የኢራን ጦር በእስራኤል ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት እንደሚያቆም አስታወቀ
የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ ዕዝ የሆነው ካሀታም አል-አንቢያ፤ እስራኤል ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት እንደሚያቆም ይፋ አደረገ።
ዕዙ ባወጣው መግለጫ “የጦር ኃይሎቻችን የሚያካሂዱት ዘመቻ መቆሙን እናሳውቃለን” ብሏል።
ነገር ግን በደቡብ ሊባኖስ የሚፈጸመው ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ ኢራን “ከዚህ ቀደም ከነበረው በባሰ ሁኔታ ምላሽ ትሰጣለች” ሲል አስጠንቅቋል።
እስራኤል በደቡባዊ ቤይሩት ላይ ጥቃት ማድረሷን ተከትሎ ኢራን የአጸፋ ምላሽ መስጠት የጀመረችው ትናንት እሑድ ሲሆን፤ የእስራኤል ጦርም በኢራን ላይ ጥቃት ፈጽሟል።
የቴህራን ከፍተኛ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ትናንት ምሽት በሰጡት ማስጠንቀቂያ ኢራን የተኩስ አቁሙ በመጣሱ የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ዝተዋል።
በሊባኖስ እና በእስራኤል መካከል ተደርሶ የነበረውን የተኩስ አቁም፤ ኢራን ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር የተደረሰው አጠቃላይ የተኩስ አቁም አካል አድርጋ ትወስደዋለች።