመረ።

ከዚያም ወላጆቹ በአካባቢው ወደሚገኝ ሆስፒታል ይዘውት ሄዱ።

ጆርዳን ሆስፒታል ውስጥ ሆኖ ይቃዥ ነበር፤ በመስታወቱ ላይ ነፍሳት ሲርመሰመሱ እንደሚታየውም ሲነግራቸው ነበር።

"ይመለከተናል፤ ግን እነማን እንደሆንን አያውቅም ነበር። እሱ ራሱ ማን እንደነበር ያውቅ ነበር ብዬም አላስብም" ብሏል ስቲቭ።

ጆርዳን ምን እንዳጋጠመው ለማወቅ ዶክተሮች ቢረባረቡም አየር ስላጠረው በኋላ ላይ ሕይወቱ ወዳለፈበት ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል ተወስዷል።

"ከዋኘ በሰባት ቀን ከግማሽ ውስጥ ተለይቶናል" የሚለው ስቲቭ፣ ጆርዳን ሌላ የጤና እክል እንዳልነበረበት እና ጤናማ እንደነበር አስረድቷል።

ጆርዳን ሕይወቱ ያለፈው በኔግሌሪያ ፋውለሪ አማካኝነት በሚመጣ እና ማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓትን በሚያጠቃ የመጀመሪያ ደረጃ አሞቢክ ሜኒንጎሴፓሊቲስ (ፒኤምኤ) የአንጎል በሽታ ነው።

የበሽታው ሰለባ እንደሆኑ በርካታ ሰዎች ሁሉ ጆርዳንም መጀመሪያ ላይ ማጅራት ገትር እንዳጋጠመው ነበር የታሰበው።

ሁለቱ የጤና እክሎች በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ሳሉ ምልክቶቻቸው ይመሳሰላል።

ዶክተሮችም በሽታውን ለይተው ያወቁት ከረፈደ በኋላ ነበር። ኢንፌክሽኑ በአንጎሉ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ እብጠት ያመጣ ሲሆን የማይመለስ ጉዳትም አስከትሏል።

"አእምሯችሁን ይሰውረዋል፤ ሃሳባችሁን ይነጥቃችኋል፤ ማን እንደነበራችሁ ሳይቀር ትረሳላችሁ" ይላል ስቲቭ።

በአዳዲስ ቦታዎች ላይ እየታየ ያለው ለምንድን ነው?

የኢንፌክሽን እና የሕብረተሰብ ጤና ጆርናል ላይ እንደታተመው የ2025 ጥናት ከሆነ ከአውሮፓውያኑ 1962 እስከ 2023 ባሉት ዓመታት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመዘገቡ 488 የበሽታው ክስተቶች አብዛኞቹ የተመዘገቡት በደቡባዊ የአሜሪካ ግዛቶች፣ በፓኪስታን እና በአውስትራሊያ ነበር።

በበሽታው ከተያዙት ውስጥም 97 በመቶ የሚሆኑት ሞተዋል።

ሆኖም ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ እነዚህ ክስተቶች ቁጥራቸው ጨምሮ ጣልያን እና ቤልጂየምን ጨምሮ በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ በሚገኙ አገራት ውስጥም እየታዩ ነው።

ሚኒሶታን ጨምሮ ቀዝቃዛ በሆኑት ሰሜናዊ የአሜሪካ ግዛቶችም ባለፉት 15 ዓመታት አዳዲስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።

ባለፈው ዓመትም ስሎቫኪያ የመጀመሪያውን የኔግሌሪያ ፋውለሪ ክስተት መዝግባለች።

የበሽታው ክስተት በተለምዶ ከአሜባ ጋር ከሚያያዙት ሐይቆች እና ወንዞች ባሻገርም የተገናኙ እየሆኑ ነው።

በ2023 በታይዋን አንድ ግለሰብ በቤት ውስጥ በሚገኝ መዋኛ ውስጥ ለኔግሌሪያ ፋውለሪ ከተጋለጠ በኋላ ሕይወቱ አልፏል።

በተመሳሳይ ዓመትም በአሜሪካ አንድ ሕፃን ሰዎች በተገለገሉበት የፕላስቲክ የውሃ ገንዳ ውስጥ ለሞት ለዳረጋት ለዚህ ጥገኛ ተውሳክ ተጋልጣለች።

የአየር ንብረት ለውጥ ሐይቆችን እና ግድቦችን በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚያሞቃቸው አሜባው ራሱን ለማሰንበት ቀዝቀዝ ወዳሉ አካባቢዎች መስፋፋት ይጀምራል።

"ውሃው ሲሞቅ አሜባው በጣም ንቁ ይሆናል" የሚሉት ቲሲኦሲስ ፣ በተለይ በዚህ ወቅት በውሃ አካላት ውስጥ የሚዝናኑ ሰዎች በተውሳኩ የመጠቃታቸው ዕድል ከፍተኛ እንደሚሆን ተናግረዋል።

"የሚያስጨንቅ ምንም ምክንያት የለም፤ ነገር ግን ሰዎች እየጨመረ ለመጣው አደጋ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው" ሲሉ መክረዋል።

ጨምረውም ተመራማሪዎች አሜባውን ለመለየት እየተቃረቡ እንደሆነ እንደሚያምኑ እና ይህም በርካታ የበሽታው ክስተቶች እንዲገኙ አስተዋፅኦ ሊያደርግ እንደሚችል ተናግረዋል።

"የእኔ መላ ምት ቁጥሩ ሁልጊዜም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል የሚል ነው። አሁን ላይ እንዴት መመርመር እንደሚቻል ስላወቅን ነው ቁጥሩ እየጨመረ እንደሆነ የተረዳነው" ብለዋል።

ሕፃናት ለምን ይበልጥ ተጋላጭ ሆኑ?

