አዲሱ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ናቸው? ለምንስ የማይገመቱ ሆኑ?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ልክ እንደ አንዲ በርንሃም ብዙም ፈተና ሳይገጥመው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆን እምብዛም ነው።

የቢቢሲ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የፖለቲካ ዘጋቢ ሮብ ዋትሰን እንደሚለው፣ የዚህ ምክንያቱ ገዥው ሌበር ፓርቲ በመጨረሻ "ከአመራርነት ውድድር" ይልቅ "በሹመት" ስለሚወስን በፖሊሲዎቻቸው እንዲሁም በሚከተሉት የአስተዳደር ዘይቤ ላይ ብዙም ክርክር አልተደረገም።

ይህ ግን ጥሩም፣ መጥፎም ጎን አለው።

በፓርቲው ውስጥ ክፍፍል እንዳይፈጠር በማድረግ መልካም ጎን ቢኖረውም፣ አዲሱ መሪው እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳይፈተኑ ግን አድርጓል።

አዲሱ ተመራጭ ምን ዓይነት ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ በቅርቡ የሚታይ ይሆናል።

ሆኖም በርንሃም ለአስር ዓመታት የግሬተር ማንቸስተር ከንቲባ ከመሆናቸው ባሻገር እምብዛም የሚታወቁ ሰው አይደሉም።

ስለበርንሃም የሚታወቁ ነገሮች የሚያመለክቱት አሁን እንዳሉት አብዛኞቹ ፖለቲከኞች፣ ከፖለቲካው ሥርዓት ውጪም፤ ውስጥም የነበሩ እና አሁን ጎልተው የወጡ መሆናቸውን ነው።

በርንሃም በሰሜን እንግሊዝ የሠራተኛው መደብ ውስጥ በማደጋቸው ከውጭ ሆነው ፖለቲካውን ማየት ችለዋል።

እንደ ውስጥ አዋቂ ደግሞ በታዋቂው ኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የቶኒብሌር እና ጎርደን ብራውን ሌበር መንግሥት ተስፋ ያለው ወጣት ሆነው በፍጥነት ወደ ፖለቲካው ገብተዋል።

በርንሃም በግለ ሰብዕናቸው ራሳቸውን ኮፍሰው የማያዩ እና ማንኛውም ተራ ሰው ሊቀርባቸው የሚችል ዓይነት ሰው ናቸው።

ቢራ እንዲሁም የእንግሊዝ ታዋቂ ምግብ የሆነውን ዓሳ እና የድንች ጥብስ ይወዳሉ።

ስለእግር ኳስ እና ሙዚቃ ማውራት የሚወዱ ሲሆን፣ በቅርብ ጊዜ ካሉ አብዛኞቹ ፖለቲከኞች ጋር ሲነጻጸሩ ዘመናዊ እና ፋሽንን የሚከተሉ ይመስላሉ።

በፖለቲካው ረገድም በርንሃም እንደሚሉት ማርጋሬ ታቸር የአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ወግ አጥባቂውን መንግሥት ነፃ እና ግላዊ ማድረጋቸውን በመጥላት ነበር በታዳጊነታቸው ወደ ፖለቲካው የተሳቡት።

ፓርቲው በወቅቱ የወሰደውን እርምጃ እርሳቸው ያደጉበትን ሰሜን እንግሊዝ የኢንደስትሪ ሥርዓት በማኮላሸት እና ተስፋ በማስቆረጥ ተጠያቂ ያደርጋሉ።

ከዚያን ጊዜ በኋላም ሶሻል ዲሞክራት ወደ ሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ መጥተዋል።

ልክ በርካታ ግራ ዘመም አውሮፓውያን እንዳደረጉት ሁሉ በርንሃምም መንግሥትን እንደ መልካም የሚመለከቱ ሲሆን፣ ትኩረታቸውን ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ማኅረሰቦች ላይ አድርገዋል።

ላለፉት 40 ዓመታት ብዙውን ጊዜ የኒዎ ሊበራሊዝም አስተሳሰብን ሲተቹ ቆይተዋል። ይህ ሥርዓት ተራ ሰዎችን ተጠቃሚ አላደረገም ይላሉ።

ያኔ ይህን ሲሉ በትክክል ምን ማለታቸው እንደሆነ ብዙም ግልፅ አልነበረም። ርዕዮተ ዓለማዊ ወይም የፖሊሲ ለውጥ ፍላጎታቸው ተደርጎም አልታየም ነበር።

በርንሃም የብሪታኒያን የውጭ እና የአገር ውስጥ ፖሊሲ ሊለውጡ ይችላሉ?

በርንሃም እስካሁን ስለአቋማቸው ብዙም ስላልተናገሩ ይህ አይታወቅም።

በአገር ውስጥ ፖሊሲ ላይ ብዙ ክፍተቶች አሉ። ብሪታኒያ ዝቅተኛ እድገት እና ከፍተኛ ብድር ያለባት አገር ናት። የሕዝብ ወጪ እና ግብር በታሪክ ከፍተኛው ሆኗል።

ግራ ዘመም የሌበር አባላት መንግሥት በሰፊው ጣልቃ እንዲገባ ይፈልጋሉ። ይህ ግን ቀላል አይሆንም።

የበርንሃም መንግሥት በመጨረሻው ምርጫ ፓርቲያቸው ብዙ ግብር እንደማይጨምር ወይም ያለገደብ ብድር ላለመውሰድ በገባው ቃል መወጠራቸውም አይቀሬ ነው።

በርንሃም የሌበር ፓርቲ መሪ ሆነው ከተመረጡ በኋላ ካነሷቸው ዋና ዋና ሀሳቦች መካከል አንዱ ሥልጣንን እና ገንዘብን ከለንደን ወደ ክልሎች የማዛወር ወይም ሥልጣን ክፍፍልን የማስፋት ጉዳይ ነው፤ ሆኖም ይህ ሃሳብ ግልጽነት የጎደለው ነው።

የውጭ ፖሊሲን በተመለከተ በርንሃም በሥራ ዘመናቸው ብዙም ትኩረት ያልሰጡበት ጉዳይ ቢሆንም ከለውጥ ይልቅ ቀጣይነት እንደሚኖር ይጠበቃል።

የውጭ ፖሊሲ ከፓርቲ ፖለቲካ ወይም በአመራሩ የግል ፍላጎት ሳይሆን በመልክዓ ምድር፣ በታሪክ እና በብሔራዊ ፍላጎት እና ሁኔታዎችን ተመርኩዞ የሚቀረጽ በመሆኑ በነበረበት መቀጠሉ አያስገርምም።

እንደ ቀደሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ሁሉ በርንሃንም ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በጣም በቅርበት ባይሆንም ማጠናከር ይፈልጋሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የብሪታኒያ ተልዕኮዎች ለሕግ የበላይነት፣ ለዓለም አቀፍ ልምዶች እና እንደ የተባበሩት መንግሥታት ላሉ የብዙ አገራት ድርጅቶች ወሳኝ እንደሆኑ ማስተዋወቅ ይሻሉ።

ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነትም ማጠናከር ይፈልጋሉ። ይህ ግን ከፕሬዚደንት ትራምፕ ጋር የሚደረግ የግል ግንኙነት ላይሆን ይችላል። ከእርሳቸውም ጋርም ቢሆን መሞከራቸው እርግጥ ነው።

በርንሃም በአስር ዓመት ውስጥ ሰባተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆናቸው ተግዳሮቶች ሊገጥማቸው ይችላል።

የሥልጣን መገለባበጡ በራሱ በርንሃም የሚወጡት ተራራ እንዳለ የሚያመለክት ነው።

ሆኖም ለበርንሃም ጥሩም መጥፎም ዜናዎች አሉ።

መጥፎው ዜና ስድስቱን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የፈተነው የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ተግዳሮቶች መጨመራቸው ነው።

ጥሩው ዜና ደግሞ በግራ ዘመም እና ቀኝ አክራሪ ፖፑሊስት መካከል ያሉት ግሪን እና ሪፎርም የተባሉ ፓርቲዎች ስጋት አለመሆናቸው ነው።

በርንሃም፤ የተወሰኑ ሰዎች ስጋት፣ የሚወደዱ ቀላል ሰው፣ የሌበር ፓርላማ አባላት ተስፋ ፣ እየተጠበቁ ያሉ ቆፍጣናው መንግሥት ? በጠቅላላው ስለበርንሃም የማይታወቁ ብዙ ነገሮች አሉ።

አንዲ በርንሃም አዲሱ የሌበር ፓርቲ መሪ ሲሆኑ በቅርቡ በአስር ዓመት ውስጥ 7ኛው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ።

በርንሃም የሌበር ፓርቲ መሪ ሆነው የተመረጡት አርብ ዕለት ሲሆን እስከ ሰኞ ድረስ የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ቦታ አይረከቡም።

የሥልጣን ርክክብ ሒደቱ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ሰኞ ከንጉስ ቻርልስ ጋር በባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ተገናኝተው መልቀቂያቸውን በይፋ ካስገቡ በኋላ ይጀምራል።

ከዚያም ንጉሱ በርንሃምን አግኝተው መንግሥት እንዲመሰርቱ ይጠይቋቸዋል።

በርንሃም ጥያቄውን ከተቀበሉ በኋላ በይፋ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ።