ቀጥታ, ኢራን ስምምነት ላይ መድረስ እንደምትፈልግ እና ጦርነቱ በቅርቡ እንደሚቆም ትራምፕ ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ስምምነት ላይ መድረስ ትፈልጋለች አሉ። የአጋማሽ ምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ በኖርዝ ካሮላይና የተገኙት ትራምፕ “ጦርነቱን ለማቆም ተቃርበናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ። እንዴት እንደሚሆን እናያለን” ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን ስምምነት ላይ መድረስ እንደምትፈልግ እና ጦርነቱ በቅርቡ እንደሚቆም ትራምፕ ተናገሩ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ስምምነት ላይ መድረስ ትፈልጋለች አሉ።

    የአጋማሽ ምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ በኖርዝ ካሮላይና የተገኙት ትራምፕ “ጦርነቱን ለማቆም ተቃርበናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ። እንዴት እንደሚሆን እናያለን” ብለዋል።

    ኢራን ስምምነት ላይ መድረስ እንደምትፈልግ ትራምፕ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ነገር ግን ባለፉት ወራት በሁለቱ አገራት መካከል የተደረገ ድርድር ወደ ተጨባጭ ስምምነት አላመራም።

    ኢራን እና አሜሪካ አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚሰነዝሩትን ጥቃት ቀጥለዋል።

    ጦርነቱ እና የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ያባባሰው በአሜሪካ ያለው የዋጋ ንረት፣ ታሪፍ እና የነዳጅ ዋጋ መጨመር አገሬውን አስግቷል።

    የአጋማሽ ዘመን ምርጫው ከመቃረቡም አንጻር ሪፐብሊካን እጩዎች ፈተና ገጥሟቸዋል።

    ትራምፕ በዚህ ጫና ምክንያት ስለ ድርድር እና ጦርነቱን የመግታት ጉዳይ በአደባባይ ንግግር ማድረጋቸውንም ቀጥለዋል።

  2. ቻይና የኢራንን መብት “ለመጠበቅ” ፈቃደኛ መሆኗን ገለጸች

    ሚኒስትር ዋንግ ይ እና አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, s_a_araghchi

    ከቴህራኑ አቻቸው ጋር ዛሬ ረቡዕ የተወያዩት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ፤ አገራቸው የኢራንን መብት “ለመጠበቅ” ፈቃደኛ መሆኗን አስታወቁ።

    በቤይጂንግ ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ “ቻይና ከኢራን ጋር ውይይት ለማጠናከር እና የኢራንን ሕጋዊ መብት እና ፍላጎቶች ለማስጠበቅ ዝግጁ ናት” ብለዋል።

    የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “ኢራን እና አሜሪካ ምክንያታዊ እንዲሆኑ እና እንዲቆጠቡ እናሳስባለን” ሲሉም አክለዋል።

    የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በቀጣይ ሳምንት ወደ አሜሪካ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

    የኢራን ዋነኛ የንግድ አጋር የሆነችው ቻይና ግጭቱን ለማርገብ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።

    “ቀጣናዊ ውጥረቱ ወደ የመን እና ቀይ ባሕር እንዲሻገር አንሻም” ሲሉ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል።

  3. ካናዳ የአውሮፓ ኅብረት “ተባባሪ አባል” እንድትሆን የቀረበው ጥያቄ ከኅብረቱ መሪ ድጋፍ ተሰጠው

    ኧርሰላ ቮን ደር ሊን እና ማርክ ካርኒ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ካናዳ የአውሮፓ ኅብረት የመጀመሪያዋ “ተባባሪ አባል” እንድትሆን የቀረበውን ምክረ ሐሳብ እንደሚደግፉት የኅብረቱ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ኧርሰላ ቮን ደር ሊን ገለጹ።

    ፕሬዝዳንቷ ዛሬ ረቡዕ ለአውሮፓ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፤ ለካናዳ “በሩን ለመክፈት” የሚጠበቅባቸውን ማከናወን ይፈልጋሉ።

    ይህም በተለያዩ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ትስስር መፍጠርን ያካትታል።

    የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር “ልዩ ጥምረት” እንደሚፈልጉ ባለፈው ሳምንት አስታውቀዋል።

    ካናዳ ከአሜሪካ ጋር የገባችበት የንግድ ጦርነት የሁለቱን አገራት ግንኙነት አጠልሽቷል።

    የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፤ ዶናልድ ትራምፕን በስም ባይጠቅሱም፤ ካናዳ በኅብረቱ የሚኖራት አባልነት “ለጋራ ጥቅም እንጂ ከማንም በተቃራኒ ለመቆም ያለመ አይደለም” ብለዋል።

  4. በጋዛ በጦርነት ጉዳት የደረሰበት ሕንጻ ተደርምሶ ቢያንስ 20 ሰዎች ተገደሉ

    በጋዛ የተደረመሰው ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በጋዛ ሰርጥ በጦርነት ሳቢያ ጉዳት የደረሰበት ሕንጻ ተደርምሶ ስምንት ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 20 ሰዎች መገደላቸውን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ገለጹ።

    በጋዛ፣ ታል አል-ሀዋ አካባቢ የሚገኘው ስድስት ፎቅ የነበረው ሕንጻ ፍርስራሽ ሥር በሕይወት ያሉ ሰዎችን ለማግኘት እና አስከሬን ለማውጣት ርብርብ እየተደረገ ነው።

    ሕንጻው ለአደጋ የተጋለጠ መሆኑ ቢገለጽም እንኳን ወደ 10 የሚጠጉ ቤተሰቦች ይኖሩበት እንደነበረ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

    በሐማስ የሚመራው የሰብአዊ መከላከያ አገልግሎት እንዳለው፤ ወደ ጋዛ የሚገቡ የእርዳታ መሣሪያዎች ላይ በእስራኤል በተጣለው ክልከላ ምክንያት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች “ባዶ እጃቸውን” ሲሠሩ ነበር።

    የሰብአዊ መከላከያው ዳይሬክተር ራይድ አል-ዳህሻን “አሁንም ድረስ ከፍርስራሽ ሥር ድምጽ ይሰማናል፤ ሰዎችን እናገኛለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

    በጋዛ ያለው የመጠለያ ውስንነት ሰዎች በሕንጻው እንዲኖሩ እንዳስገዳቸው ተናግረዋል።

    “ነገር ግን ሰዎች በተኙበት በሚያሳዝን ሁኔታ ሕንጻው ተደረመሰ” ብለዋል።

    በጋዛ የተደረመሰው ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በጋዛ የተደረመሰው ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  5. በናይጄሪያ አደገኛ እፅ የሚያመርት ቡድን መሪ እንደሆነ የተጠረጠረ ሜክሲኳዊ በቁጥጥር ሥር ዋለ

    ሜክሲኳዊው አርቱሮ ኬሬራ ሎአይዛ

    የፎቶው ባለመብት, NDLEA

    ባለፈው ወር አደገኛ እፅ የሚያመርት ቡድን መሪ እንደሆነ የተጠረጠረ ሜክሲኳዊ አገሪቷን ለቅቆ ለመውጣት ሲሞክር በናይጄሪያ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የመድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ይፋ አደረገ።

