ፕሮጀክቶች ላይ ሠራተኛ በመታጣቱ እስረኞችን አውጥተን እያሠራን ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በሚገነቡ ፕሮጀክቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች “አጥተን፣ እስረኞችን አውጥተን” በማሠራት በቀን እስከ ሰባት መቶ ብር እየከፈልን ነው በማለት ተናገሩ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ እየሰጡ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ለተመነሳላቸው ጥያቄ በእግረ መንገድ በሰጡት ምላሽ ነው። ዐቢይ፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ የለም” የሚል ትችት እንደሚነሳ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት በሚገነቡ ፕሮጀክቶች ላይ ግን ሠራተኛ እየተገኘ እንዳልሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
“አሁን እየገነባን ያለናትን ኢትዮጵያ ለመገንባት፣ ሥራ ኖሮ ሠራተኛ የምንቸገርባቸው ቦታዎች ግን ቁጥር ስፍር የላቸውም። ይሄን የኢትዮጵያ ወላጆች በደንብ እንዲያደምጡኝ እፈልጋለሁ” ብለዋል።
ይህንን “የሠራተኛ እጥረት” ለማካካስ ሲባልም በእስር ቤቶች ውስጥ ያሉ ሰዎች ለቀን ሥራ እየተቀጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
“በተለያየ ክልል ያሉ፣ እኔ በቀጥታ በምከታተላቸው በርካታ ፕሮጀክቶች ሠራተኛ አጥተን፣ እስረኞች አውጥተን በቀን 500፣ 600፣ 700 ብር እየከፈልን በአንድ ቀን ነው የምናሠራው” ሲሉ መንግሥታቸው የተከተለውን አማራጭ ጠቅሰዋል።
“አንዳንድ ቦታ ላይ እስረኞች ራሳቸው ደከመን አንሠራም ወደሚል ደረጃ ደርሰዋል” ሲሉም አክለዋል።
ዐቢይ፣ “ሹፌር ችግር ነው፤ ቀለም ቀቢ ችግር ነው፤ ጽዳት ችግር ነው፤ ወለል አንጣፊ ችግር ነው። ትናንሽ የሚባሉ ሥራዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ ሰው አግኝቶ ማሠራት ያስቸግራል” በማለት ወቅሰዋል።
“ከተለያየ ቦታ ነው ሰው እየወሰድን ፕሮጀክቶችን የምናሠራው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ምናልባትም አንዱ ችግር “ሥራ የሚመርጡ” ሰዎች መብዛት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፤ ሌብነት ደግሞ ሌላኛው ችግር እንደሆነ አክለዋል።
“ሥራ መርጠን፣ ስንሠራም ሰርቀን ከሆነ ያስቸግራል። በቀን 500፣ 600 ብር የቀን ሥራ የሚከፈል ከሆነ፣ እንደው በወር 20፣ 25 ቀን የሠራ ሰው ምን ያክል ገንዘብ ሊያገኝ እንደሚችል ገምቱ” ሲሉም ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።
“ይህንን ንቆ፣ ‘ሥራ የለም ኢትዮጵያ ውስጥ’ ብሎ ከኢትዮጵያ የሚሰደድ ሰው ካለ ምን ሊሠራ ነው እየሄደ ያለው የሚል ጥያቄ ያስነሳል” ብለዋል።