ቀጥታ, ኢራን ከአሜሪካ ጋር “ሙሉ ጦርነት” ውስጥ መገባቱን ስትገልጽ፤ ዋሽንግተን ለ10ኛ ተከታታይ ቀን ጥቃት ፈጸመች

የአሜሪካ ጦር፣ የኢራንን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚተላለፉ መርከቦች የማጥቃት አቅም "ይበልጥ ለማዳከም" ያለመ ነው ያለውን ጥቃት ለ10ኛ ተከታታይ ቀን ፈጽሟል። የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በበኩላቸው፤ አገራቸው በአሁኑ ሰዓት ከአሜሪካ ጋር "ሙሉ ጦርነት" ውስጥ መሆኗን ተናግረዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በአሜሪካ “የስደተኞች ፖሊስ ተቃዋሚ” የሆነ የቀድሞ ወታደር በጸጥታ መሥሪያ ቤት ደጅ እሳት አሰነሳ

    በፌደራል ሕንፃ ፊት ለፊት የተነሳው እሳት

    የፎቶው ባለመብት, Robert Sullivan/AP

    በአሜሪካ ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የፌደራል ሕንፃ ፊት ለፊት እሳት ያስነሳ የቀድሞ ወታደር በቁጥጥር ሥር ዋለ።

    ግለሰቡ ሰኞ ዕለት እሳት ያስነሳው የፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ)፣ የስደተኞች እና ጉምሩክ ደንብ አስከባሪ (አይስ) እንዲሁ የአሜሪካ ዜግነት እና ኢሚግሬሽን አገልግሎት ተቋማት የሚገኙበት ’26 ፌደራል ፕላዛ’ የተሰኘው ሕንፃ ደጅ ላይ ነው።

    አንድሪው አራባካ የተባለው የ43 ዓመት ግለሰብ በአየር ግፊት የሚሰራ ፔሌት ሽጉጥ እንደተኮሰ እና ርችት እንደለኮሰ ተገልጿል።

    የፌደራል የጸጥታ አባላት ቆንጨራ እና ሌሎች መሣሪያዎችን ይዞ የነበረውን ይህን ተጠርጣሪ ይዘውታል።

    በዚህ ክስተት ማመልከቻው እየታየ የነበረ አንድ ስደተኛን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ኤፍቢአይ ገልጿል።

    የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት፤ ግለሰቡን “ፀረ አይስ አማጺ” ሲል ጠርቶታል። እሳቱን ከማያያዙ በፊት በሕንፃው መግቢያ ደረጃዎች ላይ ማቀጣጠያ በማፍሰስ እሳት ማስነሳቱንም ጠቅሷል።

    ቢቢሲ ስለ ጉዳዩ አስተያየት ለማግኘት ለአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ጥያቄ አቅርቧል።

    የእሳት አደጋ ባለሙያዎች እሳቱን አጥፍተውታል።

    ኤፍቢአይ እንደሚገልጸው፤ ግለሰቡ "በክስተቱ ወቅት በርካታ መንግሥትን እና አይስን የሚቃወሙ ንግግሮችን” አሰምቷል።

    በኤፍቢአይ የኒው ዮርክ ምክትል ዳይሬክተር ጄምስ ባርናክል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አራባካ ሁለት መጥረቢያ፣ አንድ ቆንጨራ፣ ሦስት ቢላ እና ርችት ይዞ እንደነበር ተናግረዋል።

    በያዘው የፔሌት ሽጉጥ ከአምስት እስከ ሰባት ጊዜ ወደ ሕንፃው አቅጣጫ እንደተኮሰም አስረድተዋል።

  2. ኢራን ባለፉት ቀናት የአሜሪካ ወታደሮችን መግደሏን እና የጦር ጄት ማውደሟን አስታወቀች

    የኢራን ሚሳዔሎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን አብዮታዊ እስላማዊ ዘብ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት ላይ በፈጸመው ጥቃት የአሜሪካ ወታደሮችን መገደላቸውን እና የአገሪቱ የጦር አውሮፕላን መውደሙን አስታወቀ።