    የግለሰቡ በቁጥጥር ሥር መዋል በተቋም ደረጃ ‘ሜታምፔታማይን’ የተባለውን እፅ የሚያመርት ቤተ ሙከራ እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል። በአራት ወር ውስጥ ከሜክሲኳውያን ጋር የተገናኘ እንደሆነ የተገለጸ መሰል ቤተ ሙከራ ሲገኝ ይህ ሦስተኛው ነው።

    ሜታምፔታማይን ማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓትን የሚያነቃቃ አደገኛ ሰው ሠራሽ እፅ ነው።

    አርቱሮ ኬሬራ ሎይዛ የተባለው የ40 ዓመቱ ግለሰብ በሌጎስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በቁጥጥር ሥር ሲውል ባለሥልጣናት ቤተ ሙከራ ውስጥ የሚለበስ ኮት እንደሆነ ያመኑትን ልብስ ለብሶ የተነሳቸውን ዲጂታል ምሥሎች እንዲሁም ሜት ለማምረት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን እንዳገኙ ገልጸዋል።

    ምሥሎቹ የተነሱበት ቦታም መርማሪዎችን በኢቦንይ ግዛት ወደሚገኘው ቤት የመራቸው ሲሆን እዚያም ኬሚካሎች እና እፁን ለመስራት የሚያስችሉ መሣሪያዎችን እንዳገኙ ተናግረዋል።

    ሎይዛ ሜታምፔታማይን በማምረት ተሳትፏል መባሉን ውድቅ አድርጓል። ወደ ናይጄሪያ ያቀናውም አንድ የአካባቢው ምግብ ቤት ባለቤት ተጋብዞ እንደሆነ መግለጹን ብሔራዊው የእፅ ተቆጣጣሪ ተቋም በመግለጫው ጠቅሷል።

    የተቋሙ መርማሪዎች በተጠረጠረው ቤተ ሙከራ ውስጥ የደኅንነት ካሜራ ውስጥ በተገኘው ሜሞሪ ሎይዛን የሚመስል ግለሰብ ሰማያዊ የቤተ ሙከራ ልብስ ለብሶ ታይቷል።

    ከዚህ በተጨማሪም አንድ ናይጄሪያዊ ከአካባቢው ኬሚካሎችን እና መሣሪያዎች እንዲነሱ ለሌሎች ሰዎች ትዕዛዝ ሲሰጥ ታይቷል።

    የተጠረጠረው ቤተ ሙከራ ምን ያህል ሜታምፔታማይን ማምረት እንደሚችል የተሰጠ ግምት የለም።

    መርማሪዎች ሜክሲኳዊው ሎይዛ በኦዮ ግዛት በጫካ ውስጥ ድብቅ ሥፍራ እንደተገኘ በተገለጸ ቤተ ሙከራ እንዲሰሩ ሌሎች ሜክሲኳውያንን መልምሎ እንዳመጣም ገልጸዋል። ሰኔ ወር ላይ አካባቢው በፖሊስ ከተፈተሸ በኋላ አራት ናይጀሪያውያን በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

    ከአንድ ወር በፊትም መርማሪዎች የሜክሲኮ ዜጎችን እና ሰባት ናይጄሪያውያንን በቁጥጥር ሥር አውለዋል።

    በዚህ የወንጀል ቡድን ሰንሰለት ላይ እየተደረገ ያለው ምርመራም እንደቀጠለ ተገልጿል።

    እንደ ኮኬይን ወይም ሄሮይን ያሉ ከእፅዋት የሚቀመሙ እፆች ካልሆኑ በስተቀር እንደ ሜት ያለ ሰው ሰራሽ እፅ የሚያስፈልገውን ኬሚካል እና ባለሙያዎች ካሉ የትም ቦታ ሊመረት ይችላል።

    ይህም ለተደራጁ የወንጀል ቡድኖች እፁን በፍጥነት እንዲያመርቱ ቀላል አድርጎላቸዋል።

  6. ሳዑዲ አረቢያ የሁቲ ታጣቂዎች ወደ መካ የተኮሱትን ድሮን ማክሸፏን ገለጸች

    መካ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሳዑዲ አረቢያ ማክሰኞ ሌሊት በኢራን የሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች መካን ለማጥቃት መሞከራቸውን በመግለጽ ድርጊቱን አወገዘች።

    ሳዑዲ አረቢያ በመግለጫዋ መካ ላይ የሚፈጸም ጥቃት “ቀይ መስመር” መሆኑን በመግለጽ አስጠንቅቃለች።

    የሁቲ ባለሥልጣናት ወደ መካ ድሮኖች አለመተኮሳቸውን በመግለጽ በድርጊቱ እጃችን የለበትም ብለዋል።

    መካ ከየመን ድንበር 1 ሺህ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ነች።

    መካ የነብዩ ሙሐመድ የትውልድ ቦታ እና ቅዱስ ቁርዓን የተቀበሉበት ሥፍራም ነው።

    በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት የአገሪቱ አየር ኃይል በሁቲዎች ወደ መካ የተተኮሰን ድሮን ማክሸፋቸውን እና ማውደማቸውን ያስታወቀው ረበዕ ዕለት ማለዳ ነበር።

    የጥምረቱ ቃል አቀባይ ቱርኪ አል ማልኪ ድሮኑ የተተኮሰው ሌሊት መሆኑን አስታውቀው ወደ ተከለከለ ክልል ከመግባቱ በፊት ተመትቶ ስብርባሪው በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ወድቋል ብለዋል።

    አል ማልኪ ሁቲዎች መካን ዒላማ ያደረጉት ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ባሌስቲክ ሚሳዔል መተኮሳቸውን አስታውሰዋል።

    ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ከተማ በሆነችው መካ ላይ የሚፈጸም ጥቃት “ቀይ መስመር” ነው በማለት ጥምረቱ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጸም እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

    ሁቲዎች በበኩላቸው ሳዑዲ ድሮን ተኩሰዋል ስትል ያቀረበችውን ውንጀላ ውድቅ አድርገዋል።

    የሁቲ ከፍተኛ የፖለቲካ ምክር ቤት አባል ሄዛም አል-አሳድ ባወጡት መግለጫ “መካን ዒላማ የማድረግ ውንጀላዎች ከዚህ ቀደምም የተሰሙና አሁን ላይ ግን ማንንም የማያታልሉ ውሸቶች ናቸው” ብለዋል።

    ወደ መካ ድሮን መተኮሱ የተገለጸው ሁቲዎች ወደ ሳዑዲ በተኮሱት ድሮን እና ሚሳዔል በኻሚስ ሙሻይት፣ አብሃ እና ታይፍ በአጠቃላይ 13 ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው፣ ሰባት ቤቶች እና ሁለት መኪናዎች መውደማቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።

