የውጭ አገራት ወታደሮች ከሶማሊያ ሲወጡ አል ሻባብ የበላይነቱን ሊይዝ ይችላል?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 7 ደቂቃ

ሶማሊያ የውጭ አገራት ወታደሮች መውጣት በጀመሩበት፣ ለፀጥታ ኃይሎቿ የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ጫና ውስጥ በገባበት እና ከበርካታ አሥርት ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን ቀጥተኛ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ በተዘጋጀችበት ጊዜ ከባድ ፖለቲካዊ ውዝግብ ውስጥ በመግባቷ አዲስ ፈተና ገጥሟታል።

እነዚህ ተደራራቢ ችግሮች ፌደራል መንግሥቱ ከአል-ቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አል-ሸባብን እየተዋጋ በተመሳሳይ ጊዜ የተባባሰውን በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለውን ክፍፍል መቆጣጠር ይችል ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎችን አስነስቷል።

አንዳንድ ተንታኞች ሁኔታው አል-ሸባብን ሊያበረታታው እንደሚችል እና ቡድኑም በመጨረሻ ዋና ከተማዋን ሞቃዲሾ ሊቆጣጠር ይችላል ብለው ይሰጋሉ።

ቡድኑ ቀደም ሲልም መንግሥትን ለመደገፍ የተሰማሩ 12 ሺህ የሚሆኑ የአፍሪካ ኅብረት ወታደሮች ቢኖሩም የአገሪቱን ሰፋፊ ክፍሎች በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ይገኛል።

የውጭ አገራት ወታደሮች መውጣት እና ከተፎካካሪ የፖለቲካ ቡድኖች ጋር የተሰለፉ በጎሳ መሠረት ላይ የተደራጁ ሚሊሻዎች እንቅስቃሴ ማዕከላዊው መንግሥት ያለውን የቁጥጥር አቅም ማስጠበቅ ይችል ይሆን? የሚለውን ስጋት አባብሶታል።

ከአፍሪካ ኅብረት ወታደራዊ ኃይል ውስጥ ትልቁን ድርሻ የያዙት የኡጋንዳ ወታደሮች ካለፈው ወር ጀምሮ ከሶማሊያ መውጣት ጀምረዋል፤ ይህ ሂደተም እስከ ቀጣዩ ዓመት ድረስ ሙሉ በሙሉ እንደምታጠናቅቅ ይጠበቃል።

ከ7,000 በላይ ወታደሮችን ለአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ያበረከተችው ኢትዮጵያም 3,000 የሚሆኑ ወታደሮቿን ለማስወጣት እያቀደች መሆኑ ተዘግቧል።

ከዚህ ቀደም ለሶማሊያ ድጋፍ ለሚሰጠው የተባበሩት መንግሥታት ጽሕፈት ቤት የመደበችው ገንዘብ እንደሚቀንስ ያስታወቀችው አሜሪካ፣ በኋላ ግን ድጋፉን ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንደምታራዝም ገልጻለች።

ዋሽንግተን በዓመት 500 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋው ገንዘብ ለጽህፈቱ እንቅስቃሴ ታወጣለች። ይህ በጀት የሶማሊያን የፀጥታ ኃይሎች፣ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮዎችን እና ወታደሮችን ለሚያበረክቱ አገራት ድጋፍ የሚለውል ነው።

ሶማሊያ የምታገኘው ወታደራዊ ድጋፍ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ግልጽ ባልሆነበት እና አስተዳደሩ እየጨመሩ ከሚሄዱ የፖለቲካ ችግሮች ጋር በሚፋጠጥበት ወቅት፣ ተንታኞች የሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎች በራሳቸው ቆመው አገሪቱን ለመጠበቅ ዝግጁ ናቸው ወይ? የሚለውን ጥያቄ እያነሱ ነው።

እነዚህ ስጋቶች በቅርቡ አል-ሸባብ በፈጸመው ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሶማሊያ ልዩ ኃይል ወታደሮችን ገድያለሁ ማለቱን ተከትለው የበለጠ ተጠናክረዋል። መንግሥቱ ጥቃቱ መፈጸሙን ቢያረጋግጥም፣ የሟቾችን ቁጥር ግን አልገለጸም።

የሶማሊያ ብሔራዊ የደኅንነት ተቋም የቀድሞ ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አብዲሳላም ጉሌድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የደኅንነት ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