    አሜሪካ እየፈጸመችባት ላለው ተከታታይ ጥቃት ኢራን እየወሰደችው ባለው የአጸፋ እርምጃ ዮርዳኖስ፣ ኩዌት እና ባህሬን ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ይዞታዎችን ዒላማ አድርጋለች።

    ባለፉት ቀናት ከተፈጸሙት የኢራን ጥቃቶች መካከል ዮርዳኖስ ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ሠራዊት ጦር ሰፈር ላይ በደረሰው ጉዳት “በርካታ” ወታደሮች መገደላቸውን የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

    ነገር ግን የኢራን አብዮታዊ ዘብ ላወጣው መግለጫ አሜሪካ አስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጠችም።

    ቀደም ሲል ግን ከአራት ቀናት በፊት ኢራን በፈጸመችው የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት ሦስት ወታደሮቹ እንደተገደሉበት የአሜሪካ ጦር አሳውቆ ነበር።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የአሜሪካ የራዳር እና የመከላከያ ተቋማት ላይ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት በዮርዳኖስ መጠለያ ውስጥ ቆሞ የነበረ አንድ የአሜሪካ ኤፍ 15 የጦር አውሮፕላን መውደሙን አብዮታዊ ዘቡ ገልጿል።

    ኢራን ካለፈው ሳምንት ወዲህ በተለይ ዮርዳኖስ ውስጥ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እየፈጸመች ሲሆን፣ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል እንዳስታወቀው በሚሳዔል እና ድሮን ጥቃቶቹ የሚሳዔል ጥቃት መከላከያ ሥርዓቶችም ዒላማ ሆነዋል።

    የአሜሪካው ጋዜጣ ኒው ዮርክ ታይምስ ወታደራዊ ባለሥልጣንን ዋቢ አድርጎ ሰኞ ዕለት እንደዘገበው፣ ኢራን ባለፈው ሳምንት ዮርዳኖስ በሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ውስጥ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች በርካታ ወታደሮች ቆስለዋል፤ ሄሊኮፕተሮችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳረጋገጠው በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ ኢራን በፈጸመችው ጥቃት ወደ 100 የሚጠጉ ወታደሮች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

  3. በአንድ ወር ወደ 100 የሚጠጉ የአሜሪካ ወታደሮች በኢራን ጥቃት መጎዳታቸውን የዋሽንግተን ባለሥልጣናት ተናገሩ

    የጦር አውሮፕላኖች

    የፎቶው ባለመብት, US Central Command

    ኢራን በዚህ ወር በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ላይ በፈፀመቻቸው በርካታ የአየር ጥቃቶች 100 የሚጠጉ የአሜሪካ ሠራዊት አባላት ጉዳት እንደደረሰባቸው የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    የፔንታጎን ኃላፊ ቃል አቀባይ ሲን ፓርኔል የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ በላኩት መግለጫ ቁጥሩን ያረጋገጡ ሲሆን ከሰኔ መጨረሻ ወዲህ 100 የሚሆኑ ሠራተኞቹ የተለያየ መጠን ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

    አብዛኛው ጉዳት ቀላል መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ 96 በመቶ የሚሆኑት ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰዋል ብለዋል።

    ባለፈው ሳምንት ብቻ በርካታ የአሜሪካ ወታደራዊ ሠራተኞች በዮርዳኖስ የጦር ሠፈር መጎዳታቸው ተዘግቧል።

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ሁለት የአሜሪ ካወታደሮች በዮርዳኖስ በሚገኝ የጦር ሠፈር መገደላቸው እና ሌላ ወታደር የት እንደገባ አለመታወቁን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ገልጿል።

    ሌላ ወታደር ደግሞ ኢራቅ ውስጥ ተገድሏል።

    በአሁን ወቅት በርካታ ወታደራዊ ሠራተኞች መጎዳታቸው የተሰማው፣ ትራምፕ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረሰው እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ያስችላል የተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት "አብቅቷል" ካሉ በኋላ በአገራቱ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ተባብሶ በቀጠለበት ጊዜ ነው።

    የአሜሪካ ጦር ከአንድ ሳምንት በላይ በተከታታይ በኢራን ዒላማዎች ላይ የምሽት ጥቃቶችን ፈፅሟል።

    ጥቃቱን የሚፈፅመው ኢራን በንግድ መርከቦች ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ለማስቆም እንደሆነ ገልጿል።

