በአትላንቲክ መርከብ ላይ በተከሰተ የቫይረስ ወረርሽኝ ሦስት ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

በአትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ባለ መርከብ ላይ የሃንታቫይረስ ወረርሽኝ እንደሆነ በሚጠረጠር ምክንያት የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዓለም ጤና ድርጅት ለቢቢሲ ገለጸ።

አንድ የተረጋገጠ እና አምስት የተጠረጠሩ ሰዎች መኖራቸውን ዘግቧል። አንድ የ69 ዓመት የዩኬ ዜጋ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ውስጥ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል። የአካባቢው ባለሥልጣናት በኋላ ላይ ቫይረሱ እንዳለባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሃንታቫይረስ ብዙውን ጊዜ ከአይጦች በሽንታቸው ወይም በሰገራቸው በኩል ወደ ሰዎች ይተላለፋል። ከባድ የመተንፈሻ አካላት በሽታ ሊያስከትል የሚችል ሲሆን አልፎ አልፎም በሰዎች መካከል ሊተላለፍ ይችላል።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርቶችን እየተከታተለ መሆኑን እና የብሪታንያ ዜጎችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ወረርሽኙ ከአርጀንቲና ወደ ኬፕ ቨርዴ በሚጓዝ ኤምቪ ሆንዲየስ በተሰኘ መርከብ ላይ መከሰቱ ተዘግቧል።

ኤምቪ ሆንዲየስ የሚመራው በቱሪስት ኩባንያው ኦሽንዋይድ ኤክስፒዲሽንስ ነው።

ድርጅቱ በድረገጹ ላይ በወጣው የጉዞ መርሃ ግብር መሠረት ኤምቪ ሆንዲየስ መጋቢት 20 ቀን ከደቡብ አርጀንቲና ኡሹዋያ ተነስቶ ጉዞውን ግንቦት 4 በኬፕ ቨርዴ እንደሚያጠናቅቅ ይገልጻል።

107.6 ሜትር ርዝመት ያለው መርከብ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን 170 መንገደኞች፣ 57 የመርከብ አባላት፣ 13 አስጎብኚዎች እና አንድ ዶክተር አሉት።

የደቡብ አፍሪካ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፎስተር ሞሃሌ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በመርከቡ ላይ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ 150 ቱሪስቶች ነበሩ።

የዓለም ጤና ድርጅት ሦስት ሰዎች መሞታቸውን ከማረጋገጡ በፊት ሞሃሌ ለቢቢሲ ቢያንስ ሁለት ሰዎች እንደሞቱ ተናግረዋል።

እነዚህም የ70 ዓመት ወንድ እና የ69 ዓመት ሴት ባልና ሚስት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ግለሰቡ በድንገት ታመው ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የሆድ ሕመም እና ተቅማጥ አጋጠማቸው። በደቡብ አትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ በምትገኘው የእንግሊዝ ግዛት ሴንት ሄሌና ደሴት ሲደርሱ ህይወታቸው አልፏል።

ሴትየዋም በመርከቡ ላይ ታመው ወደ ደቡብ አፍሪካ ቢወሰዱም በጆሃንስበርግ ሆስፒታል ህይወታቸው አልፏል።

የኤኤፍፒ የዜና ወኪል አንድን ምንጭ ጠቅሶ እንደዘገበው ሦስተኛው ሞት የተከሰተው በመርከቡ ላይ ነው።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ምንጩ አክለውም ሌሎች ሁለት የታመሙ ተሳፋሪዎችን በኬፕ ቨርዴ ሆስፒታል ውስጥ ተለይተው እንዲቆዩ ለማድረግ ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል።

መርከቡ በመቀጠል ወደ ስፔን ካናሪ ደሴቶች እንደሚያመራ ተዘግቧል።

የዓለም ጤና ድርጅት በአባል አገራት እና በመርከቡ ሠራተኞች መካከል ሁለት ምልክቶችን የሚያሳዩ ተሳፋሪዎች የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ እና የህብረተሰብ ጤና ስጋት ግምገማ እና ድጋፍ ለማድረግ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።