    "ከየመን ወደ ቅዱሳን ሥፍራዎች የሚሰነዘር ምንም ዓይነት ስጋት የለም። የእኛ ዘመቻዎች የሚያነጣጥሩት በነዳጅ ማጣሪያ ተቋሞቻቸው እና በወታደራዊ ካምፖቻቸው ላይ ሲሆን፣ ከቅዱስ ሥፍራዎችም እጅግ የራቁ ናቸው" ሲሉ የሁቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪያ ተናግረዋል።

    ሳሪያ አክለው እንደገለጹት፣ ሁቲዎች ባለፈው ሳምንት በግዛታቸው ላይ በተፈጸሙ ከ450 በላይ የሳዑዲ የአየር ጥቃቶች የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት፣ በሳዑዲ አረቢያ ላይ ድሮኖችን እና ሚሳይሎችን ተኩሰዋል።

    እንዲሁም በማሪብ ግዛት ላይ የሳዑዲ የጦር ጄት መትተው መጣላቸውን ተናግረዋል። ይህንን በሚመለከት ግን ሳዑዲ እስካሁን ድረስ ያለችው ነገር የለም።

  7. ጀርመን የብርጌድ ንሃመዱ አባላት ናቸው ያለቻቸውን ሁለት ሰዎች አሰረች

    የጀርመን ፖሊስ አባላት

    የፎቶው ባለመብት, AP

    የጀርመን መንግሥት በአውሮፓ እና አሜሪካ የኤርትራን መንግሥት በመቃወም የሚታወቁት ብርጌድ ንሃመዱ አባላት ናቸው በሚል የጠረጠራቸውን ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር አዋለ።

    የጀርመን ፌዴራል አቃቤ ሕግ ቢሮ በድረ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ሁለት የብርጌድ ንሃመዱ አባላት በመንግሥት ደጋፊዎች በዓላት እና በፖሊስ ኃይሎች ላይ አመፅ በማደራጀት ተጠርጥረው መያዛቸውን አስታውቋል።

    የጀርመን ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መርማሪ ዳኛ ባወጣው ማዘዣ መሠረት የታሰሩት ግለሰቦች ኤርትራዊው መርሃዊ እና የጀርመን ዜግነት ያለው ትውልደ ኤርትራዊው ሽማንጉስ ናቸው።

    ሁለቱ ተከሳሾች የእንቅስቃሴው አባላት በመሆናቸው ተጠርጥረው በስቱትጋርት አቅራቢያ በሳርባሩከን በፌዴራል የወንጀል ፖሊስ መያዛቸውን አቃቤ ሕግ አስታውቋል።

    መርሃዊ "የሕዝብ ሰላምን በማወክ" በሚል ተከሷል።

    በጽሕፈት ቤቱ መግለጫ መሠረት በጀርመን የአገር ውስጥ አሸባሪ ድርጅት በሚል የተፈረጀው ብርጌድ ንሃመዱ የተቋቋመው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 ነሐሴ ወር ሲሆን “የኤርትራን መንግሥት ለመጣል” ያለመ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ነው።

    ንቅናቄው በጀርመን የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች በሚያዘጋጇቸው በዓላት ላይ አመጽን መቀስቀስ ግቦቹን ለማሳካት እንደተጠቀመበት አስታውቋል።

    በጀርመን የመንግሥት ተቋማት እና በፖሊስ ኃይሎች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ግቦቹን ለማሳካት "ተቀባይነት ያለው መንገድ" አድርጎ እንደሚመለከተው አክሏል።

    በእስር ማዘዣው መሠረት፣ የንቅናቄው አባላት በጊሰን እና ስቱትጋርት በተደረጉ በዓላት እና ሠልፎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ተሳታፊዎች እና የፖሊስ መኮንኖች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

    አቃቤ ሕግ ጥቃቱ በንቅናቄው መሪዎች የተደራጀ ነው ሲል ከስሶ ይህም 'ለሕይወት አስጊ የሆነ መሣሪያ' መጠቀምን ያካትታል ብሏል።

    መርሃዊ በጀርመን የብርጌድ ንሃመዱ ዋና ጸሐፊ እንደነበር እና ሽማንጉስ የንቅናቄው ሊቀመንበር ሆኖ ማገልገሉን መግለጫው ጠቅሷል።

    መርሃዊ በጊሰን ከተማ በተነሳው ሁከትም መሳተፉን የገለጸው አቃቤ ሕግ በአንድ ወቅትም የጥቃት ቡድንን መርቷል ሲል በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

    ባለፈው ዓመት በተለያዩ የውጭ አገራት ሁከትና ብጥብጥ አስነስቷል የተባለው የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚው ብርጌድ ንሃመዱ በጀርመን ሕግ መሰረት "በአገር ውስጥ አሸባሪነት" ተፈርጇል።

    በጀርመን፣ ቡድኑ ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት ባላቸው ፌስቲቫሎች ላይ በተቀናጁ ሁከቶች ተሳታፊ ነው በሚል ተወንጅሏል።

    አቃቤ ሕግ በነሐሴ 2022 በጊሰን የተካሄዱ ፌስቲቫሎች እንዲሁም በመስከረም 2023 በስቱትጋርት የነበረ የኤርትራውያን ማኅበር ስብሰባን ዋቢ አድርጓል።

    በእነዚህ ዝግጅቶች ላይ የከፋ ጉዳትን ጨምሮ በርካታ የፖሊስ አባላት መቁሰላቸውን እንዲሁም በርካታ ተቃዋሚዎች መታሰራቸው ተገልጿል።

    "ብርጌድ ንሃመዱ" ባለፉት ዓመታት በተለይም በምዕራባውያን እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት እየተስፋፋ እና ትኩረት እየሳበ የመጣ የኤርትራውያን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ነበር።

    የብርጌድ ንሃመዱ ደጋፊዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴያቸውን የጀመሩት የኤርትራ መንግሥት በተለያዩ ሀገራት የሚያዘጋጃቸውን ክብረ በዓሎች እና ዝግጅቶች በማወክ ነው። አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ እስራኤል፣ ካናዳ፣ ጀርመን፣ ስዊድን እና ስዊትዘርላንድ የኤርትራ መንግሥትን በሚደግፉ ፌስቲቫሎች ላይ ረብሻ ያጋጠመባቸው አገራት ናቸው።

    በእነዚህ ረብሻዎች ወቅት የመንግሥት ደጋፊ በሆኑ እና በተቃዋሚ ኤርትራውያን መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በተደጋጋሚ የፀጥታ ኃይሎችን ጨምሮ በሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

    በዚህ ዓይነቱ አመጽ ላይ የተሳተፉ ኤርትራውያን በተለያዩ አገራት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

    በአውሮፓውያኑ 2023 በስቱትጋርት የተቀሰቀውን ረብሻ ተከትሎ 56 ሰዎች በእስር እንዲቀጡ ተደርገዋል።

  8. ዴንማርክ የሩሲያ የጦር መርከቦች በሄሊኮፕተሬ ላይ ድንገተኛ ብርሃን ለቅቀዋል ስትል ከሰሰች

    ሄሊኮፕተር

    የፎቶው ባለመብት, Rune Dyrholm / Danish Armed Forces

    ዴንማርክ የሩሲያ የጦር መርከቦች በባልቲክ ባሕር ላይ ቅኝት ሲያደርግ በነበረ ሄሊኮፕተሬ ላይ ሁለት የድንገተኛ አደጋ ምልክት መስጫ ርችት ተኩሰዋል ስትል ከሰሰች።