    ኢራን በበኩሏ አሜሪካ ለምትፈፅምባት ጥቃት በዮርዳኖስ ፣ ኩዌት፣ ባሕሬን እና ሌሎች የአሜሪካ አጋር አገራት ላይ ጥቃት በመሰንዘር የአፀፋ ምላሽ እየሰጠች ነው።

  4. ኢራን ከአሜሪካ ጋር “ሙሉ ጦርነት” ውስጥ መገባቱን ስትገልጽ፤ ዋሽንግተን ለ10ኛ ተከታታይ ቀን ጥቃት ፈጸመች

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የፎቶው ባለመብት, Iran's Presidential website/WANA/Reuters

    የአሜሪካ ጦር፣ የኢራንን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚተላለፉ መርከቦች የማጥቃት አቅም "ይበልጥ ለማዳከም" ያለመ ነው ያለውን ጥቃት ለ10ኛ ተከታታይ ቀን ፈጽሟል።

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በበኩላቸው፤ አገራቸው በአሁኑ ሰዓት ከአሜሪካ ጋር "ሙሉ ጦርነት" ውስጥ መሆኗን ተናግረዋል።

    “እውነታው ዛሬ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ሙሉ የሆነ ጦርነት ውስጥ መሆኗ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ “እውነታውን መገንዘብ እና የዚህን ተጋድሎ ተፈጥሯዊ መዘዞች መቀበል ይኖርብናል” ሲሉ ባወጡት መግለጫ አሳስበዋል።

    የሰኞ ሌሊቱ የዋሽንግተን ጥቃት የተፈጸመው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፈጸመችው ጥቃት የአሜሪካ ወታደሮችን የገደለችው ኢራንን እንደሚቀጡ ከተገዘቱ በኋላ ነው።

    ባለፉት ቀናት በደረሱ ጥቃቶች ዮርዳኖስ ውስጥ ሁለት፣ በኢራቅ ደግሞ አንድ የአሜሪካ ወታደሮች ተገድለዋል።

    ኢራን ከትናንቱ ጥቃት በኋላ በወሰደቸው የአጸፋ እርምጃ፤ በሆርሙዝ ሲጓዙ የነበሩ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች እንዲሁም ባህሬን እና ኩዌት ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ይዞታዎችን መምታቷን ‘ኢርና’ የተሰኘው የመንግሥት የዜና ወኪል ዘግቧል።

    በተመሳሳይ ሰዓት፣ ከዚህ ቀደም የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት የከሸፈባቸው አሜሪካ እና ኢራን በአሸማጋዮች አማካኝነት ዲፕሎማሲያዊ መልዕክት እየተለዋወጡ መሆኑን ቴህራን አስታውቃለች።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ፤ በትናንቱ ጥቃት የኢራን "ወታደራዊ የዕዝ ማዕከላት፣ የባህር ኃይል አቅሞች፣ የሚሳዔል እና የድሮን ማስወንጨፊያ ስፍራዎች እንዲሁም የአየር መከላከያ ሥርዓቶች"መምታታቸውን ገልጿል።

    የንግድ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያደርጉትን ጉዞ እንደቀጠሉም በመግለጫው ጠቅሷል።

    ኢራን በበኩሉ ጥቃት በፈጸመችባቸው ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ውስጥ የነበሩ ባሕርተኞችን ለማውጣት የነፍስ አድን ቡድን መሰማራቱን አስታውቃለች። መርከቦቹ የተመቱት በወሽመጡ በኩል ለማለፍ በመሞከራቸው መሆኑን ኢርና ዘግቧል።

    የዮርዳኖስ መከላከያ ሠራዊት በበኩሉ ከኢራን የተወነጨፉ ሦስት ሚሳዔሎችን መትቶ መጣሉን ገልጿል። የኩዌት ጦርም ኢራን ድሮኖችን እንደጠለፈ አስታውቋል።

