ቀጥታ, ሁቲዎች በሪያድ በሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ሳዑዲ መጠነ ሠፊ ወታደራዊ ዘመቻ ጀመረች

በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምረት፣ በየመን የሚንቀሳቀሱት እና በኢራን የሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሩን አስታወቀ። ወታደራዊ ዘመቻው በቀጥታ ታጣቂዎቹን እና ወታደራዊ አቅማቸው ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የጥምረቱ ቃል አቀባይ በመግለጫቸው ወቅት ተናግረዋል። ቃል አቀባዩ፣ ጥምረቱ በሁቲዎች ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ 136 ወታደራዊ ዒላማዎችን ማውደሙን ገልጸዋል። በተጨማሪም የዓለም አቀፍ መንግሥታት ዕውቅና ላለው የየመን መንግሥት ተዋጊዎች የአየር ኃይል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. አሜሪካ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ ከባድ ማዕቀብ ጣለች

    የቀድሞው የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ዳኛ የኖቤል የሰላም ሽልማት ካሸነፉ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ዋሽንግተን ፍርድ ቤቱ ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

    የትራምፕ አስተዳደር ፍርድ ቤቱ በአሜሪካ እና እንደ እስራኤል ያሉ አጋሮቹ ላይ የሚያደርገውን ምርመራ ለማደናቀፍ በከፈተው የዘመቻ አካል በአይሲሲ ላይ ከባድ ማዕቀብ መጣሉን አስታውቋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የኖቤል የሰላም ሽልማት ለደቡብ አፍሪካዊቷ የቀድሞ የፍርድ ቤቱ እና የሌሎች ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ዳኛ ናቪ ፒሌይ ከተሰጠ በኋላ ማዕቀቡን አስታውቀዋል።

    ትራምፕ ዳኛዋ የዘንድሮውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፍ ቀደም ብለው ነቅፈዋል።

    “ከዚህ አፈንጋጭ ፍርድ ቤት ጋር የሚደረጉ ልውውጦችን እንከለክላለን፤ ሀብታቸውን እናቆማለን እና በእኛ ላይ የመሥራት አቅሙን እናዳክማለን" ሲሉ ሩቢዮ ተናግረዋል።

    "አሜሪካ እና የአሜሪካ ሕዝብ ለዚህ የውሸት ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ስልጣን ተገዢ አይደሉም።”

    ማዕቀቦቹ ፍርድ ቤቱ ከአሜሪካ የፋይናንስ አገልግሎቶች እና ከቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሚነጥል ሲሆን፤ የአሜሪካን ዶላር እንኳን ከመጠቀም የሚከለክል ነው።

    ማዕቀቡ ከፍርድ ቤቱ ጋር የንግድ ግንኙነት ላላቸው የአሜሪካ ኩባንያዎች እና ግለሰቦች ግንኙነታቸውን እንዲያቆሙ የስድስት ወር የጊዜ ገደብ አስቀምጧል።

    አይሲሲ እርምጃውን በሕግ የበላይነት እና በዓለም አቀፍ ሥርዓት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት በማለት አውግዞታል።

    የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ቶሞኮ አካኔ ፍርድ ቤቱ ቁጥር ስፍር ለሌላቸው የከባድ ወንጀሎች ሰለባዎች ሲል በሕግ እና በማስረጃ ላይ ብቻ በመመራት፣ በነጻነት እና ከአድልዎ ውጭ ሆኖ ሥልጣኑን መወጣቱን ይቀጥላል ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቷ የአይሲሲ አባላትን ድጋፍም ጠይቀዋል።

    “ይህ አንድን ተቋም ከመከላከል ባለፈ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተውን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ስለመጠበቅ ነው” ብለዋል።

    የአሜሪካን እርምጃ የመብት ተሟጋቾችም አውግዘዋል።

  2. በጣሊያን አምስት ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጣ 30 ሺህ ጠርሙስ የወይን ጠጅ ተሰረቀ

    በጣሊያን ተስከኒ ባለፈው ቅዳሜ ሌቦች ከወይን ጠማቂ ኩባንያ መጋዘን ውስጥ 30 ሺ ጠርሙስ ወይን ጠጅ መስረቃቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    ቢያንስ ሰባት ይሆናሉ የተባሉ ጭምብል ያጠለቁ ዘራፊዎች የክትትል መሣሪያዎችን በማክሸፍ በመኪና ጭነው ዘረፋውን መፈፀማቸው ተነግሯል።

    ዝርፊያው በጣሊያን በግዝፈቱ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን የወይን መጥመቂው ገልጿል።

    የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ ሬንዞ ኮታሬላ “በዚህ መጠን እና ዋጋ ልክ በጣሊያን የተፈፀመ ዝርፊያ ሆኖ አያውቅም” ብለዋል።

    “ሁለት የጭነት መኪና እቃ እንደ ጉም ሊተን አይችልም። የተስከኒ መንገዶች በካሜራ የተሞሉ ናቸው። ምናልባትም በትንሽ ዕድል ቢያንስ የተሰረቁብንን የተወሰኑ ጠርሙሶች እናገኛለን።”

    ሥራ አስፈፃሚው ለፋይናንሺያል ታይምስ “እነዚህ ወይኖች ትልቅ ዋጋ ያላቸው ናቸው። እናም ሌቦቹ ሳይታወቅባቸው በመላው ዓለም እንዴት አድርገው ሊሸጡ እንደሚችሉ አላውቅም” ብለዋል።

    ኩባንያው በጠርሙስ ከ150 እስከ 500 ዩሮ የሚሸጠው ወይን ዝርፊያ ሌቦቹ የወይን ጠጅ አዋቂ እና የቅርብ መረጃ ያላቸው እንዲሆኑ ያምናል።

    ዝርፊያው መፈፀሙ የታወቀው ከሁለት ቀን በኋላ ሠኞ ዕለት ሲሆን፤ እስካሁን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለው ተጠርጣሪ የለም።

  3. የሳዑዲ አረቢያ ጦር በየመን በሚንቀሳቀሱት የሁቲ አማፂያን ላይ በርካታ ዙር ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታወቀ

    በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምረት፣ በየመን የሚንቀሳቀሱት እና በኢራን የሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሩን አስታወቀ።