ጉሌድ እንዳሉት፣ የውጭ አገራት ወታደሮች መውጣት ሞቃዲሾን በ2021 የአሜሪካ እና የኔቶ ኃይሎች ከአፍጋኒስታን ከወጡ በኋላ ታሊባን ካቡልን እንደተቆጣጠረው ዓይነት የኃይል ቁጥጥር ለውጥ በማስከተል ለአል-ሸባብም ተጋላጭ ሊያደርጋት ይችላል።

"ሞቃዲሾ ራሷን መከላከል ትችላለች ብዬ አላስብም። አሁን ማሰብ የምችለው በጣም ሊሆን የሚችለው. . . የታሊባን ዓይነት ሥልጣንን መልሶ የመቆጣጠር ሁኔታ ነው" ብለዋል።

ታሊባን በአውሮፓውያኑ 2021 በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ፣ የአሜሪካ እና የኔቶ ኃይሎች ከአፍጋኒስታን ከወጡ በኋላ በፈጣን ዘመቻ መላውን አገር በቁጥጥሩ ሥር አስገብቶ ነበር።

ጉሌድ እንደሚያስረዱት፣ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ከዚህ ቀደም በሶማሊያ ተከስቶ ያውቃል።

ሶማሊያ ከዚህ ቀደምም የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ፈርሶ የነበረባት አገር ናት።

በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በጎሳ ላይ የተደራጁ አማፂ ቡድኖች ከበርካታ አቅጣጫዎች ወደ ሞቃዲሾ በመገስገስ የወቅቱን ፕሬዝዳንት መሐመድ ሲያድ ባሬን ከሥልጣን አባረሩ።

ይህም አውዳሚ የእርስ በርስ ጦርነትን እና ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የሰብዓዊ ቀውስን አስከትሏል። የመንግሥት ተቋማት መፈራረሳቸውም አል-ሸባብን ጨምሮ እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች ተጽዕኖአቸውን እንዲያሰፉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸው ነበር።

ጉሌድ እንደሚሉት፣ ከአውሮፓውያኑ 2007 ጀምሮ የኡጋንዳ ወታደሮች በሶማሊያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሰማሩ ወዲህ ተመሳሳይ የሥርዓት ውድቀት እንዳይደገም በማድረግ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።

እነሱ አል-ሸባብን ከሞቃዲሾ እና ከሌሎች ዋና ዋና ከተሞች በማስወጣት ረገድ ወሳኝ ሚና የተጫወቱ ሲሆን፣ አየር ማረፊያውን፣ ወደቡን፣ የመንግሥት ተቋማትን እና የዲፕሎማሲ ተቋማትን ጨምሮ ለስትራቴጂክ ቦታዎች ጥበቃ ሲያደርጉም ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ፣ የቡሩንዲ፣ የጂቡቲ፣ የኬንያ እና የሴራሊዮን ወታደሮችም የአፍሪካ ኅብረትን ተልዕኮ ተቀላቅለዋል። በተመሳሳይ ጊዜ ቱርክ እና አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች አገራት በተለየ መልኩ ወታደራዊ ኃይሎችን በማሰማራት ለሶማሊያ ኃይሎች ሥልጠና እና ትጥቅ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ሆኖም ጉሌድ እንደሚከራከሩት፣ ለዓመታት የተደረገው ዓለም አቀፍ ድጋፍ የሶማሊያ መንግሥት በራሱ ሊቆም የሚያስችለውን ያህል ወታደራዊ ነጻነት አልፈጠረለትም።

እንደ ጉሌድ ገለጻ፣ የሶማሊያ ባለሥልጣናት በውጭ ኃይሎች ጥበቃ ላይ እጅግ ከመመካታቸው የተነሳ የራሳቸው ኃይሎች ኃላፊነቱን ተረክበው እንዲሠሩ በበቂ ሁኔታ ለማዘጋጀት ቸልተኛ ሆነው ቆይተዋል።

የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስትር አብዲፈታህ ቃሲም ሞሐሙድ ግን አገሪቱ የውጭ አገር ወታደሮች ለቅቀው መውጣታቸው ችግር ላይ ሊጥላት ይችላል የሚሉትን አስተያየቶች አጣጥለዋል።

ሚኒስትሩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የሶማሊያ ጦር ኃይሎች ከዚህ ቀደም በኡጋንዳ ወታደሮች ተይዘው የነበሩ አንዳንድ ቦታዎችን ተረክበዋል፤ እንዲሁም ለአገሪቱ ደኅንነት የበለጠ ኃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ ናቸው።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ሶማሊያ ያለ ገደብ በውጭ ወታደሮች ጥበቃ ላይ ተመርኩዛ ልትቀጥል አትችልም።

"በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያስጨንቅ ምክንያት አለ ብዬ አላምንም። በአገሪቱ የደኅንነት ሁኔታም ሆነ እነሱ [የውጭ አገራት ወታደሮች] በለቀቋቸው አካባቢዎች ላይ ምንም ለውጥ አይኖርም" ብለዋል።

የውጭ አገራት ወታደሮች መውጣት የሚደቅነው ፈተና

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድም ቀጣይ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ነው።

በዚህ ሳምንት ወደ ኡጋንዳ ተጉዘው ባደረጉት ጉብኝት፣ ከኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ጋር በመሆን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሶማሊያ ያስመዘገበቻቸውን የደኅንነት ስኬቶች እንድታጠናክር ድጋፉን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ሆኖም ሁሉም ሰው የውጭ አገር ወታደሮች መውጣት የግድ ወደ የደኅንነት ውድቀት ያመራል ብሎ አያምንም።

የኡጋንዳ የደኅንነት ተንታኝ ፍሬዲ ዴቪድ ኤጌሳ እንደሚሉት፣ ለዓመታት የተደረገው ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ድጋፍ ሶማሊያ ለራሷ ደኅንነት የበለጠ ኃላፊነቱን እንድትሸከም የሚያስችሏትን ተቋማት እንድትገነባ ረድቷታል።

እርሳቸው እንደሚያስረዱት፣ የውጭ ኃይሎች መውጣት ሶማሊያ እስካሁን ያስመዘገበችውን ውጤት ለመለካት አጋጣሚ ይፈጥራል።

በተጨማሪም የሶማሊያ የፖለቲካ መሪዎች ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው ለአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የበለጠ ኃላፊነት እንዲወስዱም ግፊት ያደርግባቸዋል ብለዋል።

ሌሎች ተንታኞች ግን የወቅቱ ሁኔታ ከዚህ የባሰ ሊሆን አይችልም ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

በዓለም ዙሪያ የሚከሰቱ ቀውሶችን በሚከታተለው በኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ የሶማሊያ ጉዳይ ተንታኝ የሆኑት ኦማር ማህሙድ እንደሚሉት፣ የሶማሊያ ጦር ሠራዊት አል-ሸባብን እየተዋጉ በተመሳሳይ ጊዜ ቀደም ሲል በውጭ ወታደሮች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ለመረከብ ሲሞክሩ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይገኛሉ።

እርሳቸው እንደሚያስረዱት፣ ይህ ገና በእድገት ላይ ላለ ሠራዊት ቀላል ያልሆነ ትልቅ ተልዕኮ ነው።

በተጨማሪም ሠራዊቱ በደቡብ ምዕራብ ግዛት በሚገኘው የቤይ ክልል ተጨማሪ ጫና ውስጥ ነው። እዚያ ከሥልጣን ከተወገዱት የክልሉ ፕሬዝዳንት የአብድያዚዝ ሐሰን መሐመድ ታማኝነት ኃይሎች ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር እየተዋጉ ነው።

ማህሙድ እንደሚሉት፣ የኡጋንዳ ወታደሮች ከታችኛው ሻበሌ ክልል መውጣት ተጨማሪ የደኅንነት ተግዳሮቶችን ሊፈጥር ይችላል።

ማህሙድ በተጨማሪም ለረጅም ጊዜ የዘገዩት የሶማሊያ ምርጫዎች፣ የደኅንነት ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸው፣ የደኅንነት ሁኔታውን የበለጠ የሚያወሳስቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ይጠቁማሉ።

ሶማሊያ እስካሁን ስትከተለው የቆየውን ተዘዋዋሪ የምርጫ ሥርዓትን ለመተው እየሞከረች ነው። በዚህ ሥርዓት የጎሳ መሪዎች የፓርላማ አባላትን ይመርጣሉ፤ ከዚያም እነዚህ ተወካዮች ፕሬዝዳንቱን ይመርጣሉ። በምትኩ አገሪቱ ወደ ቀጥተኛ የሕዝብ ድምፅ ምርጫ ሥርዓት ለመሸጋገር እየጣረች ነው።