    ባሕሬን ደግሞ ከኢራን የተነሳ ድሮን የአየር መቆጣጠሪያ ስርዓቶቿን ዒላማ ቢያደርጉም በረራዎች አለመስተጓጎላቸውን ጠቅሳለች።

    የአሜሪካ ጦር በፈጸማቸው ጥቃቶች ታብሪዝ፣ ቻባሃር፣ ኮናራክ፣ ባንዳር ማህሻህር እና ባንዳር ኢማም ኾሜኒን ጨምሮ በርካታ ከተሞች መመታታቸውን ከፊል ይፋዊ የዜና ወኪል የሆነው ታስኒም ዘግቧል።

    በኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ መሠረት፣ ሆርሙዝ ወሽመጥን ለማቋረጥ የሞከሩ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ፍንዳታ ተከስቷል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ፤ መርከቦቹ "ደኅንነቱ ባልተጠበቀው እና በአደገኛው ደቡባዊ መስመር" እየተጓዙ ስለነበረ፤ “ፍንዳታ እንደተከሰተባቸው እና ጉዟቸው እንዲቋረጥ መደረጉን” አስታውቋል። የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በበኩሉ ይህንን ገለጻ አስተባብሏል።

  5. አንዲ በርንሃም የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ

    አንዲ በርንሃም

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    አንዲ በርንሃም በፈቃዳቸው ከሥልጣን የለቀቁትን የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ተክተው የአገሪቱ መሪ ሆኑ።

    የግሬተር ማንችስተር ከንቲባ የነበሩት በርንሃም፣ ዩናይትድ ኪንደግም ለመምራት በአምስት ዓመታት ውስጥ የተሾሙ ስድተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል። በአስር ዓመት ውስጥ ደግሞ ሰባተኛው የአገሪቱ መሪ ናቸው።

    አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመጀመሪያ ንግግራቸው፤ “አገራችን ውስጥ የሚታየው የጎዳና አዳር እንዲያበቃ [አደርጋለሁ]” ብለዋል።

    ይህንን ለማስፈጸምም በአምስት ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ 340 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚመደብ ተገልጿል።

    በዚህ ገንዘብ አማካኝነት 1,200 ቤቶች እንደሚገነቡ እንዲሁም በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ለ3,000 ሰዎች “ከፍተኛ ድጋፍ” እንደሚደረግ ጽሕፈት ቤታቸው አስታውቋል።

    በርንሃም፤ መንግሥታቸው “ለሰዎች ውድቀት ከመክፈል ይልቅ፣ ስኬታቸው ላይ ኢንቨስት” እንዲያደርግ እንደሚፈልጉ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

    በተያዘው 2026 መጨረሻም አገሪቱ የምትመራበት አዲስ የ10 ዓመት ዕቅድ ይፋ እንደሚደረግ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "የሕይወት መሠረታዊ ፍላጎቶችን በሕዝብ ቁጥጥር ስር ማድረግ" የሚያስችል ኢኮኖሚ እንደሚገነቡም ተናግረዋል።

    ከአውሮፓውያን 2016 ወዲህ የተሾሙ ሰባተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን በደንብ እንደሚገነዘቡ በመጥቀስም፤ “መለስ ብሎ መመልከቻ እና አዲስ ውሳኔ” ላይ መድረሻ ጊዜ እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል። ብሪታኒያ መረጋጋት ማግኘት እንዳለባትም በአጽንኦት አንስተዋል።

    ፖለቲከኞች “በበቂ ሁኔታ ጥሩ አልነበሩም” በማለት የተቹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተሻለ ለመሆን ቃል ገብተዋል። ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ ያልታዩ ከፍተኛ ለውጦችን እንደያደርጉም ተናግረዋል።

  6. ሩሲያ በጭነት መርከብ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 10 ሰዎች ተገደሉ

    ጥቃት የደረሰበት መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Andrii Sybiha

    ሩሲያ፣ ወደ ዩክሬኗ ከተማ ኦዴሳ ሲጓዝ በነበረ የጭነት መርከብ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 10 ሰዎች ተገደሉ።

    ዩክሬን አየር ኃይል እንደገለጸው፣ በጊኒ ቢሳው ሰንደቅ ዓላማ የሚንቀሳቀሰው መርከብ በሩሲያ የክሩዝ ሚሳዔሎች የተመታው ትናንት እሁድ ነው። የደረሰው ጥቃት እሳት አስነስቷል።

