ዱባይ በጦርነቱ የሸሹ ጎብኚዎችን ለመሳብ ቅናሽ እና ማበረታቻ ልትሰጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተበባሩት አረብ ኤምሬትስ ታዋቂዋ የቱሪስት ከተማ ዱባይ በጦርነት ምክንያት የተዳከመውን የቱሪስት ፍሰት ለማነቃቃት ለወራት የሚቆይ ልዩ ቅናሽ በመስጠት ጎብኚዎችን ልታበረታታ መሆኗን አስታወቀች።
ቤተሰቦቻቸውን እና ጓደኞቻቸውን ወደ ዱባይ ለጉብኝት የሚጋብዙ የከተመዋ ነዋሪዎች ከ800 ዶላር በላይ ቅናሽ እና ልዩ መስተንግዶ እንደሚቀርብላቸው የዱባይ የመገናኛ ብዙኃን ጽህፈት ቤት ዛሬ ረቡዕ አስታውቋል።
ይህ አስከ መጪው ዓመት ጥቅምት ድረስ የሚቆየው ማበረታቻ የተዘጋጀው በባሕረ ሰላጤው እየተካሄደ ያለው ጦርነት በግዛቲቱ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያስከተለውን ጫና እና ጉዳት ለመቀነስ ነው።
የዱባይ አስተዳደር በድረገጹ ላይ እንዳመለከተው ከአሁን ጀምሮ አስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ ቤተሰቦቻቸውን እና ጓደኞቻቸውን ለጉብኝት የሚጋብዙ ነዋሪዎች የሚያርፉበት ሆቴል፣ የምግብ እና የጉብኝት ቦታዎች ትኬቶችን ጨምሮ የተለያዩ ጥቅማጥቆሞችን ያገኛሉ።
በመካከለኛው ምሥራቅ ዋነኛዋ የቱሪስት መዳረሻ የሆነችው አንዷ በየዓመቱ 19.5 ሚሊዮን ጎብኚዎችን ስታስተናግድ ቆይታለች።
ነገር ግን አሜሪካ እና አስራኤል በኢራን ላይ ባካሄዱት ከአንድ ወር በላይ በዘለቀ ጦርነት የቱሪስት ፍሰቷ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።
በጦርነቱ ወቅት ኢራን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ዒላማ ያደረገች ሲሆን፣ ሆቴሎች እና ታላላቅ ተቋማቷ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።
በዚህም የተነሳ በወሳኙ የጎብኚዎች ጊዜ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በርካታ ቱሪስቶች አገሪቱን ለቅቀው መውጣታቸው ተዘግቧል።
ሚያዝያ ላይ የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላ የተወሰኑ ጎብኚዎች ወደ አገሪቱ ቢገቡም የቀደመው የቱሪስቶች ፍሰት አልተመለሰም። በዚህም የተነሳ የዱባይ መንግሥት በጦነርቱ ጫና የደረሰባቸውን የንግድ ተቋማትን ለማገዝ የ400 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አቅርቧል።



