ማህሙድ እንደሚሉት፣ ከወታደራዊው ሁኔታ ባሻገር መንግሥቱ በአገሪቱ ምርጫዎች የሚደረጉበትን ጊዜና ቅርፅን በተመለከተ እየተባባሰ የመጣውን የፖለቲካ ውዝግብ መፍታትም ይኖርበታል።

ሆኖም የታቀደው የምርጫ ሥርዓት ለውጥ መንግሥትን እና ተቃዋሚዎችን ከፋፍለዋል። ምርጫው እንዴት መካሄድ እንዳለበት በሚመለከት ከፍተኛ ልዩነቶች አሉ።

ይህ ውዝግብ በዚህ ዓመት የበለጠ ተባብሷል። ምክንያቱም ፕሬዝዳንቱ የፕሬዝዳንትነት የሥልጣን ዘመንን ከአራት ዓመት ወደ አምስት ዓመት የሚያራዝሙ የሕገ መንግሥት ማሻሻያን አፅድቀዋል። ይህም በተግባር ቀጣዩ ምርጫ እስከ 2027 እንዲራዘም አድርጓል።

ነገር ግን የሶማሊያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፕሬዝዳንቱን የሥልጣን ዘመን ማራዘሚያ ውሳኔ ውድቅ በማድረግ፣ የፖለቲካ መሪዎች በ30 ቀናት ውስጥ በቀጣይ ምርጫ ዕቅድ ላይ እንዲስማሙ እና ምርጫውም በሦስት ወራት ውስጥ እንዲካሄድ አዝዟል።

አስተዳደሩ ግን ውሳኔውን እንደማይቀበል ገልጿል።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከመሰጠቱ አንድ ቀን በፊት፣ ፕሬዝዳንቱ ዋና ዳኛውን ባሼ ዩሱፍ አህመድን ከሥልጣናቸው አንስተዋቸው ነበር። በኋላም ይህ የሥልጣን ማባረር ጉዳይ በታንዛኒያ በሚገኘው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦበታል።

ማህሙድ እንደሚሉት፣ የፖለቲካው እና የደኅንነት ቀውስ በጣም የተቆራኙ ናቸው። በምርጫው ጉዳይ ላይ መግባባት አለመኖሩ መንግሥት በአል-ሸባብ ላይ በሚያካሂደው ዘመቻ ላይ በቂ ትኩረት እንዳያደርግ እያደረገው ነው።

ጉሌድም ይህ ለሶማሊያ መረጋጋት የሚደቅነው አደጋ ከአል-ሸባብ ብቻ የሚመጣ አለመሆኑን ያስጠነቅቃሉ። በጎሳ የተደራጁ ሚሊሻዎች በፌዴራል መንግሥቱ ላይ የሚያሳድሩት ጫናን እያበረቱ ነው ብለዋል።

"ዛሬ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በሚደረገው ውጊያ ከአል-ሸባብ ጎን ተሰልፈው የሚዋጉ የጎሳ ታማኞች አሉ" ሲሉም ተናግረዋል።

አክለውም የአገሪቱ አመራር ወደፊት የሚመጡትን ተግዳሮቶች ስፋት አስቀድሞ መገመት ያልቻለ ይመስላል ብለዋል።

የውጭ አጋሮች የሚፈጥሩትን ክፍተት ማን ይሞላዋል?

የሶማሊያ የደኅንነት ተግዳሮቶች በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ ላይ ባላት ከፍተኛ ጥገኝነት የበለጠ እየተወሳሰቡ መጥተዋል።

ከአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስቴር የወጣው የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በ2026 ከታቀደው 1.36 ቢሊዮን ዶላር በጀት ውስጥ 878.8 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ማለትም ሁለት ሦስተኛው ድርሻ ከለጋሽ አጋሮች በሚገኝ ድጎማ የሚሸፈን ነው።

ነገር ግን የሶማሊያ የገንዘብ ሚኒስቴር በዚህ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ውስጥ 314 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ድጎማ ብቻ እንደተቀበለ ገልጿል። ይህም ለዓመቱ ከሚጠበቀው አጠቃላይ የእርዳታ ገንዘብ 35 በመቶውን ብቻ የሚሸፍን ነው።