ሕፃናት ከአዋቂዎች በበለጠ በኔግሌሪያ ፋውለሪ የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

"ሰዎች በዚህ በሽታ የሚሰቃዩበት ዋነኛው ዕድሜ 12 ነው። ምክንያቱም ሕፃናት በሙቅ ውሃ ውስጥ መዋኘት ይወዳሉ" ይላሉ በዌስተርን ሲድኒ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሳይንስ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ኢያን ራይት።

"ተውሳኩ በጣም ጨካኝ ነው" ይላሉ።

አንዳንድ ተመራማሪዎችም ሕጻናት በኢንፌክሽኑ ለመያዝ ይበልጥ ተጋላጭ እንደሆኑ ይገልጻሉ።

ለዚህም ምክንያቱ ተውሳኩ በታዳጊዎች አፍንጫ አልፎ ወደ አንጎላቸው ለመግባት ቀላል ስለሚሆንለት ነው።

"ልክ እንደ ቅዠት፣ አስፈሪ ፊልም ነው" ሲሉ በሽታውን የሚገልጹት ራይት "በበሽታው ላትያዙ ትችላላችሁ፤ ከተያዛችሁ ግን ልትሞቱ ትችላላችሁ" ብለዋል።

ወዲያውኑ ከተደረሰበት ዶክተሮች የመድኃኒት ውህድ በመጠቀም እንዲሁም የአንጎል እብጠትን የሚቀንስ መድኃኒት በመስጠት ታማሚውን ለማከም ይሞክራሉ። ሆኖም ከበሽታው የሚተርፉት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።

ሆኖም ከሕንድ ደቡባዊ ግዛቶች አንዷ በሆነችው እና የጎብኚዎች መዳረሻዋ ኬራላ በሽታው ምን ያህል ገዳይ እንደሆነ ያለውን አስተሳሰብ የሚለውጥ ሁኔታ አስመዝግባች።

በግዛቷ በበሽታው እንደተያዙ ከተረጋገጠ 200 ሰዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ተርፈዋል።

ይህም በታሪክ ካለው ሦስት በመቶ ከሞት የመትረፍ ዕድል እጅግ የላቀ እንደሆነ በኮሚዩኒኬሽን ሜድስን ላይ የታተመ አዲስ ጥናት አመልክቷል።

የጥናቱ ግኝቶች አንጎልን በሚበላው አሜባ የሚከሰተው በሽታ ቀደም ሲል ይታሰብ እንደነበረው የማይታከም አይደለም።

ጥናቱን እንዳካሄደው ዓለም አቀፍ የምርምር ቡድን ከሆነ ቶሎ የሚደረግ ሕክምና፣ በሕክምና ባለሙያዎች ዘንድ ያለው ግንዛቤ መላቅ እና ቀጣይነት ያላቸው የሕክምና ዘዴዎች ለተሻሻለው ውጤት አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ራሳችንን እንዴት ልንጠብቅ እንችላለን?

ኔግሌሪያ ፋውለሪ ውሃ ውስጥ ከሚደረግ ጨዋታ በተጨማሪ ሰዎች በቅዝቃዜ፣ በሳይነስ ወይም በአለርጂ ምክንያት የተዘጋ አፍንጫቸውን ለማጽዳት ወደ ውስጥ ፈሳሽ በሚያስገቡበት ወቅት አብሮ ወደ ሰውነት ሊገባ ይችላል።

ባለፈው ዓመት በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት አንዲት የ71 ዓመት ሴት በሌላ የጤና እክል የቧንቧ ውሃ በውሃ መርጫ ወደ አፍንጫዋ ባስገባች በሁለት ሳምንት ውስጥ ሕይወቷ አልፏል።

በእስልምና እና በሌሎች ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እንዲሁም እንደ አዩርቬዳ ባሉ የሕንድ አጠቃላይ የሕክምና ዘዴ አፍንጫ በሚፀዳበት ጊዜ ለበሽታው የመጋለጥ አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል።

አነስተኛ የሆነውን ተጋላጭነታችንን ለመቀነስ ሊረዱ የሚችሉ ቀላል እርምጃዎች አሉ።

የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ያልታከመ የቧንቧ ውሃ እምብዛም ካልተለመደው በሽታ ጋር ስለሚገናኝ አፍንጫን ለማጽዳት የታከመ፣ የተጣራ ወይም ፈልቶ የቀዘቀዘ ውሃ መጠቀምን ይመክራል።

በሙቅ ንጹህ ውሃ በምንዋኝበት ጊዜም ውሃው ወደ አፍንጫችን እንዳገይባ ማድረግ ተጋላነጭትን ይቀንሳል ብሏል። ለዚህም ወደ ውሃ ውስጥ ዘለን ስንገባ አፍንጫችንን መያዝ ወይም የአፍንጫ መሸፈኛ (ክሊፕ) መጠቀምን ይመክራል።

"ከተጠራጠራችሁ ደግሞ ጭንቅላታችሁን ውሃ ውስጥ አትክተቱ" ብለዋል የውሃ ሳይንስ ባለሙያው ራይት።