አንድሪው ቴት እና ወንድሙ በቀረቡባቸው ተጨማሪ የፆታዊ ጥቃት ክሶች ምክንያት አሜሪካ ውስጥ ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አወዛጋቢው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ አንድሪው ቴት እና ወንድሙ ትሪስታን ቴት ላይ ዩናይትድ ኪንግደም ዐቃቤ ሕግ ተጨማሪ ክሶች እንደሚመሠርት ማሳወቁን ተከትሎ አሜሪካ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
አንድሪው ቴት ተጨማሪ የመድፈር ክሶች እንደሚቀርቡበት ተገልጿል። ለወሲብ ንግድ ከማዘዋወር እና ከሕጻናት ልቅ ወሲብ ጋር በተያያዘም ክሶች እንደሚመሠረቱ የዩኬ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ትሪስታን በወሲባዊ ትንኮሳ አንድ ክስ፣ በመድፈር ሁለት ክሶች እና ለወሲባዊ ብዝበዛ ሰዎችን ለማዘዋወር በማመቻቸት ሦስት ክሶች ቀርበውበታል።
ወንጀሎቹ ከአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2010 እስከ ነሐሴ 2017 የተፈጸሙ እንሆኑ ይታመናል። ወንድማማቾቹ ክሶችን አስተባብለዋል።
የዩኬ ዐቃቤ ሕግ ልዩ ወንጀል ክፍል ኃላፊ ማልኮም መክሀፊ "የቤድፎርድሺር ፖሊስ መዝገብ ውስጥ በተገኘው ተጨማሪ ማስረጃ መሠረት ክሶቹ እንዲከፈቱ ተወስኗል። አጠቃላይ የተጎጂዎች ቁጥር ሰባት ደርሷል" ብለዋል።
ያመለጡ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ምርመራ፣ የታራሚዎች ዝውውር እና የዐይን እማኞች ጥበቃ የሚያደርገው የአሜሪካ ማርሻል፤ ወንድማማቾቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ለቢቢሲ አረጋግጧል።
የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንዳሉት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ወንድማማቾቹ "ተላልፈው የሚሰጡ" ይሆናል።
የዩኬ ዐቃቤ ሕግ ወንድማማቾቹ ተላልፈው እንዲሰጡት ጠይቋል። አንድሪው እና ትሪስታን የዩኬ እና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት አላቸው።
የወንድማማቾቹ ተወካይ የሆነው ጠበቃ ጆሴፍ ማክብራይድ "አንድሪው እና ትሪስታን ንጹህ መሆናቸውን ዓለም ያውቃል" ሲል መግለጫ አውጥቷል።
"ከማንም በላይ ይሄንን የሚያውቁት ጠላቶቻቸው ናቸው። ዒላማ የተደረጉትም ለዚህ ነው" በማለትም አክሏል።
የዩኬ ክሶች "የፖለቲካ ምቶች" ናቸው ሲልም አጣጥሏል።
የክሶቹ ዓላማ ወንድማማቾቹ በአሜሪካ ያቀረቡትን የስም ማጥፋት ክስ መገዳደር እንደሆነ ተናግሯል።
"ብቁ ዳኛ እውነታውን ሲመለከቱ እና የፍትሕ ሚኒስቴር ሥልጣኑ መበዝበዙን ሲገነዘቡ አንድሪው ቴት እና ትሪስታን ቴት ነጻ እንደሚወጡ እርግጠኛ ነን። አሜሪካ የእንግሊዝን ቆሻሻ የፖለቲካ ሥራ አታስፈጽምም" ብሏል።
በአውሮፓውያኑ ግንቦት 2025 ዐቃቤ ሕግ ወንድማማቾቹ በዩኬ የሚቀርቡባቸውን 21 ክሶችን አረጋግጧል።
የ39 ዓመቱ አንድሪው እና የ37 ዓመቱ ትሪስታን ወንጀሎቹን ፈጽመዋል ተብሎ የሚታመነው ከአውሮፓውያኑ 2012 እስከ 2016 ነው።
በ2024 የቤድፎርድሺር ፖሊስ ወንድማማቾቹ ላይ የወንጀል ምርመራ ለመክፈት ከሮማኒያ ሲመለሱ በቁጥጥር ሥር ለማዋል በአውሮፓ ኅብረት አገራት የሚተገበር የእስር ፈቃድ አግኝቷል።
ሰኔ ላይ ወንድማማቾቹ የዩኬ ከሳሾቻቸውን ማንነት ለማወቅ ክስ ቢመሠርቱም ውድቅ ተደርጓል። ሕጋዊ እርምጃ እስከሚወሰድ ድረስ የተጎጂዎቹ ማንነት በምሥጢር እንዲያዝ ዐቃቤ ሕግ ወስኗል።




![አንድሪው [በስተቀኝ] እና ወንድሙ ትሪታን ቴት](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/660/cpsprodpb/fe8c/live/7cf87420-0fec-11ee-816c-eb33efffe2a0.jpg.webp)