ማህሙድ እንደሚያምኑት፣ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ድጋፎች እየቀነሱ ቢሆንም፣ ሌሎች አጋር አገራት በሁለትዮሽ ስምምነቶች እና በቀጣይ ድጋፍ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት ሊረዱ ይችላሉ።

ሆኖም ጉሌድ እንደ ቱርክ፣ ኳታር እና ግብፅ ያሉ አገራት የኡጋንዳን እና የአሜሪካን ወታደራዊ እና የገንዘብ አስተዋጽኦ በፍጥነት መተካት ይችላሉ ብለው አያምኑም።

እንደ ጉሌድ ገለጻ፣ ሶማሊያ በውጭ ድጋፍ ላይ እጅግ የተመረኮዘች በመሆኗ፣ ዓለም አቀፍ አጋሮቿ ትኩረታቸውን በሚቀይሩበት ጊዜ በቀላሉ ተጋላጭ ትሆናለች።

ይህ ጥገኝነት ከአንዳንድ የውጭ መንግሥታት ጋር ያላት ግንኙነት እየተሻከረ እንዲሄድ ምክንያት ሆኗል።

በቅርቡም ሶማሊያ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (ዩኤኢ) የታጠቁ ቡድኖችን በገንዘብ እየደገፈች እና የአገሪቱን ሉዓላዊነት እያዳከመች ነው በማለት ከሳለች። ይህም አገሪቱ ውስጥ ጉልህ የደኅንነት እና የኢኮኖሚ ፍላጎቶች ካላቸው የውጭ ኃይሎች ጋር ከተከሰቱ ውዝግቦች የቅርብ ጊዜው ነው።

ኤምሬትስ የቀረበባትን ክስ ውድቅ አድርጋ የሶማሊያውን መሪ በፕሬዝዳንታዊ የሥልጣን ዘመናቸው ዙሪያ ያለውን ውዝግብ በመጥቀስ "ሥልጣናቸውን የሚያስረክቡ ፕሬዝዳንት" ስትል ገልጻቸዋለች።

ምንም እንኳን ኤምሬትስ ለረጅም ጊዜ የሶማሊያ ጠቃሚ የደኅንነት እና የኢኮኖሚ አጋር ሆና ብትቆይም በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ሁለቱ አገራት ላይ ግንኙነታቸውን በይፋ አቋርጠዋል።

ሁኔታው ባልለየበት በአሁኑ ወቅት ኡጋንዳው የደኅንነት ተንታኝ ኤጌሳ፣ የውጭ አገራት ወታደሮች መውጣት ሶማሊያ የደኅንነት ተቋማቷን በድጋሚ በመገንባት ረገድ ምን ያህል ውጤት እንዳስመዘገበች ለማሳየት ጠቃሚ ዕድል ሊፈጥር ይችላል ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚያምኑት፣ ወታደሮቹ ደረጃ በደረጃ መውጣታቸው የሶማሊያ ኃይሎች ኃላፊነትን ቀስ በቀስ እንዲረከቡ ያስችላል፤ በተመሳሳይም ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች አብረው እንዲሠሩ ግፊት ያደርግባቸዋል።

ጉሌድ ግን ከዚህ በተለየ መልኩ አስተያየት ይሰጣሉ።

ሶማሊያ ወታደራዊ ድክመቷን፣ ፖለቲካዊ ክፍፍሏን እና የታጠቁ ቡድኖች እያደገ የሚሄደውን ተጽዕኖን ካልፈታች፣ እስካሁን ያገኘቻቸው የደኅንነት ስኬቶች ሊቀለበሱ የሚችሉበት አደጋ እንዳለ ይከራከራሉ።

በአሁኑ ወቅት ሶማሊያ ሥር ከሰደደው አማፂ ቡድን ጋር መዋጋት፣ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፍላጎቶችን ማስታረቅ እና አከራካሪ ሊሆን ለሚችል የምርጫ ሂደት መዘጋጀት የሚሉ ከባድ ተግባራት ከፊቷ ተደቅነዋል። ይህ ደግሞ የሚሆነው አንዳንድ ወታደራዊ አጋሮቿ ለመውጣት በሚዘጋጁበት ወቅት ነው።

ሶማሊያ እነዚህን ጫናዎች አዲስ የፀጥታ ወይም የፖለቲካ ቀውስ ሳያስከትሉ መቋቋም ትችል ይሆን? የሚለው ጥያቄ አሁንም ግልጽ መልስ ያላገኘ ሆኖ ቀጥሏል።