በኮምቦልቻ ከተማ በደረሰ የመኪና አደጋ አብዛኞቹ ሴቶች የሆኑ ከ30 በላይ ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, kombolcha communication
በአማራ ክልል፣ ኮምቦልቻ ከተማ በደረሰ የትራፊክ አደጋ እናት እና ልጅን ጨምሮ 31 ሰዎች መሞታቸውን የከተማዋ ፖሊስ አስታወቀ።
64 ሰዎችን አሳፍሮ ከደሴ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ የነበረው አውቶብስ በኮምቦልቻ ከተማ ሐረጎ በሚባል ሥፍራ በገጠመው አደጋ ነው ሰው ሕይወት የጠፋው።
በአደጋው ሕይወታቸው ከጠፋው መንገደኞች በተጨማሪ ሌሎች ተሳፋሪዎች ላይም ከባድ እና ቀላል ጉዳት መድረሱን የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ጌታቸው ሙሕዬ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሰኞ ሰኔ 8/2018 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ የተነሳው የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ በጉዞ ላይ ሳለ ከ100 ሜትር በላይ ጥልቀት ካለው ገደል ውስጥ በመግባቱ ነው አሰቃቂው አደጋ የደረሰው።
ሕይወታቸው ካለፈው 31 ተሳፋሪዎች በተጨማሪ 33 መንገደኞች ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው እና በኮምቦልቻ እና ደሴ ሪፈራል ሆስፒታሎች በሕክምና ላይ እንደሚገኙ የፖሊስ አዛዡ ተናግረዋል።
በአደጋው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በመኖራቸው የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት እንዳለም ኮማንደሩ ገልጸዋል።
በትራፊክ አደጋው ምክንያት የሞቱት 11 ወንዶች እና 20 ሴቶች መሆናቸውን ኮማንደር ጌታቸው ገልጸዋል። ከሟቾቹ መካከል እናት እናን ልጅን ጨምሮ አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው።
የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሱ አሽከርካሪ እና ረዳቱም በአደጋው ሕይወታቸው ማለፉ ተነግሯል።
ከ30 በላይ ሰዎች ሕይወት የጠፋበት የዚህ ከባድ የተሽከርካሪ አደጋ ምክንያትን ለማወቅ ፖሊስ ምርመራ እደያረገ እንደሆነ የፖሊስ መምሪያው አዛዥ ጨምረው ገልጸዋል።
አደጋው የደረሰበት ሥፍራ ጠመዝማዛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ አደጋ የሚከሰትበት ስፍራ መሆኑን ኮማንደር ጌታቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ቦታው ለአደጋ ተጋላጭ ከመሆኑ የተነሳ ፖሊስ ለአሽከርካሪዎች የጥንቃቄ መልዕክት በማዘጋጀት በጥንቃቄ እንዲያሽከረክሩ ግንዛቤ የመፍጠር ጥረት መደረጉን አዛዡ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የደረሱ አደጋዎች "ከጥንቃቄ ጉድለት፣ ጠጥቶ ከመንዳት እና ጫት ቅሞ ከማሽከርከር" ጋር የተያያዙ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
"የአሽከርካሪዎች እንዝህላልነት እና ተሽከርካሪዎችን በየጊዜው ጥገና እና እድሳት ያለማድረግ ችግር እያስከተለ ነው" ሲሉም የአደጋዎችን መንስኤ አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, kombolcha communication