    የዴንማርክ መንግሥት ሰኞ እለት በተለመደ የቅኝት ሥራ ላይ በነበረው ሄሊኮፕተሩ ላይ የተፈፀመውን ክስተት ተከትሎ የሩሲያን አምባሳደር ጠርቷል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ሚት ፍሬድሪክሰን የሩሲያን ድርጊት “ ያልተገባ እና “ ለትንኮሳ እና ለመከፋፈል የተሰራ” ሲል ገልጾታል።

    ሩሲያ በበኩሏ ክስተቱን እንደምትመረምር ገልጻ፣ የዴንማርክ ሄሊኮፕተሮች በሩሲያ የጦር መርከቦች ላይ አደገኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር ስትል በምላሹ ከሳለች።

    የሩሲያ አምባሳደር ቭላድሚር ባርቢን፣ የዴንማርክ አየር ኃይል ሄሊኮፕተሮች በሩሲያ የጦር መርከቦች ላይ አደገኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው እንዳልሆነ ገልጸዋል።

    ባለፈው ዓመትም ተመሳሳይ ክስተት እንዳጋጠመ የገለጹት አምባሳደሩ፣ የአሁኑ ክስተት ላይ ያጋጠመው የግንኙነት ችግር ከሩሲያ መርከቦች በኩል ሳይሆን በዴንማርክ በኩል ያጋጠመ ነው ብለዋል።

    የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኡርሱላ ቮን ዲር ሊየን በበኩላቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋሩት ጽሑፍ ሩሲያ ያሳየችው ባሕርይ “ ግድየለሽ እና አደገኛ” ሲሉ ገልጸውታል።

    ይህ የሆነው የኔቶ ኃይሎች በሊቱኒያ አንድ ድሮን መትተው በጣሉ በተመሳሳይ ቀን ነው።

    በባልቲክ ባሕር ላይ የተከሰተውን ክስተት ተከትሎ የዴንማርክ ጦር በሰጠው መግለጫ “ የአየር ኃይሉ አንድ ሄሊኮፕተር በተለመደ የፎቶግራፍ ማንሳት ሥራ ላይ ሳለ ተተኩሶበታል” ብሏል።

    አንደኛው ማስጠንቀቂያ በሄሊኮፕተሩ ላይ የተተኮሰ ሲሆን አንደኛው በአቅራቢያው አልፏል ብሏል።

    የዴንማርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርጊቱን “ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌለው” ሲሉ ኮንነውታል።

  9. ከአሜሪካ ቤተ መጽሐፍት በውሰት የተወሰደ መጽሔት ከ132 ዓመታት በኋላ ተመለሰ

    መጽሐፍ የያዘ ፊቱ የማይታይ ግለሰብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከአሜሪካዋ ግዛት ኒው ሄምፕሻየር ቤተ መጽሐፍት በውሰት የተወሰደ መጽሔት ከ132 ዓመታት በኋላ ተመለሰ።

    ኮንኮርድ ቤተ መጽሐፍት እንዳለው መጽሔቱ በ1894 መስከረም ወር የወጣ እትም ሲሆን ባለፈው ሳምንት ቤተ መጽሐፍቱ መመለሻ ጊዜያቸው ላለፈባቸው የሚጥለውን ቅጣት ለአንድ ዓመት ማንሳቱን ካሳወቀ በኋላ ሊመለስ ችሏል።

    'ዘ ሴንቸሪ ኢሉስትሬትድ መንዝሊ ሜጋዚን' የተሰኘው ይህ ታሪካዊ መጽሔት መመለስ ከነበረበት ጊዜ በ48 ሺህ 220 ቀናት የዘገየ ሲሆን 12 ሺህ 55 ዶላር ቅጣትን ያስከትል ነበር።

    መጽሔቱን የመለሰው የቤተ መጽሐፍቱ ደንበኛ ጆን፣ መጽሔቱ ለአስርተ ዓመታት ቤቱ ውስጥ እንደነበር፤ ነገር ግን ቤቱ ውስጥ እንዴት ሊገኝ እንደቻለ እንደማያውቅ ተናግሯል።

    በአካባቢው በሚወጣ ጋዜጣ ላይ ቤተ መጽሐፍቱ የቅጣት ምህረት ማድረጉን ገልጾ ያወጣውን ማስታወቂያ ከተመለከተ በኋላም ለመመለስ እንደወሰነ ገልጿል።

    ቤተ መጽሐፍቱ በፌስቡክ ገጹ ባጋራው ጽሑፍ “ ቅጣቱ መነሳቱን ካስታወቅን በኋላ በርካታ ደስተኛ ፊቶች ተመልከተናል” ብሏል።

    “በእርግጥ ብዙ የመመለሻ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መጽሐፍትን እንጠብቃለን። ነገር ግን እንደዚህኛው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ የተወሰዱ አይደሉም” ሲልም ሎሎች ያልተመለሱ በርካታ መጽሐፍት እንዳሉ ገልጿል።

    ኮንኮርድ የሕዝብ ቤተ መጽሐፍት ከቅጣት ነጻ የሆነ ቤተ መጽሐፍ የሚያመጣውን ውጤት ለመገምገም የመመለሻ ጊዜ ላለፈባቸው ከአውሮፓውያኑ መስከረም አንድ ጀምሮ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የቅጣት ምህረት እንደሚያደርግ አስታውቋል።

    በማኅበራዊ ሚዲያ ባጋራው ጽሑፍም መጽሔቱ ከዚህ በኋላ በውሰት የሚወጣ ባይሆንም በቤተ መጽሐፍቱ አንድ ጥግ ቦታ ይገባዋል” ሲል በቤተ መጽሐፍቱ ለታሪክ በተለየ ምድብ እንደሚቀመጥ ገልጿል።

  10. በመካከለኛው ምሥራቅ የኢራን ሚሳዔል በአሜሪካ ጦር ላይ ያደረሳቸውን ጉዳቶች የሚያሳይ ምስል ይፋ ተደረገ

    በሲቢኤስ የተገኘው ይህ ምስል በሳዑዲ አረቢያ ከሚገኘው የልዑል ሱልጣን የአየር ኃይል ጦር ሠፈር የተነሳ ሲሆን፣ ባለአራት ሞተር ቦይንግ ኤ-3 ሴንትሪ አውሮፕላን የኋላ ክፍል ላይ የተሰነዘረ ቀጥተኛ ጥቃትን ያሳያል።

