እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል ከሊባኖስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ብትደርስም በደቡባዊ ሊባኖስ ሐሙስ ዕለት በፈጸመችው ከባድ ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴተር አስታወቀ።
ሁለተኛ ሳምንቱን በያዘው የተኩስ አቁም አሁንም እስራኤል ጥቃቶችን መፈጸሟን ቀጥላለች።
እስራኤል ሐሙስ ዕለት የሄዝቦላህ መሠረተ ልማት ናቸው ባለቻቸው ስፍራዎች በፈጸመችው ድብደባ 23 ሰዎች መጎዳታቸውን እና ከእነዚህም መካከል ስምንቱ ሕጻናት፣ ሰባቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ሄዝቦላህ በበኩሉ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል በሚገኙ የእስራኤል ጦር አባላት ላይ በድሮን ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።
በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል በዋሺንግተን ንግግር ከተደረገ በኋላ እአአ ከሚያዚያ 16 ጀምሮ የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረሰ ቢሆንም ግጭቶች ቀጥለዋል።
የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ኦወን “ምንም እንኳ የተኩስ አቁም ቢደረስም” እስራኤል ስምመነቱን በመጣስ “ጥቃት መፈጸሟን እንደቀጠለች” መሆኗን የተቹ ሲሆን በሚደርሱ የአየር ድብደባዎች የመኖሪያ እና የአምልኮ ስፍራዎች እየወደሙ ነው ብለዋል።
"እስራኤል ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና ስምምነቶችን እንድታከብር እና በሲቪሎች፣ በሕክምና ባለሙያዎች፣ በሲቪል መከላከያ እና በሰብአዊ ድርጅቶች ላይ ማነጣጠሯን እንድታቆም ጫና መደረግ አለበት" ብለዋል።
እስራኤለ በበኩሏ ጥቃቶቹን የምትፈጽመው ሄዝቦላህ ለሚተኩሳቸው ድሮን እና ሮኬቶች ምላሽ ለመስጠት መሆንን በመግለጽ ትከራከራለች።
በተኩስ አቁም ስምምነቱ ሄዝቦላህ ያልተካተተ ቢሆንም እስራኤል የምታከብር ከሆነ ለስምምነቱ እነደሚገዛ አስታውቆ ነበር።
የተኩስ አቁሙ በቤይሩት ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚካሄደውን ጥቃት በአብዛኛው ቢያቆምም፣ በደቡባዊ ሊባኖስ ግን የሚካሄደው ድብደባ እንደቀጠለ ነው።



















