አሜሪካ በአፍሪካ በርካታ የቪዛ ማዕከላትን ስትዘጋ፣ የአዲስ አበባ ኤምባሲዋ አንዱ ማዕከል ይሆናል ተባለ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አሜሪካ በአፍሪካ ውስጥ ቪዛ ይሰጥባቸው የነበሩትን ሃምሳ የሚሆኑ ኤምባሲዎቹን በማጠፍ ወደ 20 ሊቀንስ መሆኑ ሲገለጽ፤ አዲስ አበባ የቪዛ ማዕከል ከሚባሉት አንዷ እንደሆነች ተዘገበ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፍሪካ ውስጥ የውጭ ዜጎችን የቪዛ ጥያቄ በመቀበል ምላሽ የሚሰጡ የኤምባሲዎቹን ቁጥር በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ ባወጣው ዕቅድ መሠረት ነው የቪዛ ሂደት በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ እንዲታይ የወሰነው።

በዚህ ውሳኔ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ቪዛ ይሰጡ የነበሩት ወደ 50 የሚጠጉ የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች በሚቀጥለው ሳምንት ቁጥራቸው ወደ 20 እንደሚወርድ አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ሦስት ባለሥልጣናትን እና የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱን የውስጥ ማስታወሻ ጠቅሶ ዘግቧል።

ይህ ውሳኔ የትራምፕ አስተዳደር በጊዜያዊ ቪዛ ወደ አሜሪካ ገብተው የሚቀሩ ሰዎችን ለመቆጣጠር ካለው ሰፊ ዕቅድ ጋር ኤምባሲዎቹ የሚሰጧቸውን የተለያዩ አይነት ቪዛዎች ለመቆጣጠር ካለው ዕቅድ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።

ባለፈው ሳምንት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የጸደቀው ውሳኔ አርብ ዕለት በስልክ በተደረገ ስብሰባ ላይ ለአሜሪካ ዲፕሎማቶች መገለጹን አንድ ምንጭ ለኤፒ አረጋግጠዋል።

በዚህ ውሳኔ መሠረትም በአፍሪካ ውስጥ የቪዛ አገልግሎት የሚሰጡ በተለያዩ አገራት ውስጥ የሚገኙ "ማዕከላት" የሚባሉ 20 የአሜሪካ ኤምባሲዎች ብቻ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

ኤፒ የተመለከተው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የውስጥ ማስታወሻ 20ዎቹን ቪዛ የሚሰጡ የአሜሪካ ኤምባሲዎችን የያዘ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ይገኝበታል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ተጎራባች ከሆኑ አገራት መካከል የአሜሪካ ቪዛ የሚሰጥባቸው ናቸው የተባሉት ጂቡቲ እና ኬንያ የሚገኙት ኤምባሲዎች ናቸው።

በሰኔ ወር ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን በተነገረው በዚህ አሠራር አሜሪካ ወደ አገሯ ለመግባት የቪዛ ጥያቄ የሚያርቡ አፍሪካውያን በአገራቸው ውስጥ ቪዛው የማይሰጥ ከሆነ በአቅራቢያቸው በሚገኝ አገር በመሄድ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

ይህ አሠራር ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዜጎች የቪዛ ጥያቄ ላይ ከጣሏቸው ግዴታዎች ጋር ተደማምሮ የአሜሪካ ቪዛ ማግኘትን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው እየተነገረ ነው።

በፕሬዝዳንቱ ውሳኔ መሠረት የአንዳንድ አገራት ዜጎች ቪዛ እንዳይሰጣቸው መገደብ፣ የቪዛ ቆይታ ጊዜን ማሳጠር እንዲሁም ቪዛ ለማግኘት ከፍተኛ ገንዘብ ማስያዝ ከዚህ ቀደም ተግባራዊ የተደረጉ አሠራሮች ናቸው።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር በቪዛ አሰጣጥ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ከማድረጉ በተጨማሪ በአፍሪካ እና በሌሎች አገራት ውስጥ የሚገኙ የኤምባሲ እና ቆስላዎችን መጠን እንዲሁም ዲፕሎማቶቹን ካለፈው ዓመት ጀምሮ መቀነሱ ይታወሳል።