እስራኤል ተሽከርካሪ ላይ በፈፀመችው ጥቃት አንድ የሊባኖስ ጄነራልን ጨምሮ ሦስት ወታደሮች ተገደሉ

ጥቃት የደረሰበት እና የተጎዳ ተሽከርካሪ

የፎቶው ባለመብት, Lebanese Army

የምስሉ መግለጫ, የሊባኖስ ጦር በእስራኤል ጥቃት ተፈፀመበት ያለውን ተሽከርካሪ ምሥል ይፋ አድርጓል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የእስራኤል መከላከያ የሊባኖስ ወታደሮችን የያዘ ተሽከርካሪ ላይ በደቡባዊ ሊባኖስ ጥቃት መፈፀሙን ካረጋገጠ በኋላ ምርመራ መክፈቱን ተናገረ።

የሊባኖስ ጦር ቅዳሜ ዕለት "ከባድ እና አረመኒያዊ" ሲል በገለፀው ጥቃት ብርጋዴር ጀኔራል፣ ካፒቴን እና አንድ ወታደር መገደላቸውን አስታውቋል።

የእስራኤል ጦር ተሽከርካሪው "በሚያጠራጥር ሁኔታ ወደ ኃይሉ እየተጠጋ" እንደነበር ጠቁሞ በአካባቢው የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ገልጿል።

እስራኤል በቀጥታ ከሊባኖስ መንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ ባትሆንም ከእስራኤል መንግሥት ጋር የተኩስ አቁም ለመድረስ እየተነጋገረ ነው።

ይሁን እንጂ ካለፈ መጋቢት ጀምሮ በተለይም በደቡብ ሊባኖስ በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ የሮኬት እና ድሮን ጥቃቶችን መፈፀሙን ተከትሎ እየተዋጉ ነው።

የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ በሳምንቱ መገባደጃ ቀናት የመሣሪያ መጋዘኖች እና የማዘዣ ጣቢያዎችን ጨምሮ 150 የሄዝቦላህ "የመሠረተ ልማት ዒላማዎችን" መደብደቡን አስታውቋል።

የሊባኖስ ጦር ተሽከርካሪ ላይ የተፈፀመው ጥቃት ካፈር ትበኒት በተባለ መንደር አቅራቢያ መንገድ ላይ የተፈፀመ ሲሆን፤ አካባቢው ባለፉት ወራት ከባድ ግጭት የተፋፋመበት እና ሰፊ መፈናቀል ያለበት ነው።

የእስራኤል ጦር ጥቃት የፈፀመበት ተሽከርካሪ ሄዝቦላህ ተልዕኮውን ያከናውንበታል በተባለ "ግጭት ባለበት እና ሰው በለቀቀበት የጦርነት ቀጣና" ሲጓዝ ነው ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የእስራኤል መከላከያ ባወጣው መግለጫ በአካባቢው የወታደሮች እንቅስቃሴ ከእስራኤል ጦር ጋር በቅንጅት መደረግ እንደሚያስፈልገው እና ኃይሉ "ተልዕኮውን የሚፈፅመው ከሄዝቦላህ ሽብርተኛ ቡድን እንጂ ከሊባኖስ ጦር ጋር" እንዳልሆነ ደጋግሞ ገልጿል።

የሊባኖስ ጦር ለጥቃቱ ቁጣ የተሞላበት ምላሽ የሰጠ ሲሆን እስራኤልን "ጨካኝ፣ ሆን ተብሎ የተፈፀመ እና ተደጋጋሚ ጠብ አጫሪ" ሲል ከስሷል።

ጦሩ ከመንደሩ አቅራቢያ መንገድ ዳር በእሳት የተቃጠለ ተሽከርካሪ ምሥልንም አጋርቷል።

ሟቾቹ ብርጋዴር ጀኔራል ሳመር ሳብራ፣ ካፒቴን ኤሊ ኾሮይ እና ወታደር ሀሰን ጋዛል ተብለው ተለይቷል።

የጥቃቱ ዜና የተሰማው አሜሪካ ያሸማገለችውን የእስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ሄዝቦላህ ውድቅ ካደረገ በኋላ ነው።

ስምምነቱ ሄዝቦላህ እስራኤልን የማያጠቃ ከሆነ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩት ጥቃት እንደማይፈፀም እንዲሁም በደቡባዊ ሊባኖስ ሄዝቦላህ የማይንቀሳቀስበት የሙከራ የደኅንነት ዞን መመስረትን ይደነግጋል።

የሄዝቦላህ መሪ ናይም ቃሲም ስምምነቱን ውድቅ በማድረግ፤ ሊባኖስን እና እስራኤልን "ከንቱ" ብለዋቸዋል።

የሊባኖስ መንግሥት በግዛቱ የሚደረገውን ጦርነት ማስቆም ይፈልጋል። ይህ ጦርነት ከዚህ ቀደም በዋና ከተማዋ ግዙፍ የአየር ጥቃቶችን ያካተተ ነበር።

የአገሪቱ ጦር ሄዝቦላህን መሣሪያ ለማስፈታት የተኩስ አቁም ወሳኝ እንደሆነ የተናገረ ሲሆን፤ እስራኤል ከዚህ ቀደም ግን የቤሩቱ መንግሥት ይህን ለማድረግ አቅሙ የለውም ስትል ተችታለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ስምምነት ለማሰር ሲሉ የሊባኖስን ግጭት የማርገብ ፍላጎት አላቸው።

ሊባኖስ በእስራኤል፣ አሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ሄዝቦላህ የቴህራንን ጠቅላይ መሪ በመገደሉ የአፃፋ ጥቃት ሲፈፅም ተስባ ገብታለች።

እስራኤል በሄዝቦላህ ለተፈፀመባት ጥቃት የአየር ጥቃቶች በመላው ሊባኖስ እና የምድር ወረራ በደቡባዊ ሊባኖስ በመክፈት መልስ ሰጥታለች።