    ወታደራዊ ዘመቻው በቀጥታ ታጣቂዎቹን እና ወታደራዊ አቅማቸው ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የጥምረቱ ቃል አቀባይ በመግለጫቸው ወቅት ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ፣ ጥምረቱ በሁቲዎች ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ 136 ወታደራዊ ዒላማዎችን ማውደሙን ገልጸዋል። በተጨማሪም የዓለም አቀፍ መንግሥታት ዕውቅና ላለው የየመን መንግሥት ተዋጊዎች የአየር ኃይል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።

    የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት አርብ ዕለት የሁቲ አማፂያን በሪያድ በሚገኝ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ሦስት የአገሪቱ ዜጎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ይፋ አድርጓል።

    የአገሪቱ ሲቪል አቪየሽን በኤክስ ገጹ ላይ ጥቃቱ “በርካታ የሳዑዲ እና የሌላ አገር ዜጎች ላይ ጉዳት አድርሷል” ብሏል።

    የሁቲ አማፂያን ሐሙስ ዕለት ሁለት ጥቃቶች መፈጸማቸው የተገለጸ ሲሆን የመጀመሪያው አውሮፕላን ማረፊያው ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የሳዑዲ አረቢያ ብሔራዊ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን 'ሳውዲያ' አውሮፕላንን መትቷል።

    አየር መንገዱ ከተገደሉት መካከል አንዱ የአውሮፕላኑ አብራሪ መሆኑን አስታውቋል። የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣኑ የአየር ትራፊክ እንቅስቃሴ ወደ መደበኛው ሁኔታ መመለሱን ገልጿል።

    የሁቲ ታጣቂዎች ሐሙስ ዕለት አውሮፕላን ማረፊያውን በሁለት ባሊስቲክ ሚሳይሎች ማጥቃታቸውን አስታውቀዋል።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ሳዑዲ ከየመን ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ናጅራን ከተማ የሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሁም በስተሰሜን በኩል የሚገኘውን ኻሚስ ሙሻይት የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ዒላማ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ሳዑዲ አረቢያ እነዚህን ጥቃቶች አላረጋገጠችም።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አርብ ዕለት ሁቲዎች በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ ሁለት አየር ማረፊያዎች ላይ የፈጸሙትን ጥቃት አውግዘዋል።

    ትራምፕ ስለ ጥቃቶቹ በጋዜጠኞች ሲጠየቁ "ጥሩ አይደለም። ጥሩ ነገር አይደለም። በዚህ ደስተኛ አይደለሁም" ብለዋል።

    ሳውዲ አረቢያ ሐሙስ ዕለትበዋና ከተማዋ ሪያድ በሚገኘው የንጉሥ ኻሊድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ በተፈፀሙ ሁለት ጥቃቶች ሦስት የአገሪቱ ዜጎች መገደላቸውን አስታውቃለች።

    ቡድኑ የሪያድ አውሮፕላን ማረፊያን ማጥቃቱን ካስታወቀ በኋላ ሠራተኞች ዒላማ ሊሆኑ ከሚችሉ የኢነርጂ ተቋማት እንዲርቁ አስጠንቅቋል።

    ከጥቃቱ በኋላ ሉፍታንዛ እና ኤር ኢንዲያ ወደ ሪያድ የሚያደርጓቸውን በረራዎች አቋርጠው ነበር።

  4. "ከመንግሥት ማረጋገጫ ሲያገኝ" ወደ አክሱም እና ሽረ በረራ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገለጸ

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ "ከመንግሥት ማረጋገጫ ሲያገኝ" ወደ ትግራይ ክልል አክሱም እና ሽረ ከተሞችም በረራ እንደሚጀምር ለቢቢሲ ገለጸ።

    አየር መንገዱ ይህን ያለው ከቀጣዩ እሁድ ጀምሮ የመቀለ በረራውን እንደሚጀምር ዛሬ ዓርብ መስከረም 29/2019 ዓ.ም በፌስቡክ ገጹ ባወጣው አጭር መግለጫ ከገለጸ በኋላ ነው።

    እሁድ ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ በረራ ለመጀመር ነገ የአውሮፕላን ማረፊያውን ሁኔታ የሚገመግም የኢንስፔክሽን ቡድን እንደሚላክ የአየር መንገዱ የንግድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያዴቻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    በክልሉ ወደሚገኙ ሦስት መዳረሻዎች የሚደረገው በረራ መቋረጡን አየር መንገዱ ያስታወቀው የትግራይ ኃይሎች መስከረም 13፣ 2019 ዓ.ም. በክልሉ የሚገኙትን ሦስት አውሮፕላን ማረፊያዎች "መቆጣጠራቸው" ከተሰማ በኋላ ነበር።

    ወደ መቀለ በቀን 6 በረራ እንደሚደረግ የተናገሩት አቶ ለማ፣ የተጓዞች ቁጥር ታይቶ የበረራው ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ገልጸዋል።

    በሌሎች የክልሉ ከተሞች የተቋረጠው በረራ መቼ እንደሚጀመር በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም "ከመንግሥት ማረጋገጫ እስከሚገኝ ድረስ" ወደ አክሱም እና ሽሬ በቅርቡ በረራ እንደማይጀመር ተናግረዋል።

    አየር መንገዱ ከሁለት ሳምንት በኋላ ወደ መቀለ የሚያደርገውን በረራ እንደሚጀምር የገለጸው የኤርትራ ወታደሮች ወደ ክልሉ ዘልቀው መግባታቸው እየተዘገበ ባለበት እና አገራቱ እርስ በእርሳቸው እየተካሰሱ ባሉበት ወቅት ነው።

  5. ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ትንኮሳ ስትፈጽም ነበር ስትል ኤርትራ ከሰሰች

    ኢትዮጵያ ወረራ እንደተፈጸመባት በመግለጽ ለተባበሩት መንግሥታት ደብዳቤ መጻፏን ተከትሎ ኤርትራ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ትንኮሳ ስትፈጽም ቆይታለች በማለት ምላሽ ሰጠች።

    የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረአብ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ የኤርትራን ሉዓላዊነት የሚጻረሩ ትንኮሳዎች ስትፈጽም ነበር ብለዋል።

    ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት "በድርድር ወይም በኃይል የባሕር በር ለማግኘት” ዓላማ እንዳላቸው በመግለጽ እና የኤርትራ ነጻነት ላይ ጥያቄ በማንሳት የኤርትራን ሉዓላዊ ግዛት መያዝን የሚመለከቱ ንግግሮች ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመልክተዋል።

