የሳዑዲ አረቢያ ጦር በየመን በሚንቀሳቀሱት የሁቲ አማፂያን ላይ በርካታ ዙር ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምረት፣ በየመን የሚንቀሳቀሱት እና በኢራን የሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሩን አስታወቀ።
ወታደራዊ ዘመቻው በቀጥታ ታጣቂዎቹን እና ወታደራዊ አቅማቸው ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የጥምረቱ ቃል አቀባይ በመግለጫቸው ወቅት ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ፣ ጥምረቱ በሁቲዎች ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ 136 ወታደራዊ ዒላማዎችን ማውደሙን ገልጸዋል። በተጨማሪም የዓለም አቀፍ መንግሥታት ዕውቅና ላለው የየመን መንግሥት ተዋጊዎች የአየር ኃይል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።
የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት አርብ ዕለት የሁቲ አማፂያን በሪያድ በሚገኝ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ሦስት የአገሪቱ ዜጎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ይፋ አድርጓል።
የአገሪቱ ሲቪል አቪየሽን በኤክስ ገጹ ላይ ጥቃቱ “በርካታ የሳዑዲ እና የሌላ አገር ዜጎች ላይ ጉዳት አድርሷል” ብሏል።
የሁቲ አማፂያን ሐሙስ ዕለት ሁለት ጥቃቶች መፈጸማቸው የተገለጸ ሲሆን የመጀመሪያው አውሮፕላን ማረፊያው ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የሳዑዲ አረቢያ ብሔራዊ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን 'ሳውዲያ' አውሮፕላንን መትቷል።
አየር መንገዱ ከተገደሉት መካከል አንዱ የአውሮፕላኑ አብራሪ መሆኑን አስታውቋል። የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣኑ የአየር ትራፊክ እንቅስቃሴ ወደ መደበኛው ሁኔታ መመለሱን ገልጿል።
የሁቲ ታጣቂዎች ሐሙስ ዕለት አውሮፕላን ማረፊያውን በሁለት ባሊስቲክ ሚሳይሎች ማጥቃታቸውን አስታውቀዋል።
በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ሳዑዲ ከየመን ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ናጅራን ከተማ የሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሁም በስተሰሜን በኩል የሚገኘውን ኻሚስ ሙሻይት የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ዒላማ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ሳዑዲ አረቢያ እነዚህን ጥቃቶች አላረጋገጠችም።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አርብ ዕለት ሁቲዎች በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ ሁለት አየር ማረፊያዎች ላይ የፈጸሙትን ጥቃት አውግዘዋል።
ትራምፕ ስለ ጥቃቶቹ በጋዜጠኞች ሲጠየቁ "ጥሩ አይደለም። ጥሩ ነገር አይደለም። በዚህ ደስተኛ አይደለሁም" ብለዋል።
ሳውዲ አረቢያ ሐሙስ ዕለትበዋና ከተማዋ ሪያድ በሚገኘው የንጉሥ ኻሊድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ በተፈፀሙ ሁለት ጥቃቶች ሦስት የአገሪቱ ዜጎች መገደላቸውን አስታውቃለች።
ቡድኑ የሪያድ አውሮፕላን ማረፊያን ማጥቃቱን ካስታወቀ በኋላ ሠራተኞች ዒላማ ሊሆኑ ከሚችሉ የኢነርጂ ተቋማት እንዲርቁ አስጠንቅቋል።
ከጥቃቱ በኋላ ሉፍታንዛ እና ኤር ኢንዲያ ወደ ሪያድ የሚያደርጓቸውን በረራዎች አቋርጠው ነበር።




















