ቀጥታ, “የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዳይካሄድ ኃይሎችን ገዝተው አሰማርተዋል" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች” ሲሉ የጠሯቸው አካላት ሰላማዊ ምርጫ እንዳይካሄድ “የገዟቸውን ኃይሎች” በስፋት ማሰማራታቸውን ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በትውልድ ቀያቸው በሻሻ ድምፅ ከሰጡ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለምልስ ላይ ታሪካዊ ጠላቶች ያሏቸውን ኃይሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል “እምነት እንድንይዝ ሙከራ አድርገዋል” ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ጋዜጠኞች ምርጫውን ለመዘገብ ሲንቀሳቀሱ ክልከላ እንደገጠማቸው ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

    የኢትዯጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቦርዱ ተመዝግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መገናኛ ብዙኃን “በውስን አካባቢዎች” ሥራ እንዳቆሙ አስታወቀ።

    ትናንት እሑድ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር የተባለው መገናኛ ብዙኃን ዘጋቢዎቹ የምርጫ ዝግጅቱን ለመቃኘት በምርጫ ጣቢያዎች ሲንቀሳቀሱ ከምርጫ አስፈፃሚዎች እና ከፀጥታ ኃይሎች ክልከላ እንደተደረገባቸው አስታውቋል።

    በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 “ሁለት የብልጽግና ፓርቲ ታዛቢዎች መሆናቸውን የገለጹ ግለሰቦች” ከበላይ ትዕዛዝ እስኪሰጣቸው ድረስ ክልከላ ካደረጉ በኋላ ፈቃድ ቢሰጡም ምሥል መቅረፅ ግን እንደከለከሉ ገልጿል።

    በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በአንድ የምርጫ ጣቢያ የፀጥታ ኃይሎች ተመሳሳይ ክልከላ ማድረጋቸውን መገናኛ ብዙኃኑ አስታውቋል።

    በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደግሞ ጥበቃ ለማድረግ የተሰማሩ የፖሊስ አባላት ምንም እንኳ በምርጫ ቦርድ ለዘጋቢዎቹ የተሰጠን መታወቂያ ቢመለከቱም “በስፍራው መዘገብም ሆነ ፎቶ ማንሳት ከልክለዋል” ብሏል።

    ኢትዮጵያ ኢንሳይደር በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማም ተመሳሳይ ክልከላ እንደገጠመው ገልጿል።

    ቢቢሲ ምርጫውን በአገር ውስጥ ለመዘገብ ፈቃድ አልተሰጠውም።

    ቦርዱ መገናኛ ብዙኃን በተለያዩ አካባቢዎች ለመዘገብ “ደብዳቤ” እንዲፃፍላቸው መጠየቃቸውን ጠቁሞ፤ መገናኛ ብዙኃንን ከሥራ ማስቆም “የተሳሳተ” ነው ብሏል።

    አክሎም የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር መሠረት “ማንኛውም ሰው ቦርዱ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት ሲያስፈጽም የመተባበር ግዴታ አለበት” በማለት አሳስቧል፡፡

    ቦርዱ ምርጫውን እንዲዘግቡ 68 መገናኛ ብዙኃንን እና 1,815 ጋዜጠኞችን መመዝገቡን ገልጿል። እነዚህ ባለሙያዎች በምርጫ ጣቢያዎች 200 ሜትር ንፍቀ ክበበ ውስጥ ገብተው መዘገብ የሚያስችላቸውን መለያ ባጅ መስጠቱን ተናግሯል።

  2. “የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዳይካሄድ ኃይሎችን ገዝተው አሰማርተዋል" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች” ሲሉ የጠሯቸው አካላት ሰላማዊ ምርጫ እንዳይካሄድ “የገዟቸውን ኃይሎች” በስፋት ማሰማራታቸውን ገለጹ።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በትውልድ ቀያቸው በሻሻ ድምፅ ከሰጡ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ታሪካዊ ጠላቶች ያሏቸውን ኃይሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል “እምነት እንድንይዝ ሙከራ አድርገዋል” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ “ዲሞክራሲ ሥርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመገንባት የሚሻውን፣ የሚፈልገውን ለመወሰን መካሪ፣ ገሳጭ” እንደማያስፈልገው ማለዳ ድምጹን ለመስጠት በመውጣት አሳይቷል ሲሉ ተናግረዋል።

    የሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ዛሬ ከማለዳው አስራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በጅማ ዞን በሻሻ ወረዳ ተገኝተው መርጠዋል።

    በዚህ አገራዊ ምርጫ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን ቦርዱ ያስታወቀ ሲሆን፣ በምርጫው 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሳተፋሉ።

    ምርጫውን ከአገር ውስጥ ታዛቢዎች ባሻገር የአፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ ይታዘቡታል።

  3. ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮች

    ለሰባተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ዛሬ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. መራጮች በየአካባቢያቸው ድምጽ እየሰጡ ነው። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከትግራይ ክልል እና ከአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች ውጪ ምርጫው እንደሚካሄድ አስታውቋል።

    ለዚህ ምርጫ 50.5 ሚሊዮን ሰዎች በመራጭነት የተመዘገቡ ሲሆን፣ ይህም አገሪቱ ካላት አዋቂ ሕዝብ ከሁለት ሦስተኛው የሚበልጥ ነው።

    የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንሚያመለክተው ለመራጭነት ከተመዘገቡት ከ50 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን መካከል ሴቶች 46 በመቶ እንዲሁም ወንዶች 54 በመቶ ናቸው።

    ዘንድሮ በመራጭነት የተመዘገቡት ዜጎች ቁጥር ከአምስት ዓመት በፊት ከተመዘገቡት በ32 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ ካለፉት ስድስት ምርጫዎችም የበለጠ ነው።

  4. የሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ በምስል

  5. የኢትዮጵያ ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ እየተካሄደ ነው

    ከትግራይ ክልል በስተቀር በመላ አገሪቱ በሚካሄደው ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ድምጽ መስጠት ተጀምሯል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ እና በአማራ ክልል ደግሞ በተወሰኑ አካባቢዎች ምርጫው በዛሬው ዕለት እንደማይካሄድ ቀደም ብሎ አስታውቋል።

    ምርጫ ቦርድ በአማራ ክልል በስምንት የምርጫ ክልሎች በዛሬው ዕለት ድምጽ እንደማይሰጥ ሲያሳውቅ ከጠቀሳቸው ቦታዎች መካከል ደቡብ እና ምዕራብ ጎንደር፣ ደጋ ዳሞት እና አምባሰል ይገኙበታል።

    በሰባተኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ከ 54 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን ቦርዱ መግለጹ አይዘነጋም። በምርጫው የሚሳተፉ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲሆኑ ፓርቲዎቹ ከ10,000 በላይ እጩዎች ለማስመረጥ አስመዝግበዋል። ከእነዚህ ውስጥም 2,080 ለፓርላማ የሚወዳደሩ ይሆናል። 8,352 እጩዎች ደግሞ ለክልል ምክርቤት ሲዎዳደሩ፤ 80 እጩዎች በግላቸው ይወዳደራሉ። 55 የአገር ውስጥ ሲቪክ ማኅበራት ምርጫውን የሚታዘቡ ሲሆን የአፍሪካ ኅብረት በቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመራ የታዛቢ ቡድን አሰማርቷል።

    የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡደንን የሚመሩት ደግሞ ቀድሞው የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ስፔሲዮሳ ዋንድሬ ካዚምብዌ ናቸው።