    ይህ የአቶ የማነ ጽሑፍ የወጣው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው በመግባት ወረራ ፈጽመዋል በማለት ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ደብዳቤ ከጻፉ በኋላ ነው።

    ኢትዮጵያ በኤርትራ ተፈጽሞብኛል ላለችው ወረራ “ራሷን ከመከላከል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት” በመግለጽ የተባበሩት መንግሥታት ያለውን ሁኔታ እንዲገነዘብ ጠይቃለች።

    የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ፣ ኢትዮጵያ ትንከሳዎችን ስትፈጽም ታግሳ መቆየቷን ከመግለጽ ባሻገር ባለፉት ቀናት ሲዘገብ እና ኢትዮጵያ ላቀረበችው የወረራ ክስ እንዲሁም ወታደሮቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባታቸውን በተመለከተ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጡም።

  6. አሜሪካ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ ማዕቀብ ጣለች

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ላይ ማዕቀብ መጣሉን ሮይተርስ ዘገበ።

    አገሪቷ ማዕቀቡን የጣለችው ከቀድሞ የፍርድ ቤቱ ዳኞች አንዷ የሆኑት ናቪ ፒላይ የኖቤል የሰላም ሽልማት ካሸነፉ ከሰዓታት በኋላ ነው።

    የፍርድ ቤቱ ምክትል አቃቤ ሕግ ናዣት ሻሚን ካን ማዕቀቡን አውግዘው፣ እርምጃው ፍርድ ቤቱ ሥራውን ከመሥራት እንደማያግደው ተናግረዋል።

    የትራምፕ አስተዳደር የጦር፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀሙ እንዲሁም የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ከሚዳኙበት ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ጋር ለረዥም ጊዜ የሻከረ ግንኙነት ነው ያለው። ቀደም ሲልም በፍርድ ቤቱ አቃቤ ሕግ እና በዳኞቹ ላይ ማዕቀብ ጥሏል።

    ዛሬ የተላለፈው ውሳኔም ለፍርድ ቤቱ አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎችን በመቅጣት የበለጠ ሊባባስ ይችላል ተብሏል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ለሮይተርስ ባጋሩት መግለጫቸው “ፕሬዚደንት ትራምፕ ፍርድ ቤቱ አሜሪካዊያንን እንዲከስ በፍፁም አይፈቅዱም” ብለዋል።

    “ለዚህም ነው ዛሬ አሜሪካ በፍርድ ቤቱ ላይ ማዕቀብ የጣለችው። ከዚህ ፍርድ ቤት ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችን እናግዳለን፤ የሃብት ምንጫቸውን እንቆርጣለን፤ የመሥራት አቅሙን እናዳክማለን” ሲሉም አክለዋል።

    የአይሲሲ አቃቤ ሕግ ካን በበኩላቸው “ እርምጃዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕግ የበላይነትን እና አንድ ገለልተኛ የፍትህ ተቋም የሚያከናውነውን ሥራ ለማዳከም የታሰቡ ናቸው” ሲሉ ማዕቀቦቹ መወገዝ አለባቸው ብለዋል።

    አሜሪካ ፍርድ ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁን ጨምሮ በእስራኤል ባለሥልጣናት ላይ ያወጣውን የእስር ትዕዛዝ እንዲሁም ከዚህ ቀደም በአፍጋኒስታን የአሜሪካ ወታደሮችን ድርጊት በተመለከተ ያደረገውን ምርመራ አውግዛለች።

    ዘ ሄግ ኔዘርላንድስ የሚገኘው ፍርድ ቤቱ የአውሮፓ ኅብረት እና ከአሜሪካ እና ቱርክ በስተቀር ሁሉንም የኔቶ አባላትን ጨምሮ 125 አባል አገራት አሉት።

  7. በታንዛኒያ በደረሰ የመኪና አደጋ ቢያንስ 29 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ጉዳት ደረሰባቸው

    በታንዛኒያ ትናንት ምሽት በደረሰ የመኪና አደጋ ቢያንስ 29 ሰዎች ሲሞቱ፣ 30 የሚሆኑት ጉዳት ደረሰባቸው።

    አደጋው የደረሰው ከመዲናዋ ዳሬ ሰላም 174 ኪሎ ሜትር በሚርቀው በምሥራቃዊ ሞሮጎሮ ክልል ውስጥ በሚገኘው ምካምባራኒ መንደር ነው።

    አውቶብሱ ከዳሬ ሰላም ተነስቶ ወደ ደቡባዊ ታንዛኒያ ምቤያ ከተማ እየተጓዘ ነበር።

    የአካባቢው ፖሊስ ኮማንደር አንድሪው ካንቲምቦ እንዳሉት አደጋው የደረሰው መንገደኞችን ያሳፈረው አውቶብስ ከጭነት ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ነው።

    አውቶብሱ ከተጋጨ በኋላ በእሳት የተያያዘ ሲሆን በዚህም ተሳፍረው የነበሩ 28 ሰዎች ሲሞቱ በጭነት መኪናው ውስጥ የነበረ አንድ ሰውም ሕይወቱ አልፏል።

    ከሞቱት በተጨማሪ 30 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነም ኮማንደሩ ገልጸዋል።

    “ከግጭቱ በኋላ አውቶብሱ ወዲያውኑ በእሳት በመያያዙ አብዛኞቹ የሞቱት ወይም ጉዳት የደረሰባቸው ተሳፋሪዎች መውጣት አልቻሉም ነበር” ብለዋል።

    የሟቾችን ማንነት ለመለየትም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ኮማንደሩ አክለዋል።

    በዚያው ምሽት በደረሰ ሌላ አደጋም ሦስት የፖሊስ መኮንኖችን ጨምሮ የአራት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ሰባት ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    የፖሊስ መኮንኖቹ ወደ ሥራ ቦታቸው እየሄዱ ሳለ የጭነት መኪና ከመኪናቸው ጋር በመጋጨቱ አደጋው መድረሱን ፖሊስ ገልጿል።

  8. የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸነፉ

    የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ናቪ ፒላይ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸነፉ።

