አሜሪካ በጠፈር ላይ ምን ዓይነት የጦር መሣሪያዎች አሏት?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

አሜሪካ የመሬት ምኅዋር ላይ የጦር መሣሪያ እንዳላት ይፋ ማድረጓን ተከትሎ በህዋ ላይ በእርግጥ ምን ዓይነት የጦር መሣሪያዎች እንዳሉ እና ኃይላት አገራት ጠፈሩን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የጦር መሣሪያዎቹ ምን ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል ጥያቄዎችን አስነስቷል።

የአሜሪካ አየር ኃይል አዛዥ ትሮይ ሜንክ በመሬት ምኅዋር ላይ ያሉት መሣሪያዎች የአሜሪካ ኃይሎችን ከጠላት ጥቃት ለመጠበቅ አስፈላጊ መሆናቸውን ቢናገሩም፤ ስለ መሣሪያዎቹ አቅም ወይም መቼ ህዋ ላይ እንደተተከሉ ምንም ዓይነት ዝርዝር አልተሰጠም።

ታዲያ ይህ መሣሪያ ምን ሊሆን ይችላል? በጠፈር ላይ ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ አጠቃላይ ገጽታስ ምን ይመስላል? ተመሳሳይ መሣሪያ ያላቸው ሌሎች አገራትስ እነማን ሊሆኑ ይችላሉ?

የህዋ አሰሳ ዘመን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ጠፈር ለወታደራዊ እንቅስቃሴ መድረክ መሆን እንደጀመረ ይነገራል። በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ መገባደጃ ላይ ሶቪየት ኅብረት በጠፈር ላይ የጦር መሣሪያዎችን አሰማርታ ነበር።

"ኢስትሬቢቴል ስፑትኒኮቭ" (አይኤስ) የተባለው የሳተላይት አውዳሚ ፕሮግራም ሌሎችን ሳተላይቶች በተለይም የአሜሪካን ለማጥፋት የታሰቡ ሳተላይቶችን የያዘ ነበር። እነዚህ ሳተላይቶች የሚፈነዱ ተወንጫፊዎችን በመተኮስ ሲፈነዱ ፍንጣሪዎቹ በሌሎች ሳተላይቶች መስመር ላይ ይሠራጫሉ።

በአሁኑ ጊዜ ዘመናዊ ወታደራዊ ኃይሎች በጠፈር ውስጥ ሳተላይቶችን ለተለያዩ ዓላማዎች ያሰማራሉ። ከእነዚህም መካከል መረጃ መሰብሰብ፣ የግንኙነቶቻቸውን ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የሚሳዔል ጥቃቶችን ቀድሞ ማወቅ እና ለሚፈጽሟቸው ጥቃቶች የዒላማዎችን ትክክለኛ ቦታ መረጃ መስጠት ይገኙበታል።

ጦርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በቴክኖሎጂ እየተመራ በመምጣቱ፣ ተንታኞች በጠፈር ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ መሣሪያዎች አጠቃቀም ወደፊት የበለጠ እንደሚጨምር ይጠብቃሉ።

ዶክተር ብሌዲን ቦዌን፣ በሮያል ዩናይትድ ሰርቪሲዝ ኢንስቲትዩት የወታደራዊ ሳይንስ ተባባሪ ባለሙያ እና በዱርሃም ዩኒቨርሲቲ የህዋ ፖለቲካ ተባባሪ ፕሮፌሰር፣ አሜሪካ ይፋ ስላደረገችው የጠፈር መሣሪያ ትክክለኛ መረጃ ባለመኖሩ ግምት ከመስጠት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም ብለዋል።

"በእኔ ግምት ይህ ምናልባት አንድ ዓይነት የኤሌክትሮኒክ ጦርነት ወይም የሬዲዮ መልዕክት ማደናቀፊያ መድረክ ሊሆን ይችላል። ይህም ሳተላይቶችን ሳያወድም የሚያሰናክል ዓይነት ፀረ-ሳተላይት መሣሪያ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ለቢቢሲ ሬዲዮ 4 "ቱዴይ" ፕሮግራም ገልጸዋል። "የሬዲዮ ግንኙነት መስመሮቹን ካቋረጡ፣ ሳተላይቱ ብዙም ጥቅም አይኖረውም" ብለዋል።

እንዲህ ያሉ መሣሪያዎች አሁንም በምድር ላይ እንዳሉ እና የሳተላይት የመገናኛ ሥርዓቶችን ሊያደናቅፉ እንደሚችሉም ገልጸዋል።

ቦዌን በተጨማሪም እንዲህ ያለው መሣሪያ በጠፈር ውስጥ ስብርባሪዎችን በመፍጠር የበለጠ አደገኛ እና ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ዓይነት መሣሪያ ሊሆን ይችላል ብለው ያምናሉ።

ከአሜሪካ በተጨማሪ ሩሲያ እና ቻይናን የመሳሰሉ ተፎካካሪ ኃያላን አገራት ተመሳሳይ መሣሪያዎችን አስቀድመው በምድር ምህዋር ላይ ተክለው እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።