    የፎቶው ባለመብት, CBS

    የምስሉ መግለጫ, ሲቢኤስ ይፋ ያደረገው ይህ ምስል በሳዑዲ አረቢያ ከሚገኘው የልዑል ሱልጣን የአየር ኃይል ጦር ሠፈር የተገኘ ሲሆን፣ ባለአራት ሞተር ቦይንግ ኤ-3 ሴንትሪ አውሮፕላን የኋላ ክፍል ላይ የተሰነዘረ ቀጥተኛ ጥቃትን ያሳያል

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ በኢራን የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶች የወደሙ የአሜሪካ ጦር አውሮፕላኖችን ምስል ለመጀመርያ ጊዜ ማክሰኞ ዕለት ይፋ አድርጓል።

    እነዚህ ምስሎች የአሜሪካ ጦር በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የጦር ሠፈሮቹ ላይ በተፈጸመበት ጥቃት የደረሰውን ከባድ ጉዳት የሚያሳዩ ናቸው።

    የኢራን ጥቃቶች የጦር አውሮፕላን፣ ሕንጻዎች እና መኪኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ምስሎቹ አሳይተዋል።

    ምስሎቹ ለሲቢኤስ የተላኩት ስሙ እንዳይገለጽ በጠየቀ እና አሁንም በቀጣናው እያገለገለ ከሚገኝ የአሜሪካ ጦር አባል ነው።

    በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኝ የአሜሪካ ጦር አባል ስለጥቃቶቹ ለሲቢኤስ ሲናገር “በጦር ሠፈራችን ላይ የደረሰው ከፍተኛ ኪሳራ ነው፤ ነገር ግን የደረሰው ውድመት ለአሜሪካ ሕዝብ ይፋ አልሆነም። እኛ እዚያ ተቀምጠን የሚደርስብንን ድብደባ በጸጋ መቀበል ሆኗል ሥራችን” ብሏል።

    ምስሎቹ የተገኙት በሳዑዲ አረቢያ ከሚገኘው ልዑል ሱልጣን የአየር ኃይል የጦር ሠፈር ሲሆን ባለ አራት ሞተር ቦይንግ ጦር አውሮፕላን ተመትቶ ይታያል።

    ምስሉ የአውሮፕላኑ የኋላ ክፍል ከፊተኛው ጋር ተለያይቶ የሚያሳይ ሲሆን አውሮፕላኑ የአየር ላይ እንቅስቃሴዎችን መከታተል የሚያስችል ራዳር የተገጠመለት ነበር ተብሏል።

    በኩዌት፣ ካምፕ ባውሪንግ የወደመ የጦር ሠፈር

    የፎቶው ባለመብት, CBS

    የምስሉ መግለጫ, በኩዌት የሚገኘው ባውሪንግ የጦር ሠፈር የደረሰ ውድመት
    በኩዌት በሚገኘው የአሪፍጃን የጦር ሠፈር ውስጥ በሚገኝ ሕንፃ ላይ የደረሰ ጉዳት

    የፎቶው ባለመብት, CBS

    የምስሉ መግለጫ, በኩዌት በሚገኘው የአሪፍጃን የጦር ሠፈር ውስጥ በሚገኝ ሕንፃ ላይ የደረሰ ጉዳት
  11. በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ የነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ደርሶ ሁለት መርከበኞች ተገደሉ

    የኦማን የባህር ኃይል ደህንነት ማዕከል በኤል ጋይያ የሞተር ክፍል ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የእሳት አደጋ መከሰቱን አስታውቋል

    የፎቶው ባለመብት, Oman Maritime Security Centre

    የምስሉ መግለጫ, የኦማን የባህር ኃይል ደህንነት ማዕከል በኤል ጋይያ የሞተር ክፍል ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የእሳት አደጋ መከሰቱን አስታውቋል

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ደርሶ ሁለት መርከበኞች ሲሞቱ 23ቱን ማትረፍ መቻሉን ኦማን አስታወቀች።

    የኦማን የባሕር ላይ ደህንነት ማዕከል የፓናማን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለበልበው ኤል ጋይያ የተባለች መርከብ ማክሰኞ ዕለት በሞተር ክፍሏ ላይ እሳት ከተነሳ በኋላ በኦማን ወደብ መልህቋን እንድትጥል መደረጉን አስታውቋል።

    አክሎም መርከቧ ጥቃት የደረሰባት ከሙሳንዳም ባህረገብ መሬት 2.4 ኪሜትር ርቀት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

    ሰኞ ዕለት የኢራን አብዮታዊ ዘብ መርከቧ በተከለከለ እና ደህንነቱ ባልተጠበቀ መስመር ስትጓዝ ባህር ውስጥ የተቀበረ ፈንጂ ፈንድቶ መመታቷን እና በእሳት መያያዟን አስታውቆ ነበር።

    ነገር ግን የአሜሪካ ጦር የኢራን መግለጫ የተሳሳተ ነው ብሏል።

    ጦሩ አክሎም መርከቧ ባለፈው ወር በኢራን በተተኮሰ ሚሳዔል መመታቷን እና በሳምንቱ መጨረሻ ደግሞ የድሮን ጥቃት እንደደረሰባት አስታውቋል።

    የዩኬ የባሕር ላይ ንግድ እንቅስቃሴዎች ማዕከል ደግሞ እሁድ እለት በሆርሙዝ ወሽመጥ እያለፈች የነበረች መርከብ ምንነቱ ባልታወቀ ተተኳሽ መመታቷን እና በእሳት መያያዟን መረጃ እንደደረሰው አስታውቆ ነበር።

    በዚህ ወር መጀመርያ ላይ ኢራን በወሽመጡ በኩል እያለፈ የነበረ የሳዑዲ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት መድረሱን አስታውቃ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ሁለት ፊሊፒንሳውያን መርከበኞች ተገድለዋል።

    በወቅቱ አብዮታዊ ዘቡ ሲዲር የተባለችው መርከቧ በእሳት የተያያዘችው ውሃ ውስጥ የተቀበረ ፈንጂ ፈንድቶ መሆኑን አስታውቋል።

    ነገር ግን የሳዑዲ ባለሥልጣናት ኢራን ጥቃት መፈጸሟን ሲናገሩ የባህር ላይ ትራንስፖርት ደህንነት ተቋማት መርከቧ በሰሜናዊ ሙሳንዳም በተተኳሽ መመታቷን አስታውቀዋል።

    የዓለም አቀፉ የባህር ላይ ትራንስፖርት ድርጅት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ለማለፍ የሞከሩ መርከቦች ላይ በተፈጸሙ የተረጋገጡ 79 ጥቃት 22 ባህረተኞች መገደላቸውን አስታውቋል።

    ማክሰኞ ዕለት ፋርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው "የጠላት ድሮኖች" ከሙሳንዳም በስተሰሜን ምሥራቅ 80 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ባለ የኢራን ወደብ አቅራቢያ ሌሊት እየተንቀሳቀሱ የነበሩ ሁለት የዓሣ ማጥመጃ ጀልባዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል።

    ከአብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ፋርስ የዜና ወኪል የሆርሞዝጋን ግዛት ምክትል ገዥን ጠቅሶ፣ ክስተቱን ተከትሎ በርካታ ዓሣ አጥማጆች እንደጠፉ እና የፍለጋ እና የማዳን ጥረት እየተካሄደ መሆኑን ዘግቧል።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ኮማንድ፣ ሴንቲኮም፣ ቃል አቀባይ ለአክሲዮስ የዜና ድረ ገጽ ጦሩ የባህር ድሮን ለመስረቅ የሞከሩ ሁለት ጀልባዎችን ​​መምታቱን አስታውቀዋል።

    “የኢራን ትናንሽ ጀልባዎች በቅርቡ የአሜሪካን ሰው አልባ መርከብ ለመቆጣጠር ሞክረዋል፣ ነገር ግን ሴንቲኮም ጠንከር ያለ ምላሽ በመስጠቱ አልተሳካላቸውም” ሲሉ ካፒቴን ቲም ሃውኪንስ ተናግረዋል።

    የዓለማችን አንድ አምስተኛ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ በሚያልፍበት የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ከኢራን በሚተኮሱ ሚሳዔሎች እና ድሮኖች የተነሳ ለመርከቦች እንቅስቃሴ ስጋት ሆኖ ቆይቷል።

  12. የሳዑዲ አረቢያው ልዑል ቢን ሳልማን ለጉብኝት ካይሮ ገቡ

    ልዑል ሳልማን እና ፕሬዝዳንት ሲሲ ካይሮ ውስጥ

    የፎቶው ባለመብት, Egyptian Presidency

    የምስሉ መግለጫ, ልዑል ሳልማን እና ፕሬዝዳንት ሲሲ ካይሮ ውስጥ

    በጎረቤት የመን ባሉት የሁቲ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት የተፈጸመባት ሳዑዲ አረቢያ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ዛሬ ማክሰኞ ለይፋዊ ጉብኝት በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ገብተዋል።

    ልዑሉ በጉብኝታቸው የመጀመሪያ ዕለት ከግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱልፋታህ አል-ሲሲ ጋር በሁለቱ አገራት የጋራ ጉዳዮች እና በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ተዘግቧል።

    የግብፅ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት እንደገለጸው፣ አል ሲሲ እና መሐመድ ቢን ሳልማን ውይይታቸው ሁቲዎች ስጋት በፈጠሩበት የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ እንዲሁም በቀይ ባሕር የመርከብ እንቅስቃሴ ነጻነት እና ደኅንነት ጉዳይ ላይ አጽንኦት ሰጥተው ተነጋግረዋል።

    በተጨማሪም ግብፅ ሳዑዲ አረቢያ ደኅንነቷን እና መረጋጋቷን ለማስጠበቅ የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ እንዲሁም ለየመን ቀውስ አጠቃላይ ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሔ እንዲገኝ እንደምትሻ ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።

    ባለፈው ሳምንት ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው የሁቲ አማፂያን የቀይ ባሕርን ምሥራቃዊ ጠረፍ እና የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ ቁልፍ ቦታዎችን ተቆጣጥረዋል።

    ባለፉት ሳምንታት በተጠናከረው የየመን ሁቲ ኃይሎች ዘመቻ ሳዑዲ አረቢያ በተደጋጋሚ ዒላማ ሆናለች። ሁቲዎች የሚዋጉት የየመን መንግሥትን የምትረዳው ሳዑዲ በታጣቂዎቹ ላይ የአየር ጥቃቶችን ፈጽማለች።

    ሁቲዎች በቀይ ባሕር የመርከቦች መተላለፊያ በር ላይ ይዞታቸውን በማጠናከር በተለይ የሳዑዲ መርከቦች ላይ የእንቅስቃሴ ዕገዳ መጣላቸው ይታወቃል።

    ይህ የሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር ላይ እየተጠናከረ የመጣው ተጽእኖ በመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ የሚፈጥረው ጫና ከሳዑዲ ባሻገር ከሱዌዝ ቦይ ከፍተኛ ገቢ የምታገኘውን ግብፅንም የሚነካ ነው።

  13. በኢራን ጦርነት ምክንያት አሜሪካ የወሳኝ ጦር መሣሪያዎች እጥረት እንደገጠማት ተገለጸ

    የአሜሪካ ሚሳዔል ተሸካሚ ተሽከርካሪ መኪና

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ ፔንታገን ባወጣው ሪፖርት፣ ከኢራን ጋር እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የወሳኝ ጦር መሣሪያዎች እጥረት እንደተፈጠረ ተረጋገጠ። ይህም ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሲናገሩ ከነበረው ፈጽሞ የሚቃረን ነው።

    አሜሪካ በጦርነቱ የተጠቀመቻቸውን የጦር መሣሪያዎች በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ሪፖርት በቀረበበት ጊዜ፣ ከየካቲት እስከ ሰኔ ድረስ በኢራን ላይ በተካሄደው ዘመቻ 33.4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማስከተሉን የመከላከያ ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ከዚህ ውስጥም 22.3 ቢሊዮን ዶላር የወጣው በጥቅም ላይ ለዋሉ ተተኳሾች እና ሌሎች የጦር መሣሪያዎች ላይ ነው።

    አሁን የወጣው ሪፖርት እንዳለው በኢራን ላይ የተካሄደው ዘመቻ “በወሳኝ የጦር መሣሪያ ክምችቶች ላይ እጥረት አስከትሎ ለተተኳሽ እና ለመሣሪያ አቅርቦት ያለውን የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ውስንነት አጋልጧል” ብሏል።

    የጦር መሣሪያ “እጥረቶችን እና መዘግየቶችን ለመቅረፍ፣ ፔንታገን የግዥ ሂደቶችን ለማፋጠን እንዲሁም ወሳኝ ቁሳቁሶችን፣ መለዋወጫዎችን እና የተመረጡ የጦር መሣሪያዎችን ለማምረት እና ለማከማቸት የሚወስደውን ጊዜ ለመቀነስ እየሠራ ነው” ተብሏል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን በመካከለኛው ምሥራቅ በተካሄደው ጦርነት ምክንያት የአሜሪካ የጦር መሣሪያ ክምችት ተመናምኗል መባሉን ደጋግመው ሲያጣጥሉት ነበር። በቅርቡም አሜሪካ “ከሞላ ጎደል ወሰን የሌለው” የጦር መሣሪያ ትጥቅ እንዳላት ተናግረዋል።

    ሰኞ ዕለትም ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ አሜሪካ “በታሪኳ ውስጥ ከማንኛውም ጊዜ በላይ የተራቀቁ እና የላቁ መሣሪያዎችን እያመረተች ነው” ብለዋል።

    ተፈጥሯል የተባለው እጥረት ከአሜሪካ ባሻገር ከአሜሪካ በሚቀርብላቸው ትጥቅ እና ተተኳሽ የሚተማመኑ ዩክሬን እና ታይዋንን በመሳሰሉ አገራት ላይ ስጋትን ፈጥሯል።

  14. የየመን ሁቲ ታጣቂዎች ተጨማሪ ሃኒሽ ደሴቶችን መቆጣጠራቸው ተዘገበ

    የሁቲ ታጣቂዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ይዞታቸውን እያሰፉ የመጡት የየመን ታጣቂ ኃይሎች ሁቲዎች ከአሥርት ዓመታት በፊት ኤርትራ እና የመን በይገባኛል የተዋጉባቸውን ሃኒሽ ደሴቶችን መቆጣጠራቸው ተዘገበ።

    በደቡባዊ ቀይ ባሕር የሚገኙትን እነዚህ ቁልፍ ደሴቶች የሁቲ ኃይሎች ሰኞ ዕለት የያዙት በሳዑዲ የሚደገፈውን የየመን መንግሥት ኃይሎችን በማስወጣት መሆኑን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቧል።

    አሁን የሁቲ ታጣቂዎች በደቡባዊ ቀይ ባሕር ከኤርትራ እና ከጂቡቲ ጋር በሚዋሰነው ቦታ ላይ የሚገኙትን ሃኒሽ ደሴቶችን መቆጣጠራቸው በጂቡቲ የሚገኘውን የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል 32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንዲቀርቡት አድርጓቸዋል።

  15. እነ አቶ አበበ አካሉ ዋስትና ከተፈቀደላቸው ከ12 ቀን በኋላ በዋስትናው ላይ ብይን ለመስጠት በድጋሚ ተቀጠሩ

    ከግራ ወደ ቀኝ አቶ አበበ አካሉ፣ አቶ አበራ ንጉሥ እና አቶ ይሳቅ ወልዳይ
    የምስሉ መግለጫ, አቶ አበበ አካሉ፣ አቶ አበራ ንጉሥ እና አቶ ይሳቅ ወልዳይ

    "በሽብር ወንጀል" የተጠረጠሩት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ፖለቲከኞች አቶ አበበ አካሉ እና አቶ ይሳቅ ወልዳይ እንዲሁም ጠበቃ አበራ ንጉሥ፣ ዛሬ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርበው ለአርብ መስከረም 8 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው።

    ተጠርጣሪዎቹ እያንዳንዳቸው በ50 ሺህ ብር ዋስ እንዲፈቱ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዓርብ ነሐሴ 29/2018 ዓ. ም ነበር የወሰነው።

    ይሁን እንጂ፣ በዋስ ከተለቀቁ "ፅምዶን ሊቀላቀሉ ይችላሉ" በሚል ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረበው ፖሊስ፣ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሽሮ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንዲፈቀድለት በመጠየቁ የዋስትና ግዴታቸውን ቢወጡም ሳይፈቱ ቀርተዋል።

    በይግባኙ ላይ ጳጉሜ 2/2018 ዓ.ም የተደረገውን ክርክር ያዳመጠው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ቀጥሮ ነበር።

    ዛሬ መስከረም 5/2018 ዓ.ም የዋለው ይህ ችሎት ታዲያ፣ በዋስትናው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ተጨማሪ ቀጠሮ መስጠቱን የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ችሎቱ ለመስከረም 11 ቀጥሮ የነበረው ቢሆንም፣ ተከሳሾቹ እና ጠበቆቻቸው “ከፍተኛ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ” ለአርብ መስከረም 8/2018 ዓ.ም መቅጠሩን አቶ ሰለሞን ገልፀዋል።

    የፌዴራል ፖሊስ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ባቀረበው የይግባኝ አቤቱታው፣ ሦስቱ ተጠርጣሪዎች "ጫካ ከሚገኘው ፅምዶ ቡድን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው" በማለት ነበር ያመለከተው።

    በመሆኑም በዋስ የሚፈቱ ከሆነ "ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ከፀረ-ሰላም ቡድኑ ጋር ሊቀላቀሉ እና በሚፈለጉበት ጊዜ ሊሰወሩብን ይችላሉ" በማለት ተቃውሞውን መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል።

    ምንም እንኳን ከሥር ፍርድ ቤት ጀምሮ ፖሊስ የጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቢሆንም፣ ሦስቱ ተጠርጣሪዎች በዋስ እንዲፈቱ ከተወሰነ በኋላ እስከ ዛሬ ለ12 ቀናት በእስር የቆዩ ሲሆን እስከቀጣዩ ቀጠሮ ድረስ የእስር ቆይታቸው 15 ቀን ይሆናል። ይህም ለፖሊስ ከሚሰጠው ከፍተኛ ጊዜ በአንድ ቀን ይልቃል።

    ሁለቱ ፖለቲከኞች እና የሕግ ባለሞያው አቶ አበራ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም ነው።

  16. ብቸኛው ተወዳዳሪ አቶ ኢሳያስ ጅራ ለ3ኛ ዙር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

    አቶ ኢሳያስ ጅራ ዛሬ መስከረም 5/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሔደው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር ሲያደርጉ

    የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Football Federation

    የምስሉ መግለጫ, አቶ ኢሳያስ ጅራ

    የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 5/2019 ዓ. ም ባካሔደው 18ኛ መደበኛ እና የምርጫ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አቶ ኢሳያስ ጅራ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት እንዲቀጥሉ ተወሰነ።

    ከጠቅላላው 99 አባላት መካከል በጉባዔው ላይ 88ቱ የተገኙ ሲሆን፣ ከእነርሱም 81 አባላት ለአቶ ኢሳያስ ጅራ ድጋፋቸውን መስጠታቸውን በጉባኤው ላይ የታደሙ የስፖርት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

    አቶ ኢሳያስ ጅራ ፌዴሬሽኑን ለሦስተኛ ዙር በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆነው ነው የቀረቡት።

    ያለፉትን 8 ዓመታት ፌዴሬሽኑን የመሩት አቶ ኢሳያስ፣ ለተጨማሪ 4 ዓመታት በመሪነት ለመቀጠል ብቸኛ ዕጩ ሆነው መቅረባቸው ብዙዎችን ሲያነጋግር ነበር የቆየው።

    አንድ ግለሰብ ፌዴሬሽኑን ለሁለት የሥልጣን ዘመን ብቻ እንዲያስተዳድር ይደነግግ የነበረው መተዳደሪያ ደንብ በዚህ ዓመት ተሻሽሎ ነው ፕሬዝዳንቱ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን የተወዳደሩት።

    የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ሞላ፣ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ከአቶ ኢሳያስ ጋር ለመፎካከር ሌላ አንድ ዕጩ ቀርበው እንደነበረ የአቶ ኢሳያስ ብቸኛ ዕጩነት ይፋ በተደረገበት ወቅት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። ሆኖም ሌላኛው ዕጩ መስፈርት ባለማሟላታቸው ኮሚቴው ውድቅ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል።

    ከ24 ዓመታት በላይ ከታች ጀምሮ በስፖርት አመራርነት የቆዩት አቶ ኢሳያስ፣ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንትነታቸው በተጨማሪ የካፍ የሥራ አስፈጻሚ እና የፊፋ ቋሚ ኮሚቴ አባል መሆናቸውን የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።