    ደቡብ አፍሪካዊቷ ፒላይ "ለሰላም፣ ዓለም አቀፍ ሕግን ለማስከበር እንዲሁም ለጦር እና ለዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተጠያቂነት እንዲኖር ላደረጉት አስተዋፅኦ" ከኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

    በደቡብ አፍሪካ ደርባን የተወለዱት ፒላይ፣ እአአ በ1967 በደቡብ አፍሪካ ናታል ግዛት የሕግ አገልግሎት በመስጠት የመጀመሪያዋ ሴት ነበሩ።

    የሰብዓዊ መብት ሥራ ላይ የተሰማሩትም በአፓርታይድ ወቅት ሲሆን የራሳቸውን የሕግ አገልግሎት በመስጠት እና በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን የመጀመሪያዋ ነጭ ያልሆኑ ሴት ለመሆን በቅተዋል።

    ፒላይ ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ ለአፓርታይድ ተቃዋሚዎች ጥብቅና ከቆሙ በኋላም በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የሩዋንዳ ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን ተመርጠዋል።

    በዚያም በዳኝነት እና በፕሬዚደንትነት ለስምንት ዓመታት ያህል አገልግለዋል።

    የ85 ዓመቷ ፒላይ በእስራኤል በኃይል በተያዘው የፍልስጤም ግዛት የተፈፀሙ ወንጀሎችን የመረመረውን የተመድ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ኮሚሽንም ከአውሮፓውያኑ 2021 እስከ 2025 ድረስ መርተዋል።

    በ2025 የወጣው የኮሚሽኑ የምርመራ ሪፖርትም እስራኤል በጋዛ “የዘር ማጥፋት” እንደፈፀመች ደምድሟል።

    ሪፖርቱ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እና በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ዮቭ ጋላት በመግለጫዎቻቸው ኮሚሽኑን “የዘር ማጥፋት ኮሚሽን” እያሉ እንዲጠቅሱት አድርጓል።

    እስራኤል በሪፖርቱ የተቆጣች ሲሆን የምርመራ ውጤቱን ውድቅ አድርጋለች። ከዚህም በተጨማሪ ሦስት የኮሚሽኑን ባልደረቦች “የሃማስ ወኪሎች ሆነው የሚያገለግሉ” ስትል ከስሳለች።

    ፒላይ አሁን ላይ የምያንማር የዘር ማጥፋት ክስ በሚታይበት ዓለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት ዳኛ ናቸው።

    ፒላይ ሽልማቱን እንዳሸነፉ ሲነገራቸው እውነት መሆኑን ለማመን መቸገራቸውን ተናግረዋል።

    “ ቀልድ መሆን አለበት” ያሉት ፒላይ፣ "አድናቆታችሁ ለእኔ ብዙ ነገር ማለት ነው፤ ግን እንደ የሕግ ሰው እና ዳኛ ይህንን ማጣራት አለብኝ” ሲሉ ንግግራቸውን በቀልድ አዋዝተዋል።

    ቀጥለውም “ ትንሽ ካጨበጨባችሁልኝ ሽልማቱን ለትራምፕ ላጋራ እችላለሁ” ሲሉም ባለፈው ዓመት የኖቤል የሰላም ተሸላሚ የሆኑት ማሪያ ኮሪና ማቻዶ ሜዳሊያቸውን ለአሜሪካው ፕሬዚደንት መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

  9. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቀለ የሚያደርገውን መደበኛ በረራ ሊጀምር ነው

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጊዜያዊነት ተቋርጦ የነበረውን ወደ መቀለ ከተማ የሚያደርገውን መደበኛ በረራ ጥቅምት 1/ 2019 ዓ.ም. እንደሚጀምር አስታወቀ።

    አየር መንገዱ በፌስቡክ ገጹ ዛሬ ዓርብ መስከረም 29/2019 ዓ.ም ባወጣው አጭር መግለጫ ነው ከቀጣዩ እሁድ ጀምሮ የመቀለ በረራውን እንደሚጀምር ገልጿል።

    የትግራይ ኃይሎች መስከረም 13 2019 ዓ.ም. በክልሉ የሚገኙትን ሦስት አውሮፕላን ማረፊያዎች "መቆጣጠራቸው" ከተሰማ በኋላ ነበር አየር መንገዱ ወደ ትግራይ ክልል የሚደረጉ በረራዎችን ለጊዜው ማቋረጡን የገለፀው።

    በትግራይ ክልል በሚገኙ ሦስት ከተሞች፣ ማለትም መቀለ፣ አክሱም እና ሽሬ የሚያደርገውን በረራ ከረቡዕ መስከረም 13/2019 ዓ.ም. ጀምሮ ማቋረጡን አየር መንገዱ በወቅቱ ባወጣው መግለጫው ላይ ጠቅሷል።

    አየር መንገዱ በጊዜያዊነት በረራ ማቋረጡን ካሳወቀ ከ16 ቀናት በኋላ ባወጣው የዛሬው መግለጫው የመቀሌውን በረራ እሁድ ጥቅምት 1 እንደሚጀምር ቢገልጽም፣ በሌሎቹ ሁለት ከተሞች ስላቋረጠው በረራ ግን ያለው ነገር የለም።

    የመቀሌ ከተማን የመከላከያ ሠራዊት እና አጋሮቹ ከባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ጀምሮ መቆጣጠራቸው ይታወቃል።

    ጦርነቱ ዳግም ከተቀሰቀሰ በኋላ ተቋርጦ የነበረው ወደ ላሊበላ ከተማ የሚደረገው በረራ ከቅዳሜ መስከረም 23 ጀምሮ መጀመሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልፀዋል።

  10. ትራምፕ በኅዳር ወር ከሚካሄደው ምርጫ በፊት ኢራን ላይ ጥቃት እንደማይፈጸም ተናገሩ

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመላው አገሪቱ በኅዳር ወር ከሚካሄደው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በፊት ኢራን ላይ ጥቃት እንደማይፈጸም ተናገሩ።

    ይህ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ከተሰማ በኋላ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ መረጋጋት ታይቷል።

    ከኢራን ጋር “ውጤታማ ንግግር” እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ የውይይቱን ዝርዝር ግን ከመናገር ተቆጥበዋል።

    “ከአጋማሽ ዘመን ምርጫ አስቀድሞ ኢራን ላይ ጥቃት አንፈጽምም” ያሉት ትራምፕ ከቴህራን ጋር “ፍሬያማ ውይይት” እያደረግን ነው ብለዋል።