የሮያል ዩናይትድ ሰርቪሲዝ ኢንስቲትዩት የቀድሞ ተመራማሪ እና በጀርመኑ የሳይንስ እና ፖሊሲ ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ጁሊያና ዙስ ለቢቢሲ "ቻይናን እና ሩሲያን ከተመለከትን፣ ሁለቱም በዚህ መስክ እንቅስቃሴዎችን ሲያከናውኑ ታይተዋል" ብለዋል።

"ለምሳሌ፣ በሩሲያ ጉዳይ ላይ ከምህዋር ላይ የሚሠራ የጦር መሣሪያ ሙከራ የተደረገ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ እንቅስቃሴዎችን አይተናል። ስለዚህም በምህዋር ውስጥ እንደ ሙከራ አንድ ተወንጫፊ ተተኩሶ ሊሆን እንደሚችል ተመልክተናል።"

"ከዚህ በተጨማሪ ሌሎችም ተመሳሳይ መሣሪያዎች በዓለም ላይ አሉ፤ ሆኖም የአሜሪካው መሣሪያ በትክክል ምን እንደሆነ ዝርዝር መረጃ ሳይኖር፣ ቀጥተኛ ንጽጽር ማድረግ አስቸጋሪ ነው" ሲሉ አክለዋል።

ነገር ግን ወደ ምኅዋር የተላከው መሣሪያ ያልተለመደ ሊሆን ቢችልም፣ አሜሪካም ሆነች ተቀናቃኞቿ ሩሲያ እና ቻይና ወደ ጠፈር የተነጣጠሩ እና ሊተኩሱ የሚችሉ መሣሪያዎች ከረጅም ጊዜ ጀምሮ አላቸው።

ቦዌን ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ቻይና አሜሪካ ይፋ ያደረገችውን መረጃ በመተቸት በጠፈር ላይ የጦር መሣሪያ ፉክክር እንዳይፈጠር የሰነዘረችውን ማስጠንቀቂያ አጣጥለውታል።

"አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና እንዲሁም ሕንድ የተለያዩ ዓይነት ፀረ-ሳተላይት ወይም ፀረ የጠፈር ጦር መሣሪያዎችን አዘጋጅተዋል፤ በተጨማሪም ሩሲያ እና ቻይና ከፍተኛ የጦር አቅም ሊኖራቸው የሚችሉ በርካታ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ጠፈር አሰማርተዋል" ሲሉ አክለዋል።

በእርግጥም ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ሩሲያ እና ቻይና በጠፈር ላይ እንቅስቃሴዎችን ሲያከናውኑ ነበር። እነዚህም የምዕራባውያን ሳተላይቶችን በጣም ቀርበው በመከታተል ወይም በመጠጋት ቅኝት ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

"በንድፈ ሀሳብ ደረጃ፣ እነዚህ የቅኝት ሳተላይቶች ከሌሎች ሳተላይቶች ጋር በቀጥታ በመጋጨት ወይም ከምህዋራቸው በማፈናቀል 'አድኖ-ገዳይ' ሳተላይቶች ሊባሉ ይችላሉ" ሲሉ በለንደን የኪንግስ ኮሌጅ የሩሲያ መከላከያ እና የደኅንነት ጥናቶች መምህር ዶክተር ሮድ ቶርንተን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቦዌንም በበኩላቸው ቻይና "በጠፈር ፉክክር ላይ አቅም እንዳላት" ማሳየቷን ጠቅሰው፣ ይህም ለምሳሌ በጠፈር ላይ የተተተዉ አላስፈላጊ ቁሶችን ለማስወገድ እንዲሁም በሥራ ላይ ያሉ ሳተላይቶችን ከአገልግሎት ውጪ ለማድረግ ሊውል ይችላል።

ሆኖም አንዳንድ የጠፈር መሣሪያዎች እጅግ ብዙ የጠፈር ስብርባሪዎችን የመፍጠር አደጋም አላቸው።

በኪንግስ ኮሌጅ የጠፈር ደኅንነት እና የጦር መሣሪያ አጠቃቀም ልዩ ባለሙያ ዶክተር ማርክ ሂልቦርን እንዳሉት፣ ቻይና በአውሮፓውያኑ 2007 ያካሄደችውን የቀጥታ ፀረ-ሳተላይት ሚሳዔል ሙከራን የመሳሰሉ ተግባራት በምህዋር ላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ብዙ ስብርባሪዎችን ይተዋሉ።

ሱስ በበኩላቸው፣ በዚያ ሙከራ ምክንያት የተፈጠረው ስብርባሪ አሁንም በምኅዋር ውስጥ እንዳለ እና አደገኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

"ጉዳት ለማድረስ የግድ ትልቅ የብረት ቁራጭ አያስፈልግም። በምኅዋር ላይ ስለምናወራው ከፍተኛ ፍጥነት ሲታሰብ፣ ትንሽ የፕላስቲክ ቁራጭ እንኳን ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል" ብለዋል።