    ከእሁድ ምሽት አንስቶ መርከቡ ላይ የነበሩ ሰዎችን ለመታደግ እና ለማግኘት የነፍስ አድን ሥራ እየተከናወነ ነው። የዩክሬን የባሕር ወደቦች ባለሥልጣን ሰኞ ጠዋት ይፋ ባደረገው መረጃ፤ ዘጠኝ ባሕረተኞች እንዲሁም ከካፒቴኖቹ አንዱ መገደላቸውን አስታውቋል።

    ባለፉት ሳምንታት ኦዴሳ ግዛት ተከታታይ ጥቃቶችን አስተናግዷል። ሩሲያ ሐምሌ ላይ ብቻ በግዛቱ ላይ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች 28 ሰዎች መገደላቸውን የግዛቱ ዋና አስተዳዳሪ ኦሌህ ኪፐር ሰኞ ዕለት ለዩክሬን ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

    ሩሲያ በጥቁር ባሕር ላይ የሚጓዙ የጭነት መርከቦች ላይ የምትፈጽማቸው ጥቃቶችን ጨምረዋል።

    ከእነዚህ ጥቃቶች ውስጥ ብዙ ሰዎች የሞቱበት፣ እሁድ ዕለት በጊኒ ቢሳው ሰንደቅ ዓላማ የሚንቀሳቀሰው መርከብ ላይ የተፈጸመው ነው።

    ዓለም አቀፍ ባሕርተኞችን ይዘው በአብዛኛው በውጭ ሰንደቅ ዓላማ ሥር የሚንቀሳቀሱት እነዚህ የጭነት መርከቦች የሚጓዙት፣ ዩክሩን በቀራት ብቸኛ የኤክስፖርት ኮሪደር በኩል ነው። በሮማኒያ እና ቡልጋሪያ የባሕር ዳርቻዎች በኩል ከዩክሬን ወደ ቱርክ ያጓጉዛሉ።

    የሩሲያ ሙሉ ወረራ ከተጀመረ አንስቶ ላለፈው ከአራት ዓመት ተኩል በላይ የሚሆን ጊዜ በጥቁር ባሕር ላይ የሚደረገው ውጊያ በአብዛኛው አሸናፊ የነበረበት አይደለም።

    የሩሲያ ጦር አብዛኛውን የባሕር ዳርቻ በመቆጣጠሩ የዩክሬን መርከቦች በኦዴሳ ዙሪያ ወዳሉ አካባቢዎች ርቀው መጓዝ አይችሉም። ይሁን እንጂ ዩክሬን የምትፈጽማቸው የድሮን ጥቃቶች ሩሲያ ወታደራዊ አቅሟን በጥቁር ባሕር ምሥራቃዊ ክፍል ከሚገኙ የባሕር ኃይል ካምፖች እንዳታንቀሳቅስ አድርጓታል።

    ሩሲያ አሁን በዚህ ባሕር ላይ የምትፈጽመው ጥቃት ያጠናከረችው፤ የውጭ አገር ኩባንያዎች የዩክሬን ምርቶችን እንዳይገዙ እና የጥቁር ባሕር መተላለፊያን እንዳይጠቀሙ ለማድረግ እንደሆነ ይታመናል።

  7. ኢራን ከአሸማጋዮች የሰላም ዕቅድ እንደቀረበላት አስታወቀች

    የአሜሪካ ብንዲራ ከአጽም ጋር በተሳለበት ግድግዳ በኩል የምታልፍ ሴት

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    አሜሪካ እና ኢራንን በድጋሚ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ለመመለስ ያቀዱት አሸማጋዮች፣ አዲስ የሰላም ዕቅድ ማቅረባቸውን ቴህራን አስታወቀች።

    ሰኔ ላይ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራመው የነበሩት ሁለቱ አገራት፣ ላለፉት ሁለት ሳምንት ገደማ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ከባድ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ስምምነቱ አብቅቷል ብለዋል።

    ይህንን ስምምነት ዳግም ለመመለስ ያቀዱት አሸማጋይ አገራት የ10 ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቅ የሰላም ዕቅድ ማቅረባቸውን ዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ዛሬ ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀዋል። አሸማጋዮች ያዘጋጁትን ዕቅድ ለኢራን እንዳሳወቁ ቃል አቀባዩ አረጋግጠዋል።