    ትራምፕ ይህንን የተናገሩት ረቡዕ ዕለት ለጋዜጠኞች ከምርጫው በፊት ጥቃት ስለመፈጸም እያሰቡ ስለመሆኑ ከተናገሩ በኋላ ነው።

    ይህም የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከ4 በመቶ በላይ እንዲጨምር አድርጎ ነበር።

    ትራምፕ በኢራን ወደቦች ላይ የተጣለው እገዳ እንደሚቀጥል አስታውቀው ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሊኖራት አይገባም ሲሉም ተደምጠዋል።

    ትራምፕ ከአንድ ቀን በፊት ይዘውት ከነበረው አቋም ለውጥ ያደረጉበት ምክንያት አልታወቀም።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል “በታሪክ ከፍተኛ በሆነ መጠን የነዳጅ ፍሰት” መኖሩን በማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ ያስታወቁት ትራምፕ “ትናንትና ማታ ብቻ 22 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ” ማለፉን ተናግረዋል።

    “ከእነዚህ መካከል አንዲትም በርሜል ከኢራን የመጣ ወይም ወደ ኢራን የሄደ አልነበረም” በማለትም በአሜሪካ ሁሉም ግዛቶች ከሚካሄደው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በፊት በማንኛውም ጊዜ በኢራን ላይ ጥቃት አንሰነዝርም ብለዋል።

    ምንም እንኳን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ሁለቱ አገራት አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ ምንም ዓይነት ጥቃቶች ባይፈጽሙም ፕሬዚዳንቱ ከምርጫው በኋላ መቼ ጥቃቶችን ለመፈጸም እንዳሰቡ በግልጽ አልተናገሩም።

    ባለፈው ወር ትራምፕ፣ ኢራን ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር ስትል ጦርነቱን እያራዘመችው እንደሆነ በመግለጽ፣ ጦርነቱ ከምርጫው በኋላ ወዲያውኑ እንደሚያበቃ ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር።

    ረቡዕ ዕለት ‘ዘ አትላንቲክ’ ዋይት ሐውስ በኢራን ዒላማዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችል ዕቅድ ፔንታጎን እንዲያቀርብ ግፊት እያደረገ ስለመሆኑ ዘግቧል።

    አንድ የዋይት ሐውስ ባለሥልጣን “የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ በማንኛውም ጊዜ ሁሉም አማራጮች አሏቸው” ሲሉ ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል።

    "ኢራን ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል፤ ሁኔታዎቹም በአንድ ወይም በሌላ መንገድ፣ ማለትም በቀላል ወይም በከባድ መንገድ፣ ሊፈቱ ይችላሉ። ሁሉም አማራጮች በፕሬዚዳንት ትራምፕ እጅ ናቸው፤ እርሳቸውም ለአሜሪካ የሚበጀውን እርምጃ ይወስዳሉ" ሲሉ ባለሥልጣኑ ገልፀዋል።

  11. ደቡብ አፍሪካ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የገቡ ሰዎች የጥገኝነት ጥያቄ እንዲያቀርቡ የሚፈቅደውን መመሪያ ሰረዘች

    የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የገቡ ሰዎች የሚያቀርቡትን የጥገኝነት ማመልከቻ እንዲቀበል የሚፈቅደውን አወዛጋቢ መመሪያ መሰረዙን አስታወቀ።

    መመሪያው የተሰረዘው ተግባራዊ በሆነ በጥቂት ቀናት ውስጥ ነው።

    ይህ እርምጃ የተወሰደው በጆሃንስበርግ አቅራቢያ በሚገኘው ሶዌቶ እና የባሕር ዳርቻዋን ደርባንን ጨምሮ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የፀረ-ስደተኞች የተቃውሞ አመጽ ከተካሔደ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።

    የደቡቡ አፍሪካ የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፣ መመሪያው በወጣ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከአቅም በላይ የሥራ ጫና መፈጠሩን እና የመንግሥት ሠራተኞችም ለአደጋ መጋለጣቸውን ገልጿል።

    በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ የገቡ ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄ የማመልከት መብትን ማጣት የለባቸውም በሚል የአገሪቱ የሕገ-መንግሥት ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ መመሪያው ሥራ ላይ የዋለው መስከረም 20/2019 ዓ.ም. ነበር።

    ይህም በብዙ የመንግሥት ቢሮዎች ውጭ ረጅም የስደተኞች ሰልፎች እንዲፈጠሩ አድርጓል።

    በደቡብ አፍሪካ የስደት ጉዳይ ለረጅም ጊዜ አከራካሪ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ የፍርድ ቤቱ ውሳኔም በአንዳንድ የፀረ-ስደተኛ ቡድኖች ዘንድ ቁጣ በመፍጠር የአመጽ እንቅስቃሴን አስከትሏል።

    ሐሙስ ዕለት በነበሩ የአመጽ ተግባራት መኪኖች ተቃጥለዋል፤ በውጭ ዜጎች ባለቤትነት የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ሱቆችም ጥቃት ደርሶባቸዋል።

    መንግሥት ዛሬ የወሰደው መመሪያውን የመሰረዝ እርምጃ የፖለቲካ ውሳኔ እንዳልሆነ ገልፆ፣ የሕገ-መንግሥት ፍርድ ቤቱን ውሳኔ የሚያከብርበትን ሌሎች መንገዶች እንደሚፈልግ አስታውቋል።

  12. ሩሲያ በአውቶብስ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 30 ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ

    የዩክሬን ባለሥልጣናት በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል በምትገኘው ክራማቶርስክ ከተማ ሩሲያ በሁለት የመንገደኞች አውቶቡሶች ላይ በፈፀመችው የቦምብ ጥቃት ቢያንስ 30 ሰዎች መገደላቸውን ተናገሩ።

    ባለሥልጣናቱ እንዳሉት የክራማቶርስክ አካል በሆነችው ቢሌንኬ መንደር ተጨማሪ ሦስት ሰዎችም ተገድለዋል።

    ሌሎች 18 ሰዎችም መቁሰላቸውን የተናገሩት የዶኔትስክ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ቫዲም ፊላሽኪን፣ ሩሲያ በተቻለ መጠን "ብዙ ሰላማዊ ሰዎችን ለመግደል ተሳፋሪዎችን የሚጭኑ አውቶቡሶችን ዒላማ አድርጋለች" ሲሉ ከስሰዋል።

