ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ቻይናን እና አውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ በበርካታ አገራት ላይ አዲስ ታሪፍ ጣለች
በታሪፍ የሚመራ የንግድ ፖሊሲ መለያቸው የሆነው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ቻይና፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ በበርካታ አገራት ላይ አዳዲስ ቀረጦችን ጣሉ።
ወደ አሜሪካ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የተጣሉት አዲሶቹ ታሪፎች ያነጣጠሩት የዋሽንግተን ትላልቅ የንግድ አጋር በሆኑ አገራት ላይ ነው። ታይዋን እና ሌሎች 12 ግዛቶችም የታሪፉ ዒላማ ሆነዋል።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም "የነፃነት ቀን" በሚል ስያሜ በርካታ የዓለም አገራት ላይ የጣሉት ታሪፍ በጠቅላይ ፍርድ ቤት 'ሕገ ወጥ' ተብሎ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም ዋይት ሐውስ ካለፈው መጋቢት አንስቶ የሌሎች ሀገራትን የንግድ አሰራር ሲመረምር ቆይቷል።
በአዲሱ ውሳኔ 40 በመቶ የሚሆነው ከፍተኛው የታሪፍ መጠን የተጣለባት ቻይና ናት። ቬትናም እስከ 35 በመቶ የሚደርስ ቀረጥ በመሸከም የምትከተል ሲሆን ሌሎች አገራት ደግሞ 20 ወይም 25 በመቶ ታሪፍ ይጠብቃቸዋል።
የአሜሪካ የንግድ ተወካይ መስሪያ ቤት ይህንን የታሪፍ እቅድ ይፋ ሲያደርግ፣ የእያንዳንዱ አገር ወይም አስተዳደር የንግድ አሰራር በአሜሪካ ንግድ ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የሚያሳዩ ሰፊ ሪፖርቶችን አብሮ አቅርቧል።
አዲሶቹ ቀረጦች ጥር ላይ እስከሚጀምረው አዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት ድረስ ተግባራዊ ይሆናሉ ተብሎ አይጠበቅም። ተፈጻሚ ከመሆናቸው በፊት ተከታታይ የሕዝብ ምክክሮችን ሂደቶችን ማለፍ ይኖርባቸዋል።
ታሪፍ ከአንድ አገር ወደሌላ በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣል ቀረጥ ነው። ብዙውን ጊዜም መጠኑ የሚሰላው ከዕቃው ዋጋ አንጻር በመቶኛ ነው።
ይህንን ቀረጥ ለመንግሥት የሚከፍሉት፣ ምርቱን ወደ አገር ውስጥ በሚያስገቡ የንግድ ድርጅቶች ናቸው።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ስምምነት ላይ የደረሱበት የታሪፍ ጣሪያዎች ገደብ በመኖሩ ከእነዚህ ታሪፎች ውስጥ አንዳንዶቹ መቀንስ ይኖርባቸዋል።
አዲሱ ታሪፍ ከቻይና፣ ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከሲንጋፖር፣ ከስዊዘርላንድ፣ ከኢንዶኔዥያ፣ ከማሌዥያ፣ ከካምቦዲያ፣ ከታይላንድ፣ ከኮሪያ፣ ከቬትናም፣ ከታይዋን፣ ከባንግላዴሽ፣ ከጃፓን እና ከህንድ በሚመጡ ዕቃዎች ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል።
የአሜሪካ የንግድ ተወካይ መስሪያ ቤቱ ኃላፊ ጄሚሰን ግሪር፣ አዲሶቹ ታሪፎች "የመጫወቻ ሜዳውን ለአሜሪካ ሠራተኞች እኩል ያደርጋሉ፤ ለዓለም ኢኮኖሚም አዲስ እና ይበልጥ ዘላቂ የሆነ አቅጣጫ ይፈጥራሉ" ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ብዙዎቹ የአሜሪካ የንግድ አጋሮች "ለአሥርት ዓመታት" አገሪቱን "አምራች ዘርፍ ዒላማ ማድረግን፣ ደመወዝን እና የሠራተኛ መጨቆንን" ያካተቱ የኢንዱስትሪ ስትራቴጂዎችን ሲከተሉ ቆይተዋል።
"የአሜሪካን የማምረት መሠረት እየሸረሸሩ፣ የንግድ ሚዛኑ ወደ እነርሱ እንዲያዘነብል የሚያደርጉ ሌሎች ገበያን የሚያዛቡ አሰራሮችን ተግብረዋል" ሲሉ ከስሰዋል።
የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ግን እንደዚህ ዓይነት ታሪፎች፣ ወጪያቸው ከፍ የሚልባቸው የንግድ ድርጅቶችን ጭማሪውን ወደ ሸማቹ እንዲያስተላልፉ እና በዚህም የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይናገራሉ። ዓለም አቀፍ ንግድን ሊያቀዛቅዙ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል።