ቀጥታ , ፕሮጀክቶች ላይ ሠራተኛ በመታጣቱ እስረኞችን አውጥተን እያሠራን ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በሚገነቡ ፕሮጀክቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች “አጥተን፣ እስረኞችን አውጥተን” በማሠራት በቀን እስከ ሰባት መቶ ብር እየከፈልን ነው በማለት ተናገሩ። ዐቢይ፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ የለም” የሚል ትችት እንደሚነሳ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት በሚገነቡ ፕሮጀክቶች ላይ ግን ሠራተኛ እየተገኘ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኤል ኒኖ “አንድ ፐርሰንት እንኳ የሚያክል ጫና ሳይፈጥር ነው ያለፈው” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ አፍሪካ ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል የተገመተው ኤል ኒኖ “አንድ ፐርሰንት እንኳ የሚያክል ጫና ሳይፈጥር ነው ያለፈው” አሉ።

    ከባድ የሆነ አየር ሁኔታን የሚፈጥረው ኤል ኒኖ፣ ከመጠን በላይ የሆነው የውሃ መጠን እንዲኖር ወይም የእርጥበት በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ የሚያደርግ ተፈጥሯዊ ክስተት ነው። የዘንድሮው የኤል ኒኖ ክስተት በታሪክ ከተመዘገቡት ጠንካራው እንደሚሆን ተገምቷል።

    የኤል ኒኖ ተጽዕኖ ከፍተኛ ይሆንበታል በተባለው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ይህ የአየር ሁኔታ ከሚያጋጥማቸው አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች።

    በዛሬው የፓርላማ ውሎ ስለዚህ ጉዳይ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ኤል ኒኖ “ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ድርቅ እና ሞት ያስከትላል የሚል ትንበያ ነው የነበረው” ብለዋል። መንግሥትም፣ አስቀድሞ “ሰፊ ዝግጅት” ማድረጉን ጠቅሰዋል።

    ከዝግጅቶቹ መካከል፣ “ቆላማ አካባቢ በፍጥነት የሚደርሱ ምርቶች አዳዲስ ዝርያዎች ማምጣት፣ መኖ በስፋት በማምረት፣ በስፋት ሊመረት የሚችልባቸው አካባቢዎች ደግሞ በደንብ መሥራት” እንደሚገኙበት ዝርዝረዋል።

    አክለውም፣ “ኤልኒኖ ያደርሳል የተባለው ጉዳት እንደው ዜሮ ነው ባልላችሁ፣ አንድ ፐርሰንት እንኳ የሚያክል ጫና ሳይፈጥር ነው ያለፈው፤ ይህም በቂ ዝግጅት በማድረጋችን” ሲሉ ተናግረዋል።

    የዝናብ እጥረት የሚያስከትል የኤል ኒኖ ክስተት ከተፈጠረ በኋላ “ውሃ በዝቶ ጎርፍ ያስከትላል” የሚል ስጋት መኖሩን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን ለመከላከል “ባለፉት ወራት የውሃ ማቆያ ቦታዎች እና ጥንቃቄዎች በስፋት” መሠራታቸውን ተናግረዋል።

    “ኤልኒኖ በምዕራቡ አካባቢ ቡና፣ ስንዴ፣ ሩዝ የሚመረትባቸው አካባቢ ከፍተኛ ዝናብ ነው ያለው፤ የዝናብ ችግር የለም። ቆላማ አካባቢዎች ደግሞ አንዳንድ የተለዩ ቦታዎች ደግሞ ከፍተኛ የዝናብ እጥረት ነበር። ያንን ጊዜ አልፈነዋል” ብለዋል።

    • ተያያዥ ዘገባዎች ፦
  2. ፕሮጀክቶች ላይ ሠራተኛ በመታጣቱ እስረኞችን አውጥተን እያሠራን ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በሚገነቡ ፕሮጀክቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች “አጥተን፣ እስረኞችን አውጥተን” በማሠራት በቀን እስከ ሰባት መቶ ብር እየከፈልን ነው በማለት ተናገሩ።

    በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ እየሰጡ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ለተመነሳላቸው ጥያቄ በእግረ መንገድ በሰጡት ምላሽ ነው። ዐቢይ፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ የለም” የሚል ትችት እንደሚነሳ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት በሚገነቡ ፕሮጀክቶች ላይ ግን ሠራተኛ እየተገኘ እንዳልሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

    “አሁን እየገነባን ያለናትን ኢትዮጵያ ለመገንባት፣ ሥራ ኖሮ ሠራተኛ የምንቸገርባቸው ቦታዎች ግን ቁጥር ስፍር የላቸውም። ይሄን የኢትዮጵያ ወላጆች በደንብ እንዲያደምጡኝ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

    ይህንን “የሠራተኛ እጥረት” ለማካካስ ሲባልም በእስር ቤቶች ውስጥ ያሉ ሰዎች ለቀን ሥራ እየተቀጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

    “በተለያየ ክልል ያሉ፣ እኔ በቀጥታ በምከታተላቸው በርካታ ፕሮጀክቶች ሠራተኛ አጥተን፣ እስረኞች አውጥተን በቀን 500፣ 600፣ 700 ብር እየከፈልን በአንድ ቀን ነው የምናሠራው” ሲሉ መንግሥታቸው የተከተለውን አማራጭ ጠቅሰዋል።

    “አንዳንድ ቦታ ላይ እስረኞች ራሳቸው ደከመን አንሠራም ወደሚል ደረጃ ደርሰዋል” ሲሉም አክለዋል።

    ዐቢይ፣ “ሹፌር ችግር ነው፤ ቀለም ቀቢ ችግር ነው፤ ጽዳት ችግር ነው፤ ወለል አንጣፊ ችግር ነው። ትናንሽ የሚባሉ ሥራዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ ሰው አግኝቶ ማሠራት ያስቸግራል” በማለት ወቅሰዋል።

    “ከተለያየ ቦታ ነው ሰው እየወሰድን ፕሮጀክቶችን የምናሠራው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ምናልባትም አንዱ ችግር “ሥራ የሚመርጡ” ሰዎች መብዛት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፤ ሌብነት ደግሞ ሌላኛው ችግር እንደሆነ አክለዋል።

    “ሥራ መርጠን፣ ስንሠራም ሰርቀን ከሆነ ያስቸግራል። በቀን 500፣ 600 ብር የቀን ሥራ የሚከፈል ከሆነ፣ እንደው በወር 20፣ 25 ቀን የሠራ ሰው ምን ያክል ገንዘብ ሊያገኝ እንደሚችል ገምቱ” ሲሉም ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።

    “ይህንን ንቆ፣ ‘ሥራ የለም ኢትዮጵያ ውስጥ’ ብሎ ከኢትዮጵያ የሚሰደድ ሰው ካለ ምን ሊሠራ ነው እየሄደ ያለው የሚል ጥያቄ ያስነሳል” ብለዋል።

  3. አማጺ ተቃዋሚዎች "በአገር ክህደት መከሰስ አለባቸው" - የምክር ቤት አባሉ ቀጀላ መርዳሳ

    የምክር ቤት አባሉ ቀጀላ መርዳሳ "ከግብፅ ተልዕኮ" ተቀብለዋል ያሏቸው አማጺ ተቃዋሚዎች "በአገር ክህደት" እንዲከሰሱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል።

    እነዚህ ኃይሎች ትደግፋለች ያሏት ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ "ያልታወጀ ጦርነት" ከፍታለች ሲሉ ካይሮ የአገሪቱን ሰላም እና ፀጥታ ለማወክ በመጣር ከስሰዋል።

    አክለውም "የአገር ውስጥ ከሃዲዎች" ያሏቸው ኃይሎች ከግብፅ ድጋፎችን በማግኘት የኢትዮጵያን አንድነት እና ሉዓላዊነትን እንዲሁም በሕዝቡ ደኅንነት ላይ አደጋ ለመጣል እየጣሩ መሆኑን ገልጸዋል።

    ስለዚህም "ያለምንም ሐፍረት ኢትዮጵያን የማፈራረስ የግብፅን ተልዕኮ ተቀብለው ኢትዮጵያን የሚወጉ እና ሉዓላዊነቷ ላይ አደጋ የሚደቅኑ ከሃዲዎች በአገር ክህደት ወንጀል የሚያስጠይቅ ቋሚ የሕግ ማዕቀፍ ሊኖር ይገባል" ሲሉ አቶ ቀጀላ ሐሳብ አቅርበዋል።

    ሥራ አስፈጻሚው አካል ይህንን ሐሳብ ተቀብሎ ረቂቅ የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ በማቅረብ እንዲጸድቅ እንዲያስደርግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ቀጀላ ጠይቀዋል።

  4. የኤርትራን “ሰላም እና ደኅንነት የሚፈታተኑ ድርጊቶችን እስከመቼ እንታገሳለን?” - የምክር ቤት አባል ጋሻው ዳኘው

    ማብራሪያ ለመስጠት በፓርላማ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች አንዱ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ልትገባ ትችላል የሚል ስጋት የተነሳባትን ኤርትራን የተመለከተ ነው።

    ጥያቄ ለማቅረብ ሁለተኛውን ዕድል ያገኙት ጋሻው ዳኘው የተባሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል፣ “ኤርትራ መንግሥት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ ሲከተለው የቆየው አፍራሽ እና አሉታዊ” እንደሆነ በመግለጽ ከስሰዋል።

    “የወንድማማችነት እና የወዳጅነት እጅ ተዘርግቶለትም ጭምር ዕድሉን መጠቀም አልቻለም” ሲሉ የተደመጡት የምክር ቤት አባሉ፣ “ይልቁንም ኢትዮጵያን ሰላም እና መረጋጋት ለማወክ” እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በማንሳት ወንጅለዋል።

    ኤርትራ መንግሥት “አፍራሽ ኃይሎችን በመደገፍ እና በማስታጠቅ የራሱን ሕልውና ማስጠበቅ እንደሚፈልግ በተደጋጋሚ አሳይቷል፤ ከታሪካዊ ስህተቶቹም ሊማር አልቻለም።” ብለዋል።

    የምክር ቤት አባሉ አክለውም፣ “ከዚህ አንጻር የመደመር መንግሥታችን ለዚህ ተደጋጋሚ አፍራሽ ያለው የፖሊሰ አቋም እና የተግባር ምላሽ ምንድነው?” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል። ”የኢትዮጵያ ሰላም እና ደኅንነት የሚፈታተኑ ድርጊቶችንስ እስከ መቼ እንታገሳለን?” በማለትም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል።

    የምክር ቤት አባሉ አክለውም፣ “የሰላምን አማራጭ ለሚቀበሉ ኃይሎች የድርድር እና ሰላማዊ ፖለቲካ በር ክፍት” እንዲሆን እንዲሁም “በኃይል እና በጥፋት መንገድ መቀጠል በሚመርጡ” ላይ “በሕግ መሠረት ጠንካራ እና ውጤታማ እርምጃ” እንዲወሰድ አሳስበዋል።

  5. አሜሪካ ስፔስኤክስ አንድ ሚሊዮን የመረጃ ሳተላይቶችን ወደ ህዋ እንዲያመጥቅ ፈቃድ ሰጠች

    አሜሪካ በህዋ ላይ የመረጃ ማዕከላትን ለመገንባት የሚያግዙ አንድ ሚሊዮን ሳተላይቶችን ወደ መሬት ምህዋር እንዲያመጥቅ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ፈቃድ ለስፔስኤክስ ሰጠች።

    በኤሎን መስክ ባለቤትነት የሚተዳደረው ኩባንያ፣ ለሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚያገለግሉ መረጃዎችን የሚያቀነባብሩ እና ውጤቱን ወደ መሬት መልሰው የሚልኩ ሳተላይቶችን በፀሐይ ኃይል ለማንቀሳቀስ አቅዷል።

    የአሜሪካ ኮሙኒኬሽን ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ፣ “ስታርማይንድ” በመባል የሚታወቀው ይህ ፕሮጀክት “በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የአሜሪካ የላቀ የአስተውሎት ኢኮኖሚ ይደግፋል” ብሏል።

    ይህ ፈቃድ የተሰጠው በመላው አሜሪካ የሚገኙ ማኅበረሰቦች በመሬት ላይ የመረጃ ማዕከላት መስፋፋትን እየተቃወሙ ባሉበት ወቅት ነው።

    ስፔስኤክስ “በምህዋር ላይ የሚገኙ የመረጃ ማዕከላት” “ከምድር አቅም በላይ” እየሆነ የመጣውን እና እያደገ የሄደውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት የኮምፒውተር ኃይል ፍላጎትን ለማሟላት እጅግ ወጪ ቆጣቢ እና ኃይል ቆጣቢ መንገዶች ናቸው ብሎ ያምናል።

    የአሜሪካ ኮሙኒኬሽን ኮሚሽን ሊቀመንበር ብሬንዳን ካር በሰጡት መግለጫ ፕሮጀክቱ “የአሜሪካን መሪነት እና እድገት ለማስቀጠል ለሚያስፈልገው የኮምፒውቲንግ መሠረተ ልማት አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል” ብለዋል።

    መስክ ለዚህ ውሳኔ በኤክስ ገጹ ላይ በሰጠው ምላሽ “በጣም አመሰግናለሁ። ይህ ለአሜሪካ እና ለዓለም ትልቅ ሀብት ይሆናል” ሲል ጽፏል።

    በአሜሪካ ኮሙኒኬሽን ኮሚሽን ፈቃድ መሠረት፣ የሳተላይቶቹን የማምጠቅ ሥራ ቢያንስ እስከ አውሮፓውያኑ ኅዳር 2033 መጀመር አለበት። ስፔስኤክስ እስከ ኅዳር 2035 ድረስ 10 በመቶውን፣ እስከ ኅዳር 2038 ድረስ ደግሞ 50 በመቶውን ማምጠቅ ይጠበቅበታል።

    ኩባንያው የመጀመሪያውን የስታርማይንድ ሳተላይት በሚቀጥለው ዓመት ማምጠቅ እንደሚፈልግ ቀደም ብሎ ገልጿል።

    አንድ ሚሊዮን ሳተላይቶች በሙሉ ይምጠቁ አይምጠቁ ወይም ስፔስኤክስ ከሚጠቀምበት በላይ ቁጥር ፈቃድ ጠይቆ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

    ከ10,000 በላይ በሚሆኑ ሳተላይቶች አማካኝነት ፈጣን ኢንተርኔት እንደሚያቀርበው የአሁኑ የስፔስኤክስ ስታርሊንክ ኔትወርክ ሁሉ፣ የስታርማይንድ ሳተላይቶችም ከ500 እስከ 2,000 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ከፍታ ላይ በዝቅተኛ የመሬት ምህዋር ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ።

    የስታርማይንድ ሳተላይቶች ከስታርሊንክ ሳተላይቶች ጋር በመገናኘት መረጃውን ወደ መሬት ያስተላልፋሉ።

    ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኮምፒውቲንግ አጠቃቀም፣ በዓለም ዙሪያ መቀመጥ እና መቀነባበር ያለበትን የመረጃ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል።

    አዳዲስ ማዕከላት መገንባታቸውን ቢቀጥሉም የሚገነቡበትን ቦታ ማግኘት ግን አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። የመረጃ ማዕከላት ሰፋፊ ቦታ የሚይዙ፣ ለማቀዝቀዣነት ከፍተኛ ኃይል እና ውሃ የሚጠቀሙ በመሆናቸው፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በአቅራቢያቸው እንዲገነቡ አይፈልጉም።

  6. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተገኙበት የፓርላማ ውሎ ተጀምሯል

    መስከረም ላይ በድጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡት ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ሐሙስ ሕዳር 17/2019 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው ማብራሪያ ይሰጣሉ።

    የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎቻቸውን ማቅረብ ጀምረዋል።

    ዐቢይ ዛሬ ማብራሪያ የሚሰጡት፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዳግም ባገረሸበት እንዲሁም ኢትዮጵያ ከኤርትራ እና ሱዳን ጋር የገባችባቸው ውጥረቶች በተባባሱበት ሁኔታ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዙ እና ሌሎች ጉዳዮች በዛሬው ስብሰባ እንደሚነሱ ይጠበቃል።

    በቀጥታ ዘገባችን የፓርላማውን ውሎውን የምናቀርብላችሁ ይሆናል።

  7. ዩክሬን ወታደራዊ አየር ማረፊያ ላይ በፈጸመችው ጥቃት አምስት የሩሲያ የጦር ጄቶች መመታታቸውን ገለጸች

    ዩክሬን ከሞስኮ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የሩሲያ ሳቫስሌይካ የአየር ኃይል ማረፊያ ላይ በፈጸመችው ጥቃት አምስት የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ላይ ጉዳት ማድረሷን አስታወቀች።

    ሦስት ሚግ-31 እና ሁለት ሱ-34 ተዋጊ አውሮፕላኖች መመታታቸውን የዩክሬን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

    የደረሰው ጉዳት መጠን ገና እየተገመገመ መሆኑን የጠቀሰው ጽሕፈት ቤቱ፣ “ከዚህም የተሻለም ዜና ሊሰማ ይችላል” ብሏል።

    የአየር ኃይል ማረፊያው ለመምታት ምን ዓይነት የጦር መሣሪያዎችን እንደተጠቀመ ግን አላብራራም።

    ሩሲያ እስካሁን ተፈጽሟል ስለተባለው ጥቃት አስተያየት አልሰጠችም።

    በሩሲያ ኒዥኒ ኖቭጎሮድ ክልል የሚገኘው ሳቫስሌይካ የአየር ኃይል አውሮፕላን ማረፊያ ለበርካታ ዓመታት በዩክሬን ዒላማ ሲደረግ ቆይቷል። አየር ማረፊያው የሩሲያን ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎች እና ተንሸራታች ቦምቦችን ለማስወንጨፍ የምትጠቀምባቸውን አውሮፕላኖች ያስተናግዳል።

    ከስፍራው የሚነሱት በተለይም የሩሲያ ሚግ-31 ጄቶች የሚሸከሟቸው ኪንዣል ሚሳዔሎች ትላልቅ መሠረተ ልማቶችን እና ወታደራዊ ዒላማዎችን በመምታት የሚታወቁ ሲሆን መትቶ ለመጣልም አስቸጋሪ ናቸው።

    በዚህም የተነሳ ሚግ-31 ጄቶች እንቅስቃሴ ሲጀምሩ በመላው ዩክሬን በተደጋጋሚ አገር አቀፍ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደወሎች እንዲጮሁ ይደረጋል።

    በተጨማሪም ዩክሬን ሌሊቱን በፈጸመችው ጥቃት፣ ከጦር ግንባር 800 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በሚገኘው የሩሲያ ሳማራ ክልል ሁለት የነዳጅ ማጣሪያዎችን መምታቷን ገልጻለች። ኪዬቭ የሞስኮን ነዳጅ ማጣራት አቅም ያዳከሙ ተከታታይ የረጅም ርቀት ጥቃቶች መፈጸሟ ይታወሳል።

    የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር፣ “ጠገናችኋቸው? እንደገና እንመታቸዋለን” የሚል ዛቻ አስተላልፏል።

    የሳማራ ክልል አስተዳዳሪ ቭያቼስላቭ ፌዶሪሽቼቭ ሌሊቱን የተፈጸሙትን ጥቃቶች “ትክክለኛ መከራ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል። ከ145 በላይ ድሮኖች ተመትተው መውደቃቸውንም ተናግረዋል።

    አስተዳዳሪው እንደሚናገሩት፣ በጥቃቶቹ አንድ ሰው ሲገደልም፣ በርካታ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ አጋጥሟቸዋል።

    በተጨማሪም ኪዬቭ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር በሚገኙ የዩክሬን ግዛቶች ውስጥ አንድ የራዳር ሥርዓት እንዲሁም የነዳጅ እና የሎጂስቲክስ ማከማቻዎችን መምታቷን አስታውቃለች።

    የኪዬቭ የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪ በፍጥነት እያደረገ ነው። ሞስኮ ሙሉ ወረራ ከጀመረች ወዲህ ባሉት ዓመታት ዩክሬን ከጦር ግንባር በብዙ ርቀው በሚገኙ የሩሲያ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟል የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

    የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአገሪቱ የኃይል ማመንጫ እና ነዳጅ ተቋማት ዙሪያ የሚወሰዱ የደኅንነት እርምጃዎች እንዲጠናከሩ ማክሰኞ ዕለት ጥሪ አቅርበዋል።

    ሩሲያ “ወሳኝ ጉዳት” ሳይደርስባት የአገር ውስጥ የነዳጅ ገበያዋን ማረጋጋት መቻሏን የሚናገሩት ፑቲን፣ ሞስኮ በኪዬቭ ላይ “አይቀሬ” የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ዝተዋል።