የኒውክሌር ስጋት

ቶርንተን እንዳሉት፣ ሩሲያ በጠፈር ውስጥ ባሏት የጦር መሣሪያዎች እና ሳተላይቶች ብዛት ላይ ያለባትን እጥረት፣ በሚሳዔል አቅሟ ታካክሰዋለች።

"ሩሲያውያኑ...ወደ ጠፈር ተወንጭፈው በዝቅተኛ የምድር ምህዋር የሚገኙ ሳተላይቶችን ሊመቱ የሚችሉ በምድር ላይ የተተከሉ ሚሳዔሎች አሏቸው። በተጨማሪም በጣም ከፍ ብለው በሚበሩ አውሮፕላኖች የሚወነጨፉ ፀረ-ሳተላይት ሚሳዔሎችም አሏቸው" ሲሉ ተናግረዋል።

"ከሩሲያ አንፃር፣ ኔቶ ከሩሲያ ጦር ኃይል በበለጠ በርካታ እና የተሻሉ ሳተላይቶች እንዳሉት ይመለከታሉ። ስለዚህም የጦርነቱን ሚዛን በከፊል ለማስተካከል ሲሉ በፀረ-ሳተላይት መሣሪያዎች ላይ ብዙ ገንዘብ አፍስሰዋል" ብለዋል።

ቶርንተን አሳሳቢ የሆነ ሌላ ሃሳብም ጨምረዋል "እንደ መጨረሻ አማራጭ፣ ሩሲያውያኑ የኒውክሌር መሣሪያዎችን ወደ ጠፈር ሊያስወነጭፉ ይችላሉ፤ በዚህም የሚፈጠረው የኒውክሌር ኤሌክትሮማግኔቲክ ንዝረት በሰፊ አካባቢ ያሉ ያልተጠበቁ ሳተላይቶችን ሙሉ በሙሉ ከሥራ ውጭ ሊያደርጋቸው ይችላል።"

ታዲያ በጠፈር ላይ የኒውክሌር ጦርነት የመፈጠር ዕድሉ ምን ያህል ነው? ይህ በአብዛኛው ሊፈጠር የሚችለው በምድር ላይ የኒውክሌር ጦርነት በተመሳሳይ ጊዜ ከተከሰተ ብቻ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ነው።

ቦዌን "በጠፈር ላይ ጦርነት ሊከሰት የሚችለው ብቻውን ተነጥሎ አይደለም" በማለት "ምንም ላይከሰት ይችላል፤ ወይም ደግሞ ብዙ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ።"

በጠፈር ውስጥ የሚጠቀሙባቸው መሣሪያዎች ለረጅም ጊዜ ሲኖሩ ከቆዩ፣ አሜሪካ ይህን ማስታወቂያ በዚህ ወቅት ለምን አወጣች?

ይህ በህዋ ላይ የጦር መሣሪያን የማስቀመጥ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ሲነዳ የነበረ ቢሆንም አሜሪካ አሁን ለምን ይፋ ማድረግ ፈለገች? ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን ጉዳዩ አዲስ ክስተት ሳይሆን ፖለቲካዊ መልዕክት ለማስተላለፍ የታለመ ነው።

ቦዌን እንደሚያምኑት፣ ይህ እርምጃ ቻይና እያዳበረችው ላለው የህዋ ተሳትፎ እና ለተመዘገቡ እድገቶች የተሰጠ ምላሽ ሊሆን ይችላል።

"ቻይና ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ የወታደራዊ ኃይሏን በእጅጉ አዘምናለች" ብለዋል። "ብዙ ተጨማሪ ወታደራዊ ሳተላይቶችን ወደ ጠፈር አሰማርታለች፤ እንዲሁም የአሜሪካንን ጦር ትኩረት የሚስቡ በርካታ አዳዲስ ዒላማዎችን ፈጥራለች።"

ከዚህ አንጻር አሁን "አሜሪካ የጠፈር መሣሪያዎችን ማዳበር የበለጠ ፍላጎት አላት፤ ምክንያቱም ቻይናም ልክ እንደ አሜሪካ በጠፈር ላይ የተቀመጡ የጦር መሣሪያ ሥርዓቶችን በብዛት ስለምትጠቀም፣ ለተመሳሳይ ስጋት ተጋልጣለች" ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ አስገራሚ የኃይል አለመመጣጠን ፈጥሯል ተብሏል።

ቶርንተን እንደገለጹት፣ በማንኛውም የጠፈር ጦርነት ውስጥ ሩሲያ "ትልቋ አሸናፊ" ልትሆን ትችላለች፤ ምክንያቱም ከአሜሪካ እና ከቻይና ጋር ሲነጻጸር በጠፈር ላይ ያሏት ሳተላይቶች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው።

"እንዲህ ዓይነቱ ግጭት ወደ ጠፈር በሚተኮሱ ሚሳዔሎች፣ ሌሎች ሳተላይቶችን ለማፈናቀል ወይም ለማጥፋት ተብለው በተነደፉ ተንቀሳቃሽ ሳተላይቶች፣ እንዲሁም ከመሬት ላይ በሚሠሩ የጨረር ሥርዓቶች ሊካሄድ ይችላል" ብለዋል።