    ክራማቶርስክ እና በአቅራቢያዋ የምትገኘው ስሎቪያንስክ፣ "የምሽግ ቀለበት" በመባል የሚታወቁ ሲሆን ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግባቸው የከተሞች ሰንሰለት አካል ናቸው። ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እንዳሉት፣ ሩሲያ እነዚህን ከተሞች ለመቆጣጠር የምትሞክረው በምሥራቅ ዩክሬን የሚገኘውን አጠቃላይ የዶንባስ የኢንዱስትሪ ክልል በቁጥጥሯ ስር ለማድረግ በማሰብ ነው።

    የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ "ይህ ጥቃት ያለአጸፋ ምላሽ እንዲሁ አይተውም" ብለዋል።

    በቴሌግራም ላይ ባጋሩት ጽሑፍ ላይ "ሩሲያ በዶንባስ ውስጥ ያለውን ሕይወት በሙሉ ለማጥፋት እየሞከረች ነው፤ እናም ዓለም ለዚህ ምላሽ መስጠት አለበት። ሩሲያውያን ላደረሱት ሞት ሁሉ የሚገባውን ያህል የኃይል ምላሽ ይስጡ።"

    የአካባቢው አቃቤ ሕግ ቢሮ ያጋራቸው ምስሎች የሚቃጠለውን አውቶቡስ ከስብርባሪዎች ጋር እና ከተጎዱ መንገደኞች ጋር የሚያሳይ ነው።

    ሞስኮ ስለጥቃቱ እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም። ሩሲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመላው ዩክሬን የምትፈጽመውን ትቃት አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን የሰላማዊ ሰዎች ሞትም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

    እንደ መንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ከሆነ ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ ብቻ የተገደሉት ዩክሬናውያን ቁጥር እአአ በ2025 ከተገደሉት የበለጠ ነው።

  13. ሁቲዎች የሳዑዲ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት ፈጽመው የመንገደኞች አውሮፕላን ላይ ጉዳት አደረሱ

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በሳዑዲ አረቢያ ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ሐሙስ ዕለትም አጠናክረው በመቀጠል የአውሮፕላን ማሪፊያ እና የነዳጅ ተቋማቷን በሚሳዔል ማጥቃታቸው ተሰማ።

    በጥቃቱ ሦስት ሰዎች መሞታቸው ሲገለጽ አንድ አውሮፕላንም በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    አንድ የዐይን እማኝ ሐሙስ ዕለት በሪያድ በርካታ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ገልጸው ከእነዚህም መካከል በከተማዋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተከሰተው ትልቁ መሆኑን ተናግረዋል።

    በየመን የሚንቀሳቀሱት እና በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማፅያን፣ በሪያድ በሚገኘው የኪንግ ኻሊድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የባሌስቲክ ሚሳዔል ጥቃት መፈጸማቸውን ተናግረዋል። አማፅያኑ ለዚህ ምንም ዓይነት ማስረጃ ያላቀረቡ ሲሆን፣ የሳዑዲ ባለሥልጣናትም በጉዳዩ ላይ ወዲያውኑ የሰጡት አስተያየት የለም።

    ቡድኑ የሪያድ አውሮፕላን ማረፊያን ማጥቃቱን ካስታወቀ በኋላ ሠራተኞች ዒላማ ሊሆኑ ከሚችሉ የኢነርጂ ተቋማት እንዲርቁ አስጠንቅቋል።

    የፈረንሳይ ዜና ወኪል ያነጋገራቸው የዐይን እማኝ ከአውሮፕላን ማረፊያው የሚነሱ በረራዎች ተቋርጠው እንደነበር ተናግረው ተሳፋሪዎች ከአውሮፕላን ማረፊያው እንዲወጡ ተነግሯቸው ነበር ብለዋል።

    ምን ያህል በረራዎች እንደተስተጓጎሉ በግልጽ ባይታወቅም፣ ስማቸው እንዳይገለጽ በመጠየቅ ለኤኤፍፒ የተናገሩ ሰዎች ግን የመንገደኞች ማስተናገጃ ክፍሉ ግን በተሳፋሪዎች ተጨናንቆ እንደነበር እና ሰዎች አስቀድመው ያስገቧቸውን ሻንጣዎች ትተው እንዲወጡ እንደታዘዙ አስረድተዋል።

    ሐሙስ ዕለት በሪያድ የሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት ተፈጽሞ የሳዑዲ አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን በተተኳሽ መመታቱን እና በእሳት ከተያያዘ በኋላ ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዱን ስለጉዳዩ መረጃ ያላቸው ሦስት ሰዎች ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    መንገደኞች በአውሮፕላኑ ውስጥ አልነበሩም ብለው እንደሚያምኑ ተናግረው ነገር ግን ሰዎች ተጎድተው ሊሆን አንደሚችል ገልጸዋል።

    ሮይተርስ የተመለከተው እና ትክክለኛነቱን ያረጋገጠው ተንቀሳቃሽ ምስል ከአውሮፕላን ማረፊያው ጥቁር ጭስ ሲወጣ ያሳያል።

    የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት፣ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን እና የሳዑዲ አየር መንገድ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    ሉፍታንዛ እና ኤር ኢንዲያ ከሁቲ ትቃት በኋላ ወደ ሪያድ የሚያደርጓቸውን በረራዎች አቋርጠዋል።

    በሌላ ዜና የሳዑዲ ባለሥልጣናት በአየር ላይ ሳለ ተመትቶ እንዲወድቅ የተደረገ ፍንጥርጣሪ በሪያድ የሚገኝ መዋዕለ ሕጻናት እና ሕክምና ተቋም ላይ መውደቁን ተናግረዋል።

  14. ትራምፕ ከኢራን ጋር ስምምነት ማድረግ "የሚመርጡት ነገር አለመሆኑን" ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ልዩ መልዕክተኛቸው ስቲቭ ዊትኮፍ ከኢራን ጋር በሚያደርጉት ድርድር "በጣም ጥሩ" እየሠሩ መሆኑን ገልጸው ስምምነት ግን የሚመርጡት ውጤት እንዳልሆነ ተናገሩ።