  8. የየመን ሁቲዎች የሳዑዲ አረቢያ ትልቁ ነዳጅ ማጣሪያ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ገለጹ

    የየመን ሁቲዎች ረቡዕ ዕለት ራስ ታኑራ በተባለው የሳዑዲ አረቢያ ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያ እና በሪያድ የፋይናንስ ቀጣና ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታወቁ።

    ሳዑዲ አረቢያ፣ ሁቲዎች ራስ ታኑራ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ የሰነዘሩትን የድሮን ጥቃት ማክሸፏን ተናግራለች። የሳተላይት ምስሎች ግን ከዚህ ነዳጅ ማጣሪያ ስፍራ ላይ ትልቅ ጭስ ወደላይ እየወጣ መሆኑን አሳይተዋል።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ጥቃት እንደፈጸሙበት የገለጹት ራስ ታኑራ፣ ከዓለም ትላልቅ የድፍድፍ ነዳጅ ኤክስፖርት ወደቦች አንዱ አጠገብ የሚገኝ የሳዑዲ አረቢያ ትልቁ የነዳጅ ማጣሪያ ነው።

    600 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ገደማ ስፋት እንዳለው የሚገመተው የነዳጅ ማጣሪያ ስፋቱ ከአሜሪካዋ ቺካጎ ከተማ ጋር እንደሚቀራረብ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭን ጠቅሶ ዘገቧል።

    በሌላ በኩል፣ በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ጦር ረቡዕ ዕለት በአገሪቱ የቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ በምትገኘው ጂዳ ወደብ አቅራቢያ አንድ የሁቲ ድሮንን ጠልፎ ማውደሙን አስታውቋል።

    የየመን ሁቲዎችም ይህ ከተገለጸ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ሳዑዲአረቢያ በየመን ወደብ ላይ ለፈጸመችው ጥቃት የአጸፋ እርምጃ መውሰዳቸውን ተናግረዋል። በዚህ የአጸፋ ጥቃት በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙትን ሁለቱን የጂዳ እና የጃዛን ወደቦችን ዒላማ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

    የሁቲዎች እና የሳዑዲ መራሹ ጥምር ጦር ግጭት ባለፉት ቀናት ይበልጥ ተባብሶ ታይቷል።

    የትናንቶቹ ጥቃቶች የተፈጸሙት ከሁቲዎች ጋር የሚዋጋው በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት፣ በየመን የቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘውን የሆዴይዳ ወደብን ዒላማ ያደረገ ጥቃት መፈጸሙን ካስታወቀ በኋላ ነው።

    የሁቲዎች ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ “ሁለቱም ዘመቻዎች ዒላማዎቻቸው ላይ ጉዳት አድርሰዋል” ብለዋል።

    ከዚህ አስቀድሞ፣ በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በሁቲዎች የተወነጨፈ ተተኳሽ ጃዛን ወደብ ላይ ማረፉን አስታውቆ ነበር።

    የሳዑዲ መራሹ ጥምረት ቃል አቀባይ ቱርኪ አል ማሊኪ “ቀላል ጉዳት የደረሰ ሲሆን የተገደለ ወይም የቆሰለ ሲቪል የለም” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

    አክለውም «የተተኳሹን ዓይነት ለመለየት ጥረቶች ቀጥለዋል” ብለዋል።

    ዋና ከተማዋ ሰንዓን ጨምሮ አብዛኛውን የምዕራብ የመን ክፍል የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች፣ ረግቦ የነበረው የመን ግጭት በኢራን ጦርነትን ምክንያት ባለፈው ሐምሌ ላይ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በሳዑዲ አየር ማረፊያዎች፣ የነዳጅ መሠረተ ልማቶች እና የመስሪያ ቤት ሕንፃዎች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

    ከዚህ ቀደም በግዙፉ የሳዑዲ የነዳጅ አምራች አራምኮ ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች፣ ተቋሙ በጊዜያዊነት ሥራ እንዲያቆም አስገድደው ነበር። አየር ማረፊያዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶችም ወደ ሪያድ የሚደረጉ አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ በረራዎች እንዲሰረዙ ምክንያት ሆነዋል።

  9. የኅዳር 17 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ዘገባ ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የሐሙስ ኅዳር 17 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ዘገባችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። አብራችሁን እንድትቆዩ በአክብሮት እንጋብዛለን።