  17. ኬንያ የዓለም አትሌቲክስ ውድድርን በማስተናገድ የመጀመሪያዋ የአፍሪካ አገር ልትሆን ነው

    ኬንያዊቷ አትሌት ፌዝ ኪፕቾጌ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ኬንያዊቷ አትሌት ፌዝ ኪፕቾጌ

    ኬንያ የ2029 የዓለም አትሌቲክስ ውድድር አስተናጋጅ አገር ሆና ተመረጠች። በቡዳፔስት በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ምክር ቤት ውይይት ላይ ናይሮቢ የውድድሩ አዘጋጅ እንድትሆን ተወስኗል።

    ናይሮቢ አዘጋጅ ከተማ ሆና የተመረጠችው ለንደንን አሸንፋ ነው።

    የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ኮ እንደተናገሩት ናይሮቢ “በጣም አሳማኝ እና ስሜት የሚያጭር የአስተናጋጅነት ጥያቄ” አቅርባለች።

    “ለ2029 እና 2031 አራት የአስተናጋጅነት ጥያቄዎች ስለቀረቡልን ዕድለኛ ነን። ውሳኔው ላይ መድረስ ለምክር ቤቱ ቀላል አልነበረም” ብለዋል።

    በውሳኔው አማካኝነት "አትሌቲክስን በመላው ዓለም የማሳደግ" ግባቸውን እንደሚያሳኩ ገልጸዋል።

    የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮንሺፕስ በቀጣይ ሦስት ዙር በእስያ፣ በአፍሪካ እና በአውሮፓ ይከናወናል።

    “የዓለም አትሌቲክስ ውድድሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ መውሰድ ታሪካዊ ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

    “ትክከለኛዋን አዘጋጅ አገር እና ትክክለኛውን ሁኔታ ስላገኘን ወደ አፍሪካ መምጣቱ ትልቅ ነገር ነው። ናይሮቢ ጊዜው የሷ መሆኑን አሳይታለች” ሲሉም አክለዋል።

    ናይሮቢ ውድድሩን የምታስተናግረው 48,000 ታዳሚዎች በሚይዘው ካሳራኒ ስቴድየም ይሆናል።

  18. በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ቁጥር መቀነሱ ተገለጸ

    ሸቀጥ የጫኑ መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ ሸቀጥ የጫኑ መርከቦች ቁጥር ቀንሶ ትናንት ሰኞ አራት መርከቦች ብቻ መጓጓዛቸው ተገለጸ።

    የመርከቦችን እንቅስቃሴ የሚከታተለው ኬፕለር ባወጣው ሪፖርት እሑድ በወሽመጡ ያለፉ መርከቦች 10 ነበሩ።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የአሜሪካ ባሕር ኃይል ከለላ ሰጥቷቸው የሚተላለፉ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ሳምንታዊ አማካይ ቁጥር መጨመሩን የአሜሪካ ኢነርጂ ሚኒስትር ክሪስ ራይት መናገራቸው ይታወሳል።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ሁለት መርከቦች በወሽመጡ ያለፉ ሲሆን አንደኛው ሸቀጥ ጭኗል። በሌላ በኩል ሰኞ ዕለት ሁለት ነዳጅ የጫኑ መርከቦች ወደ ወሽመጡ ገብተዋል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ትናንት ባወጣው መግለጫ ‘አልጋያ’ የተባለው ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ በደቡባዊ የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በፈንጂ ምክንያት አደጋ ገጥሞታል።

    እሳቱን ለማጥፋት የተደረገው ጥረት እንዳልተሳካም ተገልጿል።

    ኢራን በደቡባዊው መንገድ የሚደረግ ጉዞ “ሕገ ወጥ” እና “አደገኛ” መሆኑን ገልጻለች። አሜሪካ ግን ለዚህ የጉዞ መስመር ጥበቃ እንደምትሰጥ አስታውቃለች።

  19. ትራምፕ ኤአይ ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ የቀረበውን ጥሪ ውድቅ አደረጉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር የተያያዙ ስጋቶች “ማታለያ” ናቸው ብለው አጣጣሉ።

    በፍጥነት እየተጓዘ ያለው የኤአይ ቴክኖሎጂ ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ የቀረቡ ጥሪዎችንም ውድቅ አድርገዋል።

    የኤአይ ኩባንያው አንትሮፒክ አጋር መሥራች ጃክ ክላርክ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ቴክኖሎጂው አደገኛ መልክ ሲይዝ ሙሉ በሙሉ ለመግታት ‘ኪል ስዊች’ ያስፈልጋል ብሏል።

    አደገኛ ኤአይን ማቆም እና በሦስተኛ ወገን ፍተሻ ማድረግም እንደሚያሻ አሳስቧል።

    ኤአይ ለሰው ልጆች ኅልውና ስጋት እየሆነ መምጣቱ መገለጹን ተከትሎ ባለፉት ቀናት በዘርፉ ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥያቄዎች ቀርበዋል።

    የግዙፍ ኤአይ ኩባንያዎች መሪዎችም ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።

    ትራምፕ ግን የተስተጋባውን ስጋት “ጥግ ከያዙ ዲሞክራቶች የተሰነዘረ” ሲሉ አጣጥለዋል።

    ኤአይ አስጊ ነው መባሉን ያልተቀበሉት ፕሬዝዳንቱ “የሩሲያ ማጭበርበሪያ ነው” ብለዋል።

    “ስለ ኤአይ እና የዳታ ማዕከሎች የሴራ ትንታኔ እየተሰማ ነው። በዚህ የምትደሰተው ቻይና ብቻ ናት። በኤአይ ዘርፍ የሚያሸንፈው አካል በሌላውም ድል ይነሳል” ብለዋል ትራምፕ።

  20. ኢራን ከሳዑዲ ጋር ጦርነት ውስጥ እንዳልገባች አስታወቀች

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የፎቶው ባለመብት, SPUTNIK/KREMLIN/EPA/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን አገራቸው ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ጦርነት ውስጥ አለመግባቷን ተናገሩ።

    ከኢንዲያ ቱደይ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የቀጣናው አገራት ኢራን በአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የምታደርሰውን ጥቃት “በተዛባ መንገድ” እንደሚመለከቱም ገልጸዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ሕንድ ሳሉ ለብሪክስ ጉባዔ ባደረጉት ንግግር “ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ጦርነት ውስጥ አልገባንም። ሁቲዎች የራሳቸው ጉዳዮች አሏቸው። ሁሉም የቀጣናው አገራት ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን መነጋገር አለባቸው” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ “እርስ በራሳችን ጦርነት ውስጥ ወይም ግጭት ውስጥ የምንገባበት ምክንያት የለም” ሲሉም አክለዋል።

    ችግሩ አሜሪካ በአረብ አገራት መሬት ላይ የጦር ሰፈር መገንባቷ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ጥቃት የሚፈጸምባቸው ከእነዚህ የጦር ሰፈሮች እንደሆነም ጠቅሰዋል።

    “እኛ ጥቃት አላደረስንባቸውም። የጥቃቱን መነሻ ዒላማ አድርገናል። ይህም በቀጣናው ቁጣን አጭሯል” ሲሉም ተናግረዋል።