    “በአሸማጋዮች ስለዘተጋጁት ዕቅዶች ገለጻ ተደርጎል፤ ዕቅዱም ደርሶናል። ነገር ግን ለአሁኑ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ባንገባ ይሻላል” ሲሉ ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    ባለፉት ቀናት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፤ “በአንዳንድ አሸማጋዮች የቀረቡ ዕቅዶች ለኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መድረሳቸው የተረጋገጠ ነው” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደፊት ለመደራደር የሚጠይቁ ከሆነ የኢራን ምላሽ ምን እንደሚሆንም ጥያቄ የቀረበላቸው ቃል አቀባዩ ኢስማኤል ባጋይ፣ “ዲፕሎማሲ ወይም ጦርነት” የሚል አማራጭ ለኢራን “ጠቃሚ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

    “ራስን መከላከል ከዲፕሎማሲ ጋር አይጣጣምም ብሎ ማሰብ ትክክለኛ አመክንዮ አይደለም። [የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ] ሰይድ አባስ አራግቺ የሚያከናውኑት ሥራ እና [የመከላከያ ሚኒስትሩ] ሰይድ መጂድ የሚፈጽሙት ተግባር ተመሳሳይ ግብ የሚያሳኩ ናቸው” ብለዋል።

    ባለፈው ሳምንት በመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት ላይ የነበሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፤ ከጉዟቸው ሲመለሱ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ዋሽንግተን “አሁንም ከኢራን ጋር ለሚደረግ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ በሯ ክፍት” መሆኑን ተናግረው ነበር።

    “ሁሌም ለዲፕሎማሲ ክፍት የሆንን ይመስለኛል። [መፍትሔው ግን] እውነተኛ መሆን አለበት። ልንገዛበት ፈቃደኛ የምንሆነው መሆን አለበት” ብለዋል።

    ኢራን ሰኔ ላይ ለተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት እንዳልተገዛች በመጥቀስ የከሰሱት ሩቢዮ፤ ሆርሙዝ ክፍት መሆን እንደነበረበት እንዲሁም በወሽመጡ የሚጓዙ መርከቦች ከጥቃት እና ከክፍያ ነጻ መሆን እንደነበረባቸው ገልጸዋል።

    አሜሪካ ለዲፕሎማሲ ክፍት ስለመሆኗ የተነሳላቸው የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ፣ “አሜሪካ ዲፕሎማሲ የምትለው ማስገደድ፣ ማስፈራራት፣ ዛቻ እና ማዕቀብ ነው” በማለት ተችተዋል።

  8. አሜሪካ ወሳኝ የኢራን የነዳጅ ዘይት ማዕከል የሆነችውን ደሴት ለመቆጣጠር እንዳታስብ ቴህራን አስጠነቀቀች

    ኻርግ ደሴት ላይ ያሉ የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች እና ማስተላለፊያ ቧንቧዎች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, ኻርግ ደሴት የኢራን የነዳጅ ማዕከል ናት

    አሜሪካ ወሳኟን የኢራን የነዳጅ እና የጋዝ መተላለፊያ ደሴት ኻርግ ለመቆጣጠር ጭራሽ እንዳታስብ እና ወረራ ለመፈጸም የምትሞክር ከሆነ ከባድ ምላሽ እንደሚጠብቃት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስጠነቀቀ።

    አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈጽመው ጥቃት በቀጠለበት እና ኢራን የአጸፋ ጥቃት እርምጃ በአጎራባች አገራት ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ እየወሰደች ባለበት በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ የኢራንን ግዛት የምትይዝ ከሆነ ጦርነቱ ይባባሳል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

    ከዚህ ቀደም ዶናልድ ትራምፕ በደቡባዊ ኢራን የምትገኘውን ኻርግ ደሴት የመቆጣጠር ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረው የነበረ ሲሆን፣ ግጭቱ በተባባሰበት ጊዜ አሜሪካ ይህንን ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ ኢራን ራሷን እንደምትከላከል አስታውቃለች።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ እንደተናገሩት “እንዲህ ያለው ጀብደኝነት ከባድ መዘዝን ያስከትላል” ሲሉ አሜሪካን አስጠንቅቀዋል።