    "በኢራን ስምምነት ላይ በጣም ጥሩ እየሰራ ነው። ስምምነቱ እኔ ማድረግ የምፈልገው ነገር እንዳልሆነ አስባለሁ፤ ነገር ግን ጦርነቱን ለማቆም ማንኛውንም ነገር ለመስጠት ፈቃደኛ ናቸው" ሲሉ ትራምፕ በቴክሳስ ሳን አንቶኒዮ በተካሄደው የምርጫ ዘመቻ ላይ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።

    “የኒውክሌር ጦር መሳሪያ በፍፁም አይኖራቸውም” ሲል አክለዋል።

    ትራምፕ በጋዛ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጥቀስ ዊትኮፍን “ታላቅ ተደራዳሪ” እና “አንዳንድ አስደናቂ ነገሮችን ያደረገ” ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ከኢራን ጋር የተደረገው ጦርነት በቅርቡ እንደሚቆምም ተናግረዋል።

    “ጦርነቱ ያበቃል፤ ይህም በጣም በቅርቡ ይሆናል። በጣም በቅርቡ መሆን አለበት” ካሉ በኋላ ኢራንን “የወደቀች አገር” በማለት ገልጸዋታል።

    ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት መገናኛ ብዙኃን ዋይት ሐውስ ከኅዳሩ ምርጫ በፊት በኢራን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በሚመለከት ፔንታጎን አማራጮችን እንዲያዘጋጅ መጠየቁን ከዘገቡ በኋላ ነው።

    አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ ቴህራን በቀጣናው በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ በሚሳኤልእና በድሮን ጥቃቶችን በመፈጸም ምላሽ ሰጥታለች።

    በተጨማሪም የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ የባህርወሽመጥን ዘግታለች።

    አሜሪካ እና ኢራን በሰኔ ወር በአደረዳሪዎቻቸው በኩል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

    ሁለቱ አገራት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መግባባት ባለመቻላቸው ስምምነቱ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል።

  15. በአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ላይ የደረሰው ጉዳት ከተነገረው በላይ መሆኑን ኢራን አስታወቀች

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ መከላከያ ኃይላቸው 81 የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ከጥቅም ውጭ አድርጓል የሚለውን ሪፖርት በመጠቀስ የደረሰው ጉዳት ከተነገረው በላይ ነው አሉ።

    አራጋቺ ሐሙስ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ ለአሜሪካ ምክር ቤት የቀረበው ሪፖርት በኢራን ጦርነት ዘመቻ ወቅት 81 ጦር አውሮፕላኖች በጦርነቱ መጥፋታቸው ወይንም መውደማቸው ይገልጻል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ወታደራዊ ጦር ሠፈሮች ያሉበትን ሁኔታ ለመፈተሽ ሴናተሮች ያቀረቡት ትኣቄ ተቀባይነት አላገኘም።

    “በግንቦት ወር የኮንግረስ የምርምር አገልግሎት የኢራን ጦር ኃይሎች 42 የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ማውደሙን ይፋ አድርጎ ነበር። አሁን 81 ደርሷል” ሲሉ ጽፈዋል።

    “ትክክለኛው የደረሰው ጉዳት ግን ከዚህም የባሰ ነው። ማስረጃ? አሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ደህንነታቸው የተጠበቀ ናቸው ያላቸውን ጦር ሠፈሮች ላይ ሴናተሮች ምልከታ እንዲያደርጉ አልፈቀደም” ሲሉ አጋራቺ አብራርተዋል።

    አራጋቺ በኤክስ ልጥፋቸው ላይ የአሜሪካ ኮንግረስ ምርምር አገልግሎት ያወጣውን ሪፖርት ፎቶ አንስተው አጋርተዋል።

    ሪፖርቱ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ 81 የጦር አውሮፕላኖች መጥፋታቸው ወይንም መውደማቸውን ዘርዝሯል።

    ሪፖርቱ የተዘጋጀው ከወጡ የዜና ዘገባዎች፣ የአሜሪካ መከላከያ እና ሴንቲኮም እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስቴር ቁጥጥር ቢሮ ያወጧቸው ሪፖርቶችን መነሻ በማድረግ እንደሆነ ተጠቅሷል።

    በሪፖርቱ ላይ የተቀመጠው ቁጥር ሊቀየር እንደሚችል ተገልጿል።

    ከየካቲትመጨረሻ 2026 ጀምሮ ኢራን በሳዑዲ አረቢያ፣ አረብ ኤምሬትስ፣ ኳታር፣ ኩዌት፣ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፣ ባህሬን እና ኦማን በሚገኙ ከ 20 በላይ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት እና የጦር ሰፈሮች ላይ በሚሳኤሎች እና ድሮኖች ጥቃት ሰንዝራለች።

  16. በአዲሱ ሹመት ውስጥ ሳይካተቱ የቀሩት ሚኒስትሮች እነማን ናቸው?

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት ዕጩ የካቢኔ አባሎቻቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው አስሹመዋል።

    በዚህም በቀደመው ካቢኔያቸው የነበሩ ሚኒስትሮች ባሉበት የቀጠሉ እና ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት የተዘዋወሩ ሲኖሩ በርካታ አዳዲስ ሚኒስትሮችን አካተዋል።

    በቀደመው ካቢኔ ውስጥ ከነበሩት ሚኒስትሮች መካከል ከአስር የሚበልጡት ቦታቸውን ለአዲስ ተተኪዎች ለቅቀዋል። ከመካከላቸውም የተወሰኑት በሌላ ኃላፊነት የተሾሙ ሲሆን የበርካቶቹ መዳረሻ ግን እስካሁን አልታወቀም።

    በአዲሱ የሚኒስትሮች ዝርዝር ውስጥ ሳይካተቱ የቀሩት ባለሥልጣናት እነ ማን ናቸው?