    ጨምረውም አሜሪካ እግረኛ ጦሯን አሰማርታ ወረራ የምትፈጽም ከሆነ የአገሪቱ መሪዎች “አቀባበል ሊያደርጉላቸው ደቂቃዎችን እየቆጠሩ ነው” በማለት የአገራቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።

    የኢራን የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪ ዋነኛ ማዕከል የሆነችው ኻርግ ደሴት ከኢራን የባሕር ዳርቻ በ55 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

    ከወራት በፊት ጦርነቱ በተባባሰበት ጊዜ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደሴቱቱን በመቆጣጠር የኢራንን የነዳጅ ምርት በእጃቸው እንደሚያስገቡ በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደነበር ይታወሳል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ንግግር ለመጀመር በአሸማጋዮች በኩል የዲፕሎማሲያዊ መልዕክት ልውውጥ እየተካሄደ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

  9. ኢራን ላይ አዲስ ጥቃት የተፈፀመው ለተገደሉ አሜሪካውያን ወታደሮች ‘ክብር’ እንደሆነ ትራምፕ ተናገሩ

    የጦር አውሮፕላን

    የፎቶው ባለመብት, US Central Command

    የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ ምሽቱን ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ በበርካታ የኢራን ከተሞች ፍንዳታዎች ተሰምተዋል

    ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ “ከባድ ጥቃት” እንደደረሰ እና ይህም ሰሞኑን ለተገደሉ ሦስት አሜሪካውያን ወታደሮች “ክብር” ሲባል የተፈፀመ እንደሆነ ተናገሩ።

    ሦስቱ ወታደሮች የተገደሉት ኢራን በዮርዳኖስ እና በኢራቅ በፈፀመቻቸው ጥቃቶች ነው።

    ጥቃቱ ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት እንደቀጠለ እና ትናንት ምሽት አዲስ ጥቃት እንደተከፈተ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ገልጿል።

    በመላው ኢራንም ከፍተኛ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።

    ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል እንደዘገበው አሜሪካ በፈፀመቻቸው ጥቃቶች ታብሪዝ፣ ቻባሃር፣ ኮናራክ፣ ባንዳር ባንዳር ማህሻህር እና ባንዳር ኢማም ኻሜኒን ጨምሮ በርካታ ከተሞች ተመትተዋል።

    በሌላ በኩል ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ወሽመጡን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ፍንዳታ እንዳጋጠማቸው የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ዘብ፣ መርከቦቹ “ደኅንነቱ ባልተጠበቀ እና አደገኛ በሆነው ደቡባዊ መስመር እየተጓዙ ሳሉ ፍንዳታ አጋጥሟቸዋል” ብሏል።

    ሴንትኮም ግን ይህን አስተባብሏል።

    አሜሪካ ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በመርከቦች ላይ የምትፈፅመውን ይህንን ጥቃት ለማስቆም “ወታደራዊ ሥፍራዎችን እና የመገናኛ ኔትዎርኮችን” ዒላማ እንዳደረገች ገልጻለች።

    ኢራን በበኩሏ ለጥቃቱ በሶሪያ ድንገተኛ ጥቃት በመፈፀም እና በዮርዳኖስ አቃባ አየር ማረፊያ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላንን ዒላማ በማድረግ አፀፋ መስጠቷን ገልጻለች።

    በቀጠናው ያለው ግጭት ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን የኩዌት ወታደራዊ ኃይል የኢራንን የድሮን ጥቃት አክሽፌያለሁ ብሏል።

  10. ኢራን በኩዌት እና በባህሬን የሚገኙ የአሜሪካ ይዞታዎችን መምታቷን አስታወቀች

    ከርቀት የሚታይ ቃጠሎ እና ጭስ

    የፎቶው ባለመብት, Vahid Online

    የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ በበርካታ የኢራን ክፍሎች ውስጥ ሌሊቱን ጥቃት ፈጽማለች

    አሜሪካ በኢራን ላይ ለተከታታይ ዘጠነኛ ቀን ጥቃት መፈጸሟን ካስታወቀች በኋላ የኢራን አብዮታዊ ዘብ በኩዌት እና በባህሬን ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎችን መምታቱን አስታወቀ።

    ዘቡ ባወጣው መግለጫ በአሜሪካ ሠራዊት ይዞታ ላይ በፈጸመው የአጸፋ የድሮን ጥቃት “የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ የራዳር ሥርዓትን” ጨምሮ የተለያዩ ዒላማዎችን ማጥቃቱን እና “የጠላት የራዳር ሥርዓትን ሙሉ ለሙሉ” ማውደሙን ገልጿል።

    ጨምሮም እዚያው ኩዌት ውስጥ አሊ አል-ሳሌም ጦር ሰፈር ላይ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት የድሮኖች መጠለያን እና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ዒላማ ማድረጉን አመልክቷል።

    ዛሬ ማለዳ ኢራን በአካባቢው አገራት ውስጥ ያሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ በማድረግ ጥቃት መፈጸሟን የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ሲሆን ኩዌት እና ባህሬን ለነዋሪዎቻቸው ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል።

    የባሕሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እየተፈጸመ ካለው ጥቃት አንጻር ሕዝቡ “ተረጋግቶ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጥቃት መከላከያ ቦታ እንዲሸሸግ” አሳስቧል።

    የኩዌት ጦር ሠራዊትም ከኢራን በኩል የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶችን ለማክሸፍ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቆ፤ በአገሪቱ ውስጥ ከባድ የፍንዳታ ድምጽ የተሰማው ጥቃቱን ለማክሸፍ በሚወሰድ እርምጃ ምክንያት መሆኑን ለሕዝቡ አስታውቋል።

    መልሶ ካገረሸ ሳምንት ባለፈው የአሜሪካ እና የኢራን ጦርነት አሜሪካ በተከታታይ ዙር በኢራን ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎችን መምታቷን ስታስታውቅ፣ ኢራን ደግሞ በምላሹ በኩዌት እና ባህሬን የሚገኙ የአሜሪካ ይዞታዎችን ማጥቃቷን እየገለጸች ነው።

    የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ ሌሊት ላይ ዘጠነኛ ዙር ጥቃት መፈጸሙን የገለጸ ሲሆን፣ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ደግሞ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ዘግበዋል።

  11. ኢራን በሰሜን ኢራቅ በፈጸመችው ጥቃት የአሜሪካ ወታደር ተገደለ

    ሰሜን ኢራቅ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኢራን በሰሜን ኢራቅ በፈጸመችው ጥቃት አንድ የአሜሪካ ወታደር እንደተገደለ እና ሌላ ወታደር እንደቆሰለ የአገሪቱ ማዕከላዊ ዕዝ አስታወቀ።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እንደገለጸው፤ ወታደሩ የተገደለው ተመትቶ የወደቀ የኢራን ድሮንን “ለማፈንዳት በተደረገ ሙከራ” ወቅት ነው።

    ሌሎች ብዙ የአሜሪካ ወታደሮች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተገልጿል።

    ኢራን እና አሜሪካ ለተከታታይ ስምንት ቀናት የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

    ባለፉት ቀናት ሁለቱም ወገኖች መሠረተ ልማቶች ላይ በደረሱ ጥቃቶች አንዳቸው ሌላቸውን ሲከስሱ ቆይተዋል።

    ዋሽንግተን በኢራን ወደቦች ላይ እገዳ ስትጥል ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታለች።

    ኢራን በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ቀጥላለች።

    የአሜሪካ ጦር እንዳለው፤ በኢራን ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ “አገሪቱ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት የምታደርስበትን አቅም ለማዳከም” ያለመ ነው።

    ኢራን በዮርዳኖስ ባደረሰችው ጥቀት ሁለት የአሜሪካ ወታደሮች ሲገደሉ አንድ ወታደር የደረሰበት እንዳልታወቀ መገለጹ ይታወሳል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በዮርዳኖስ ላደረሰው ጥቃት “በጽኑ እንደሚቀጣም” አክሏል።

    እስካሁን ድረስ የተገደሉ የአሜሪካ ወታደሮች ቁጥር 17 ደርሷል።