    1. አሕመድ ሽዴ የገንዘብ ሚኒስትሩ የነበሩ፣ አሁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ

    2. ሙፈሪያት ካሚል፣ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር የነበሩ፤ አሁን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ

    3. አብርሃም በላይ፣ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር የነበሩ፣ አሁን የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽነር

    4. ኢንጅነር አይሻ መሐመድ፣ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩ

    5. ጫልቱ ሳኒ፣ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር የነበሩ

    6. መላኩ አለበል፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር የነበሩ

    7. ዓለሙ ስሜ፣ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር የነበሩ

    8. ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩ

    9. በለጠ ሞላ፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የነበሩ

    10. ሃብታሙ ተገኝ፣ የማዕድን ሚኒስትር የነበሩ

    11. ካሳሁን ጎፌ፣ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር የነበሩ

    እነዚህ ሚኒስትሮች በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ ባይካተቱም በቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ በሚያደርጓቸው ሹመቶች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።

  17. ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ዘጠኝ ባለሥልጣናት ባሉበት ኃላፊነት ይቀጥላሉ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ መስከረም 28፣ 2019 ዓ. ም. በሰጡት ሹመት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ዘጠኝ ባለሥልጣናት ባሉበት ኃላፊነት ይቀጥላሉ።

    ተመስገን ጥሩነህ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የሚቀጥሉ ሲሆን፤ ጌዲዮን ጤሞቲዮስ (ዶ/ር) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ይቀጥላሉ።

    በተጨማሪም ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር፣ አዲሱ አረጋ የግብርና ሚኒስትር፣ ሃና አርኣያሥላሴ የፍትሕ ሚኒስትር በመሆን በኃላፊነታቸው ይቀጥላሉ።

    ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር፣ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ጤና ሚኒስትር፣ ዐይንዓለም ንጉሤ የገቢዎች ሚኒስትር እና ሰላማዊት ካሳ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው ይቀጥላሉ።

    ባለፈው ዓመት ከተካሄደው ምርጫ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አስተዳደራቸውን አዋቅረዋል።

  18. የሰላም ሚኒስቴርን ጨምሮ 14 መሥሪያ ቤቶች አዳዲስ ሚኒስትሮች ተሾሙላቸው

    ባለፈው ዓመት ከተካሄደው ምርጫ በኋላ አዲስ አስተዳደራቸውን ያዋቀሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ የሰላም ሚኒስቴርን ጨምሮ ለ14 የሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች አዳዲስ ሚኒስትሮች ሾሙ።

    ዛሬ መስከረም 28/2019 ዓ.ም. አቶ ሙሳ አደም የሰላም ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ ሲሆን፤ ሱልጣን ወሌ (ዶ/ር) የመስኖ እና ቆላማ ሚኒስትር ሆነዋል።

    መሐመድ እድሪስ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ ሲሆን ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) የገንዘብ ሚኒስትር ሆነዋል።

    በተጨማሪም ያስሚን ወሀቢረቢ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር፣ ፍሰሐ ይታገሱ (ዶ/ር) የኢንዱስትሪ ሚንስትር ሆነው ተሹመዋል።

    አወሉ አብዲ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር፣ በረከት ፍሰሐጽዮን የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር ሆነዋል።

    ዓለምፀሐይ ጳውሎስ የማዕድን ሚኒስትር፣ ሳዳት ነሻ የሎጀስቲክስ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

    በተጨማሪም ሻዊት ሻንካ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ፍሬሕይወት ታምሩ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር፣ መሐመድ አብዱራህማን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር እንዲሁም አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር ሆነዋል።

  19. ሁቲዎች በሳዑዲ አውሮፕላን ማረፊያዎች ባደረሱት ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

    ሁቲዎች ለሁለት ቀናት በሳዑዲ አረቢያ አውሮፕላን ማረፊያዎች ባደረሱት ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

    በየመን ተባብሶ የቀጠለው ውጊያው ሳዑዲ ላይ ጥቃት ወደማድረስ ተሻግሯል።

    የሳዑዲ አረቢያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እንዳለው በአብሀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሰ ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ፣ 28 ሰዎች ተጎድተዋል።

    በሪያድ በሚገኘው ንጉሥ ኻሊድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተፈጸመ ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል፣ ስምንት ሰዎች ተጎድተዋል።

    የሁቲ አማጺያን ለጥቃቶቹ ኃላፊነቱን ወስደዋል። በሳዑዲ የሚደገፈው የየመን መንግሥት እና ሁቲዎች ውጊያ ተባብሶ ቀጥሏል።

    በሁለቱ አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ጥቃት የደረሰው በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 6 እና 7 መሆኑ ተገልጿል።

    የተገደሉት ሁለት ሞሮኳዊ ሴቶች እና አንደ የአልጄርያ ዜጋ ናቸው።

    አብሀ አውሮፕላን ማረፊያ ከየመን ጋር ባለው ድንበር አቅራቢያ ይገኛል። በንጉሥ ኻሊድ አውሮፕላን ማረፊያ ሱዳናዊ መገደሉም ተገልጿል።

  20. አሜሪካ በቀጣይ ቀናት በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት ለመክፈት እየተዘጋጀች መሆኑ ተዘገበ

    ፔንታጎን በቀጣይ ቀናት ውስጥ በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት ለመክፈት እየተዘጋጀ መሆኑን ሁለት የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    አክሲዮስ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ባለፉት ቀናት የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ኢራን ላይ “ከፍተኛ ኦፕሬሽን” ለማከናወን እንዲዘጋጅ ከፔንታጎን ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።

    አትላንቲክ መጽሔት ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ባወጣው ልዩ ዘገባ መሠረት፤ ከአሜሪካ የግማሽ ዘመን ምርጫ አስቀድሞ የኢራን ዒላማዎችን መምታት የሚቻልባቸውን መንገዶች ፔንታጎን እንዲፈልግ ከዋይት ሀውስ ትዕዛዝ ተላልፏል።

    የፔንታጎን ትዕዛዝ ጥቃቱ የሚጀመርበትን ትክክለኛ ቀን እንዳላስቀመጠ እና ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ እንዳልደረሱ የአክሲዮስ ዘገባ ያሳያል።

    የአክሲዮስ የአሜሪካ እና እስራኤል ምንጮች እንዳሉት ከሆነ ከአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ እና ከእስራኤል ምርጫ አስቀድሞ ጥቃቱ ሊፈጸም ይችላል።

    የአሜሪካ ምርጫ ኅዳር መባቻ ላይ የሚከናወን ሲሆን ከዚህ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የእስራኤል ምርጫ ይካሄዳል።

    አክሲዮስ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በኢራን ላይ የሚፈጸሙ ኦፕሬሽኖች በአገሪቱ የኃይል አቅርቦት፣ መሠረተ ልማት እና የኒውክሌር ተቋማት ላይ የሚደርስ መጠነ ሰፊ ጥቃትን ያካትታሉ።